መስከረም 13 ፣ 2013

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት፣ የአዲስ አበባ የሚኒባስ ታክሲዎችና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደዋነኛ ችግር ከሚነሱ ነገሮች አንዱ የትራንስፖርት ችግር ነው። በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በስራ መውጫና መግቢያ…

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት፣ የአዲስ አበባ የሚኒባስ ታክሲዎችና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደዋነኛ ችግር ከሚነሱ ነገሮች አንዱ የትራንስፖርት ችግር ነው። በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓታት ረጅም ሰልፎችን መመልከት የተለመደ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። መሳይ ሸምሱ የመንገድ አጠቃቀም ፍትሃዊነት በተሰኘው ፕሮግራሙ ላይ ይህን የከተማዋን ችግር ለማስረዳት ሲሞክር ሰዎች በአሁን ጊዜ የሚኖሩባቸው ከተሞች ከጥንታዊ አነስተኛ ከተሞች በተለየ በመጠናቸው ትልቅ በመሆናቸው በየእለቱ ተራምደው የማይጓዙባቸውን ርቀቶች ለመጓዝ መሞከራቸውን እንደዋቢነት ያነሳል። የትራንስፖርት ኢንጅነሩ መሳይ አክሎም በአዲስ አበባ ከተማ የግል መኪና ተጠቃሚ ነዋሪዎች ከ15 በመቶ እንደማይበልጡ አስታውሶ የተቀሩት የከተማዋ ነዋሪዎች በአንፃሩ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንደሆኑ በፕሮግራሙ ላይ ያናገራል። ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መካከል ደግሞ ሚኒባስ ታክሲዎች በተቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ መሳይ ይናገራል። ይህ ከተማዊ ችግር በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ከተባባሱ የአዲስ አበባ ከተማ ተግዳሮቶች መካከልም አንዱ ነው። ወረርሺኙ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት በግማሽ አቅም እንዲሰጥ መወሰኑ አንዱ ሲሆን ይህ አሰራር በቫይረሱ አማካኝነት ወጥቶ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተተገበረበት አምስት ወራት ውስጥ ሲሰራበት ቆይቷል። ነገር ግን የተቀጠረለት የአምስት ወር ቀጠሮ መጠናቀቁን ተከትሎ ይህ አሰራር ተቀይሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሙሉ አቅማቸው መስራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ውሳኔው ከተለያዩ አቅጣጫዎች መታየት አለበት ይላል የትራንስፖርት ኢንጅነሩ መሳይ ሸምሱ። “ይህን ውሳኔ ለመወሰን ሊሰጡ የሚችሉት ምክንያቶች ሁለት ናቸው። አንደኛ ከኢኮኖሚው አንፃር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትራንስፖርት እጥረቱ የተነሳ ነው። ከእነዚህ መመዠኛዎች አንፃር ውሳኔውን የምታየው ከሆነ ውሳኔው አሳማኝ ነው።” በማለት ሀሳቡን የሚያስቀምጠው መሳይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አንፃር ግን ውሳኔው ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ብሎ እንደሚያምን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። የአፍና የአፍንጫ ማስኮችን አለመጠቀምና ትርፍ መጫንን ጨምሮ የተለያዪ አስጊ የሚላቸውን ጉዳዮች እንደምክያትነት ያነሳው መሳይ ከዚህ በተጨማሪ በታሪፍና በስምሪት ላይ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮችን እንደታዘበም ተናግሯል። ታድያ ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትና ከተለያዩ ጉዳዮች አንፃር በግማሽና በሙሉ አቅም በመጫን ወቅት ምን መታዘብ ይቻላል? አዲስ ዘይቤ በታክሲ ትራንስፖርት ዘርፉ የተሰማሩ የታክሲ ሹፌሮች፣ ተራ አስከባሪዎች፣ ረዳቶችንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የከተማዋ ነዋሪዎችን አነጋግራለች።ከአጎና ወደ ደምበል መንገድ ባለው መንገድ ላይ በታክሲ አስከባሪነት ተሰማርቶ የሚተዳደረው በሀይሉ ብርሀኔ በበኩሉ ታክሲዎች በሙሉ አቅም መጫን መጀመራቸውን ተከትሎ በህዝቡ ላይ የበለጠ መዘናጋትን እንዳመጣ ያምናል። “ምንም እንኳን የበለጠ የሚከፍልበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፣ ህብረተሰቡ በግማሽ በሚጫንበት ወቅት የተሻለ ጥንቃቄም ሆነ  ትብብር ይታይበት ነበር።” በማለት ከዚህ ቀደም የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሰው በሀይሉ ውሳኔው ከተወሰደ ጀምሮ የአፍና የአፍንጫ ማስክን ካለማድረግ አንስቶ የተለያዩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎች መቀነሳቸውን አስረግጦ ይናገራል። በሀይሉ አክሎም ውሳኔውን ተከትሎ የተለያዩ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች በመኖራቸው አንዳንድ ክፍተቶች እንደሚታዩ የተናገረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የተሳፋሪዎች ከኋላ ወንበር ለመግባት አለመፈለግና ይህን ተከትሎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እንደምክንያትነት ያነሳል። አሁንም ቢሆን መንግስት ለተራ አስከባሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚለው በሀይሉ ምንም እንኳን ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ቢሰጋም ውሳኔውን ተከትሎ ግን በአካባቢው የሚታየው የሰልፍ ችግር መስተካከሉን ግን እንደውሳኔው መልካም ጎን ሳያነሳ አላለፈም።ተጠቃሚዎች ዘንድ ያለው ምልከታም ተመሳሳይ ነው። በየቀኑ ከአያት አካባቢ ወደ ልደታ በመመላለስ በግል ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ዘመድኩን አለሙ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረው ከሆነ በእርሱም ዘንድ በሙሉ አቅም የመጫን ውሳኔው ከመወሰኑ አስቀድሞ የተሻለ ጥንቃቄ እንደነበረ ይገልፃል። “ውሳኔው በመወሰኑ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም የተሻለ የትራንስፖርት አቅራቦት አሁን አለ። በተጨማሪም እንደኔ አቅማቸው ከፍ ዝቅተኛ ለሆነ ሰዎች ታሪፉን በመክፈልና እጥፍ በመክፈል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ።” የሚለው ዘመድኩን ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ውሳኔው ለቫይረሱ ይደረግ የነበረውን ጥንቃቄ እንደቀነሰ በሙሉ እምነት ይናገራል። ዘመድኩን ብዙሀኑ ህዝብ በሚጠቀማቸው የሚኒባስ ታክሲዎች ላይ የሚመለከተውን መዘናጋት ሲገልፅ “ትርፍ መጫን፣ ማስክ አላደርግም ማለት፣ አካላዊ ንክኪን ማድረግና ሌሎች የተለያዩ ስጋትህን የሚያሳድጉ ድርጊቶችን ትመለከታለህ። ያለምንም ጥርጥር ከአሁን ይልቅ በግማሽ በሚጫንበት ወቅት የተሻለ ደህንነት ይሰማኝ ነበር።” ይላል። ከከተማዋ በተቃራኒ የምትኖረው ማክዳ እውነቱ በበኩሏ አዲሱ ገበያ ከሚገኘው ቤቷ ቦሌ ማተምያ አካባቢ ወዳለው የስራ ቦታዋ ለመሄድ ቢያንስ ሁለት ታክሲዎችን ለመያዝ ትገደዳለች። ማክዳ ከቤት መውጣት በራሱ ይዞት የሚመጣው ስነልቦናዊ ጫና እንዳለው ትናገራለች። የህይወት ጥያቄ ባይሆን ኖሮ ከመኖርያ ቤቷ እንደማትወጣ የምትናገረው ማክዳ “በህዝብ ማመላለሻ ታክሲዎች ላይ አንዳንዴ የምትመለከተው ነገር ግራ ያጋባል። ትርፍ ካልተጫንን የሚሉ ሰዎች ጋር ከመጨቃጨቅ አንስቶ መስኮት መክፈት የማይቻልባቸው ታክሲዎች ውስጥ እስከመሳፈር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች አሉ።” በማለት ያላትን ስጋት ለአዲስ ዘይቤ አስረድታለች።የከተማዋን ነዋሪዎች ከጠዋት እስከ ማታ ከአንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ የሚያመላልሱት ሹፌሮች ከዚህ የተለየ አመለካከት የላቸውም። ከአጎና ደምበል በሁለት ብር ታሪፍ የታክሲ አገልግሎትን በመስጠት የሚተዳደረው ሀብታሙ ሚደቅሳ እንደገለፀው የመጫን አቅሙ በግማሽ በነበረበት ወቅት የተሻለ ጥንቃቄ እንደነበረ ይገልፃል። ሀብታሙ የታክሲ አገልግሎትን በሚሰጥበት ወቅት የሚታዘበውን ሁኔታ በሚያስረዳበት ወቅት “ሰዉ መጠንቀቁን ትቶታል። ጓደኛዬ አብራኝ ናትና ትርፍ ካልጫንከኝ፣ የአፍና ያፍንጫ ማስክን አላደርግም ወይም አልያዝኩም እንዲሁም መነካካት ስራውን ስትሰራ የምትታዘባቸው የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንደሰው ትሰጋለህ። ግን ስራ ነውና ትሰራዋለህ።” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። አክሎም የሚኒባስ ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ዋነኛ የትራንስፖርት አማራጭ እንደመሆኑ መጠን መንግስት ተገቢውን ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ሀብታሙ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

አስተያየት