ሰኔ 30 ፣ 2013

“የድሬደዋ ቆንጆ” አሁን የት ነች?

City: Dire Dawaአካባቢ

“የድሬዳዋ ቆንጆ” በሚል ቅጽል ስሟ የምትታወቀው፣ አብዛኛው ተማሪ በስእል ደብተሩ ላይ የሳላት፣ ምስሏ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ሠራተኞች መታወቂያ ላይ የነበረው ሴት አሁን የት ናት?

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

“የድሬደዋ ቆንጆ” አሁን የት ነች?

1939 ዓ.ም. የድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የተቋቋመበት ዘመን ነበር፡፡ ከድሬዳዋ አልፎ የመላው ኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ፍላጎት እንደሚያሟላ ተስፋ የተጣለበትን ፋብሪካ መመረቅ ተከትሎ አፄ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ፋብሪካውን ለመጎብኘት ድሬዳዋ ተገኙ፡፡ ለንጉሡ የክብር አቀባበል ድምቀት የአበባ ጉንጉን እንዲሰጡ ሦስት የፋብሪካው ሠራተኞች ተመረጡ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መሰሉ ካሳ ተስፋዬ አንዷ ነበረች፡፡

“የድሬዳዋ ቆንጆ” በሚል ቅጽል ስሟ የምትታወቀው፣ አብዛኛው ተማሪ በስእል ደብተሩ ላይ የሳላት፣ ምስሏ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ሠራተኞች መታወቂያ ላይ የነበረው፣ ድርጅቱ  ጨርቅ ማምረት አቁሞ ክር ብቻ ማምረት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ የድርጅቱ ምልክት ሆና ያገለገለችው ሴት አሁን የት ናት? በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ተሸጦ አዲስ ኢዘሚር በሚባል ስም በግለሰብ እየተዳደረ ይገኛል።

ሰላሳ ሁለት አመታትን በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው በአሁኑ ሰአት ጡረታ ከወጡ 15 አመት የሞላቸው ወ/ሮ ባየች ጥላሁን የድሬደዋ ቆንጆ ተብላ የምትጠራዋን እንስት ፎቶ በሚገባ ያስታውሱታል። እሳቸው በተቀጠሩበት ወቅት በስራ ላይ እንዳልነበረች ገልፀው ነገር ግን በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ያለችበትን አካባቢ በዝና እንደሚያውቁት ተናግረው በአሁኑ ሰአት ግን የት እንደምትገኝ እንደማታውቅ ገልፃለች። 

“የሷን ፎቶ መታወቂያዬ ላይ የሚያየው ልጄ በሰአቱ ስዕል እንጂ የመስሪያ ቤታችን ሰራተኛ ስለማትመስለው በአካል እንዳሳየው ይጎተጉተኝ ነበር” ሲሉ ወ/ሮ ባየች ጥላሁን ወደኋላ ተመልሰው ስለመሰሉ ውበት በአድናቆት አጫውተውናል።

መሰሉ በልጅነቷ በተቀላቀለችው በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ለ16 ዓመታት አገልግላለች፡፡ የፋብሪካው ብቻ ሳይሆን ተወልዳ ያደገችበት ከተማ ‘ብራንድ’ እስከመሆን ለደረሰው የምስል ማስታወቂያዋ ግን አልተከፈላትም፡፡ የብራንድ አምባሳደር ወይም የማስታወቂያ ሞዴል በመሆን የሚከፈሉ ክፍያዎችን አታውቃቸውም፡፡

ምስሏ በፋብሪካው መግቢያ በር ላይ በግዙፍ ተሰቅሎ፣ በእያንዳንዱ ሰራተኛ መታወቂያ ላይ ታትማ፣ በእያንዳንዱ ምርት ላይ ፎቶግራፏ ተለጥፎ፣… መሰሉ ያገኘችው አንዳችም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለም፡፡

ፎቶውን በዝግጅቱ ላይ የተነሳችው የነበረ ሲሆን ድርጅቱ ለማስታወቂያ እንዲሁም እንደ ብራንድ አምባሳደር ለመጠቀም እንዳሰበ ምንም የምታውቀው ነገር እንደሌለ ትጠቅሳለች። በጉዳዩ ላይ በሰአቱ እውቀት ስላልነበራት ገንዘብ እንዲከፈላትም አልጠየቀችም።

በድሬዳዋ ከተማ የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ለማቋቋም ምክንያት የሆነው የከተማዋ አቀማመጥ ነው፡፡ ድሬዳዋ ከጅቡቲ ወደብ እና ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሐዲድ ባለቤት መሆኗ በቀዳሚነት ያስመረጣት ጉዳይ ነው፡፡ ለፋብሪካው አስፈላጊ የሆነ ግብአትም ሆነ መለዋወጫ ዕቃዎችን ወጪ በቆጠበ መንገድ ለማጓጓዝ፣ ለምርት ሂደቱ አስፈላጊ የሆነ የውሃ ክምችት ያላት መሆኑ፣ ለጨርቃጨርቅ ምርት አስፈላጊ ከሆኑ ግብአቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ቋሚ እና የማይለዋወጥ የአየር ንብረት (የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያ በሌለበት ከ20-30oC ሙቀት እና ከ40-50% የአየር እርጥበት)፣… ያሟላች ከተማ መሆኗ ለፋብሪካው መቀመጫነት አስመርጧታል፡፡   

የፋብሪካውን 60ኛ ዓመት አስመልክቶ የታተመው መጽሔት እንዳሰፈረው የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ድርጅቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ምቹ አጋጣሚዎች ቢሆኑም እንደ መሰሉ ያሉ አምባሳደሮችም የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡

በወቅቱ በጨርቃ ጨርቅ የምርት 37% ያህሉን የሀገሪቱን ገበያ የሚሸፍነው የድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

የድሬደዋ ቆንጆ መሰሉ ካሳ ተወልዳ ያደገችው በድሬደዋ ከተማ ነው፡፡ ዐይን የሚገባ መልክ እና ጆሮ የሚስብ ድምጽ ነበራት፡፡ በወጣትነቷ ዘመን “ኮተን” የሚል ስያሜ በነበረው የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ የመዝናኛ ክበብ አባል በመሆን በድምጻዊነት አገልግላለች፡፡ በበርካታ የከተማዋ ተማሪዎች ከሚታወቀው መምህር ስለሺ እና ድምጻዊ ታምራት ደስታ አብራቸው ከዘፈነች ድምጻዊያን መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከኮተኒ ክበብ በተጨማሪ በዴሳን፣ መቻራን እና አሰበን በመሳሰሉ ትንንሽ ከተሞች በመዘዋወር የሙዚቃ ሥራዋን አቅርባለች፡፡

መሰሉ ካሳ በፋብሪካ ስራ ላይ በነበረችበት ጊዜ በጥጥ ማምረቻ ክፍል ውስጥ የ”ካቻሬ”ሰራተኛ ነበረች፡፡ (ካቻሬ ማለት ማደወር ማለት ነው) በሰዓቱ ለነበሯት ለሁሉም አገልግሎቶች ማለትም ለብራንድ አምባሳደርነቷ፣ ለሙዚቃ ሥራዋ፣ በፋብሪካው ውስጥ ለምታገለግላቸው አገልግሎቶች ሁሉ የሚታሰብላት የቀን ደሞዝ 1 ብር ከ 50 ብቻ ነበር፡፡

ከድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ከተሰናበተች በኋላም ከባድ የኑሮ ውጣ ውረድ አሳልፋለች፡፡ የአብራኳ ክፋይ የሆኑት ሁለት ልጆቿን በሞት አጥታለች፡፡ የሚጦራት ልጅ ወይም የሚረዳት ዘመድ የላትም፡፡በአሁን ሰዓት ቀበሌ 04 በሚገኘው ገንደቆሬ በተባለው የድሬዳዋ ከተማ ገበያ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ ተሰማርታ ህይወቷን ትገፋለች፡፡

አስተያየት