የሲዳማ ብሄር ልዩ እና ሳቢ የባህል ዘውጎች መካከል እሳቤዎቹ፣ እምነቱ፣ የዘመን ቀመር፣ የቀናት ፍረጃው፣ ሀገር በቀል ዕውቀቱ፣ ስርአተ ክዋኔውና፣ ጭፈራው ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ የቱባ ባህል ዘውጎች ውስጥ የሚመደበው የ"ፋሮ" ጭፈራ ባህላዊ የክንውን አውዶችን እና ዓመታዊ ክብረ-በዓላትን ተንተርሰው ከሚጨፈሩ የሲዳማ ባህላዊ ጭፈራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ያላገቡ ወጣቶች ስሜታቸውን፣ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት የሚያጋሩበት እንዲሁም የሚተጫጩበት መድረክም ጭምር ነው።
የብሄሩ ተወላጅ የሆኑት አዛውንት አቶ ዓለማየሁ ኤልያስ “ፋሮ” በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ታዋቂ እና ተወዳጅ የልጃገረድ ሴቶች እና የወጣት ወንዶች ጨዋታ መሆኑን፣ አጨዋወቱ የተወሰደው ከእርግቦች (lemboolla)ዎች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የተለያየ ቦታ የነበሩ እርግቦች ሲገናኙ አንገት ለአንገት በመቀራረብ ከፍ ዝቅ እያሉ እንደሚያሳዩት እንደ ሰላምታ ዓይነት እንቅስቃሴ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የ“ፋሮ” ጨፋሪ ወጣት ወንዶች እና ሴቶችም የእርግቦቹን እንቅስቃሴ የሚመስል የአጨፋፈር ስልት አላቸው።
ከዚህ በነመሳት ይመስላል የፋሮ ጨዋታ “lembooho, lemboolena…” በሚል ሳቢ ዜማ የሚታጀበው ቀጥተኛ ትርጉሙም (እርግቤ እርግቤዋ) እንደማለት ነው፡፡ የዘፈኑ ግጥም እርግብን በማንሳት ዜማውን የሚጀምረው በማኅበረሰቡ ዘንድ እርግብ የየዋህነት ምሳሌ ተደርጋ ስለምትወሰድ ነው። በእርግብ የተነሳው ዜማና ግጥም በጎነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን የሚያስተጋቡ ሐሳቦች ይተላለፉበታል፡፡
የዚህ ጨዋታ ተሳታፊ ወጣቶች በሀገር በቀል ዕውቀት በተሸመኑ፣ ቁሳዊ ባህልን በሚያንጸባርቁ የፈትል ጥበቦችና ጌጣጌጦች ይዋባሉ፣ የማኅበረሰቡ መለያ ከሆኑት ጌጣጌጦች በተጨማሪ ባህሉን በጠበቀ የጸጉር አሰራር እና አቆራረጥ ደምቀው ጦር ይይዛሉ፡፡
ወጣት ወንዶች ፀጉራቸውን አጎፍረው የተዋቡ ብትሮቻቸውን ይዘው፣ "ሀፋሮ እና ዳባርታ" (የወጣት ወንዶች ባህላዊ አልባሳት) ለብሰው ትከሻ ለትከሻ ተገጣጥመው፣ በረድፍ ተደርድረው ልጃገረዶችን እያሞካሹ ግጥም እየደረደሩ ይጫወታሉ። ልጃገረዶችም "ቆሎ" የተባለውን (የሴቶች ባህላዊ ልብስ) ለብሰው ጸጉራቸውን ወደኋላ በጨሌ አውርደው "goodayya" (ባህላዊ የጸጉር አሰራር ነው) ተሰርተው፣ ቅቤ ተቀብተው በአጭር ርቀት በመሆን የወንዶችን ጨዋታ ለአጭር ጊዜ በጥሞና ከተከታተሉ በኋላ ተራ በተራ ቀልባቸው ወደፈቀደው ወጣት ያመራሉ፡፡ ፊት ለፊቱ በመቆምም ግጥም እየደረደሩ ይጫወታሉ። በወንዶች ፊት ልጃገረዶች እንደተደረደሩ ወንዶቹ የሴቶቹን ትከሻ ይዘው እና አገጭ ለአገጭ በመነካካት ወደፊት እና ወደኋላ እንዲሁም ወደጎን እያወዛወዙ ይጨፍራሉ። ለየት ያለው የጭፈራ ስልት ዐይንን ይስባል፣ ቀልብን ይገዛል፡፡
ወጣቶች የ“ፋሮ” ጭፈራን የሚጨፍሩት በሲዳማ የዘመን መለወጫ "ፍቼ" በዓል ላይ፣ የተገረዙ ወንዶችን ለመጠየቅና ስጦታ ለማቅረብ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት ላይ እንዲሁም በሰርግ እና በተለያዩ የባህል ክንውኖች ላይ ነው።
በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምሽን ቢሮ የፎክሎር ጥናት እና ልማት ባለሙያ የሆነው አቶ ጥበቡ ላሊሞ ፋሮ ወጣት ወንዶች እና ልጃገረዶች ባህላዊ አውዶችን ተንተርሰው በጋራ በመጨፈር የወደፊት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አንዲሁም የሚተጫጩበት ባህላዊ የጨዋታ ስልት ነው ሲል ገልጿል።