ሰኔ 30 ፣ 2013

የከተማዋ ተንቀሳቃሽ የሳንቲም ሙዚየም

City: Addis Ababaአካባቢኹነቶች

ጥቂት አስርት ዓመታትን ካስቆጠሩት ወጣት ሳንቲሞች ጀምሮ የ100 ዓመት እድሜ ያላቸው የሳንቲም ስብስቦችን የተሸከመችው የሹፌር ደረጄ ብርሃነ ሚኒባስ ታሪክን እና ትዝታን ተሸክማ ከቄራ ስቴድየም የሚጓዙ መንገደኞችን አድርሳ ትመልሳለች፡፡

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed for the past five years.

የከተማዋ ተንቀሳቃሽ የሳንቲም ሙዚየም

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከቦታ ቦታ ከሚያመላልሱት ታክሲዎች ውስጥ በአንዷ ለየት ያለ ነገር ተመለከትኩ፡፡ በሚኒባስ ታክሲዋ ‘ዳሽቦርድ’ ላይ የተለጠፉት ልዩ ልዩ የሕጻናት መጫወቻዎችና የበርካታ ሐገራት ሳንቲሞች ቀልብን ይስባሉ፡፡ እግር ጥሎት የፊተኛው ወንበር “ጋቢና” የተቀመጠ ተሳፋሪ እግረ-መንገዱን የሳንቲም ስብስቦቹን ይጎበኛል፡፡ ጥቂት አስርት ዓመታትን ካስቆጠሩት ወጣት ሳንቲሞች ጀምሮ የ100 ዓመት እድሜ ያላቸው የሳንቲም ስብስቦችን የተሸከመችው “ዳሽቦርድ” ታሪክን እና ትዝታን ተሸክማ ከቄራ ስቴድየም የሚጓዙ መንገደኞችን አድርሳ ትመልሳለች፡፡

የሚኒባስ ታክሲዋ ሹፌር ደረጄ ብርሃነ ይባላል፡፡ ረዳት ሆኖ ሥራ የጀመረባትን የእናቱን ታክሲ ማሽከርከር ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመኪና ዙርያ ያልሰራሁት ሥራ የለም የሚለው ደረጄ የገራጅ ሥራ፣ የከባድ መኪና ረዳት፣ የቡና እርሻ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች ሰርቪስ መኪና ማሽከርከር፣ የታክሲ ረዳትነት ያለፈባቸው የሥራ መስኮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሹፌር ሆኖ የሚያገለግለው ደረጄ ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምሯል፡፡

ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ሳንቲሞችን መሰብሰብ ደስታ የሚሰጠው የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ‘ሆቢው’ ነው፡፡ በአጋጣሚ ተሳፋሪዎች ሂሳብ ሲከፍሉ ከሌሎች ሳንቲሞች ጋር ተቀላቅላ የገባች ጊዜ ያለፈባት ሳንቲም ሲያገኝ ደስታው ነው፡፡ እንደሌሎች በተሳፋሪ ተጭበረበርኩ ብሎ አይበሳጭም፡፡ ተቀብሎ ያስቀምጣታል፡፡ በትንሹ አንድ ሁለት እያለ የሰበሰባቸው ሳንቲሞች ዛሬ በቁጥር በርክተዋል፡፡ ከ10 ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ ሲጠራቀሙ ከ500 በላይ ደርሰዋል

“ሰዎች እንግዛህ ብለውኝ ያውቃሉ፡፡ እኔ ግን መሸጥ አልፈልግም” የሚለው ደረጄ ሳንቲሞቹን መሰብሰብ የጀመረበትን ሁኔታ ሲያስታውስ “አጋጣሚ ነው” ይላል፡፡ “ሳንቲም መሰብሰቡን ማንንም ዓይቼ አልጀመርኩትም፡፡ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አገኝበታለሁ ብዬም አይደለም፡፡ በአጋጣሚ ነው”  ይላል።

አብዛኛዎቹ የሳንቲም ስብስቦቹ ከሰዎች የተበረከቱለት ናቸው፡፡ ከጓደኞቹ እና ቤተሰቦቹ ጀምሮ ታክሲውን ተሳፍረው ሆቢውን የተረዱት ሰዎች በልዩ ልዩ አጋጣሚ እጃቸው የገባውን የቆየ ወይም የሌሎች የዓለም ሐገራት ሳንቲሞች ያበረክቱለታል፡

ሳንቲሞችን ለመሰብሰብ የመጀመርያዋ መነሻው በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አገልግሎት ትሰጥ የነበረች 10 ሳንቲም እንደሆነች ይናገራል፡፡ “ከሁሉም በፊት ያገኘኋት እሷን ነው፡፡ በርካታ ዓመታት አገልግላለች፡፡ እኔ እጅ ውስጥ ከገባች ራሱ 10 ዓመት አልፏል፡፡ ነገርግን አሁንም አንጸባራቂና ውብ ናት፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የአጼ ምኒልክን 1 ብር ሰው ሰጠኝ፡፡ የሰጡኝን እናት ራሱ አስታውሳቸዋለሁ ወፈር አጠር ያሉ በእድሜ ገፋ ያሉ እናት ናቸው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ነው እንግዲህ አሁን ያሉበት ቁጥር ላይ የደረሱት፡፡ ካሉት ሳንቲሞች ውስጥ አጥብቄ የምወዳቸው እነሱን ነው”።

በአስር ዓመታት ውስጥ ከተሰባሰቡት ሳንቲሞች ውስጥ 100 ዓመታት ያስቆጠሩ የታንዛኒያ እና የኢትዮጵያ ሳንቲሞች ይገኛሉ፡፡ በኦፓል፣ በብር፣ በነሐስ ማዕድናት የተሰሩም ይገኙበታል፡፡

“ሁሉም ሳንቲሞች አገልግሎት የማይሰጡ አይደሉም፡፡ በሥራ ላይ ያሉ፣ ሊመነዘሩ የሚችሉም አሉበት፡፡ ነገር ግን እኔ ሳንቲሞቹን መንዝሮ የመጠቀም ፍላጎት የለኝም፡፡ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ካላየኋቸው ራሱ ደስ አይለኝም” የሚለው ደረጄ በስብስበቹ ምክንያት ሰዎች የሚሰነዝሩትን ሐሳብ አስመልክቶ ያቀረብንለትን ጥያቄ እንዲህ መልሷል፡

“ሰዎች የተለያየ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡ እስካሁን ያጋጠሙኝ አምስት ዐይነት ሰዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ለነገሩ ጥሩ አመለካከት የሌላቸው ናቸው፡፡ ከሳንቲሞቹ በተጨማሪ ‘ዳሽቦርዱ’ ላይ የተለጠፉት የሕጻናት መጫወቻዎች እና መገልገያዎች ምቾት የማይሰጧቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ‘ኮተታም’ ወይም ‘ምን አለሽ ተራ’ ብለው ሰድበውኝ ከታክሲው ይወርዳሉ፡፡ ንጽሕና እንደጎደለኝ ወይም በአዕምሮ ቀውስ ምክንያት የማይፈለጉ ኮተቶችን እንደምሰበስብ ያስባሉ፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ጅል ወይም የዋህ እንደሆንኩ ይሰማቸዋል፡፡ ኮተት ከምሰበስብ የሚመነዘረውን ባንክ ወስጄ እንድመነዝር፣ በማእድን የተሰሩትን ለማእድን ሻጮች እንድሸጥ፣ የማያገለግሉትን እንድጥል ይመክሩኛል፡፡ ሦስተኛዎቹ አርት መሆኑ የገባቸው ናቸው፡፡ በተለይ ለስዕል እና ኪነ-ጥበብ ቀረብ ያሉ ሰዎች ‹ሆቢዬ›ን ያደንቃሉ፡፡ እንግዛህ የሚሉኝ ደግሞ አራተኛዎቹ ናቸው፡፡ ከባእድ አምልኮ ጋር የሚያገናኙትም ሰዎች አሉ”።

የሐገሩን የቆየ ሳንቲም አግኝቶ የተደሰተውን ጀርመናዊ እና ከውጭ ሐገር የመጣች ተሳፋሪ ከ5 ዓመታት በፊት ያነሳችውን የራሱን ሳንቲም ስብስብ ያሳየችውን ኢትዮጵያዊት ከማይረሳቸው ገጠመኞቹ መካከል ናቸው፡፡

አስተያየት