ሐምሌ 23 ፣ 2013

“ሀላሌ” የሲዳማ ህዝብ በእውነት የመኖር መርህ

City: Hawassaባሕል

"ሀላሌ" የሲዳማ ህዝብ እንደ መርህ የሚከተለው ባህላዊ እሴቱ ነው፡፡“ሀላሌ” ሀገር በቀል እውቀትን በመመርኮዝ በሸንጎ አውዶች ላይ ጭምር እውነትን ይዞ በመቅረብ ሃቅን ለባለሀቁ የመፍረድ ሂደት ነው።

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

“ሀላሌ” የሲዳማ ህዝብ በእውነት የመኖር መርህ

"ሀላሌ" የሲዳማ ህዝብ እንደ መርህ የሚከተለው ባህላዊ እሴቱ ነው፡፡“ሀላሌ” ሀገር በቀል እውቀትን በመመርኮዝ በሸንጎ አውዶች ላይ ጭምር እውነትን ይዞ በመቅረብ ሃቅን ለባለሀቁ የመፍረድ ሂደት ነው። 

በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የፎክሎር ጥናት እና ልማት ባለሙያ አቶ ጥበቡ ላሊሞ “የሀላሌ ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉም እውነት ወይም የማይካድ ሃቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሲዳማ ብሄር ዘንድ "ሀላሌ" ፈጣሪ ነው ተብሎ ይታመናል። "hola halaale" የሚባል የሚታመን መርህ አላቸው። ይህም (እግዚኦ ለእውነት) እንደማለት ነው።” በማለት ያብራራሉ፡፡ ነገራቸውን በምሳሌ ሲደግፉም፡-

“ለምሳሌ አንድ የሰውን ንብረት የሰረቀ ግለሰብ መስረቁን ሽማግሌዎች ተሰብስበው በሀላሌ መርህ መሰረት እንዲያምን ይጠየቃል። አላምን ካለ "hola halaale" (እግዚኦ ለእውነት) ብለው እውነቱን ለፈጣሪ ትተው ይለያያሉ። ይህም ሽማግሌዎቹ እውነታውን ለፈጣሪ በመተዋቸው የተበላው የሰው ሀቅ መቅሰፍትን ይዞ ይመጣል ተብሎ ይታመናል። ለዚህም ነው የሲዳማ ማኅበረሰብ መቅሰፍት ከመምጣቱ በፊት የሀላሌ መርህ ባህላዊ እሴትን የእለተ እለት የህወት መስተጋብሩ ያደረገው” ይላል አቶ ጥበቡ።

የሲዳማ ሰዎች የአንድን ነገር እውነተኛነት በመሀላ ለማረጋገጥ ሀላሌ ይላሉ፡፡ ለሲዳማ ከሀላሌ በላይ መሀላ የለም። ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ነባር እምነት ዘንድም ሀላሌ ከ“ማጋኖ” (ፈጣሪ) ጋር የሚያገናኝ ድልድይ እንደሆነ ይታመናል። በብሄረሰቡ ዘንድ በሀላሌ የሚኖር ሰው በማኅበራዊ ህይወቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እና ተደማጭነት ያለው ነው። በማኅበራዊ ህይወት ውስጥ እውነትን መለወጥ እንደማይገባ፣ ከእውነት ዝንፍ ማለት እንደማያስፈልግ እንዲሁም እውነትን መሸሽ እና ማጣመም እንደሚያጠፋ በጽኑ ይታመናል። 

በአንፃሩ የሀላሌን መርህ የሚጥስ ማንኛውም የብሄረሰቡ ተወላጅ በራሱ ላይም ሆነ ከእርሱ በሚፈጠረው ተከታይ ትውልድ ላይ መልካም ነገር አይገጥመውም የሚል ፅኑ እምነት በማኅበረሰቡ ዘንድ አለ። ስለሆነም የአንድን ሰው ሀቅ ማጣመምም ሆነ ማዳፈን በሕብረተሰቡ ዘንድ የተወገዘ እና በእጅጉ የተጠላ ነው። በሀላሌ መርህ ታላቅነትን፣ መሀላን፣ እውነተኛነትን የመሳሰሉ ጉዳዮች ከፍ ያለ ስፍራ ይሰጣቸዋል። 

አንድ ሰው የሌላውን ሰው ሀላሌ ሳይፈፅም የሞተ እንደሆነ የእርሱ ወገኖች (ቤተሰብ፣ ዘመድ) ለባለሀቁ የሚገባውን በማድረግ ሀላሌ ያስጨርሳሉ። እንዲሁም አንድ ሰው የሚፈልገው ሀቅ ሳይፈፀምለት የሞተ እንደሆነ ልጆች ካሉት በልጆቹ ላይ ልጆች የሌሉት ከሆነ በመቃብሩ ላይ ሀቁ እንዲመለስ ይደረጋል። ይህ የሚሆነው የሀላሌን መርህ መጣስ ለዘር ማንዘር የሚተርፍ መቅሰፍት ከፈጣሪ (ማጋኖ) ዘንድ ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን ነው።

በሌላ መልኩ የሀላሌ መርህ የሰዎችን፣ የእንስሳትንና በአጠቃላይ የተፈጥሮን መብት ከማክበር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለምሳሌ የሴት ሀቅ "meyaate halaale" በመባል በማኅበረሰቡ ከሚታወቁት መካከል ከአንድ በላይ ሚስቶች ያሏቸው አባወራዎቸ የመጀመሪያ ሚስታቸውን በአክብሮት መያዝ፣ መንከባከብ እና የሚገባትን ሁሉ አለማጓደልና እንዲሁም እንደ ፍቼ (ዘመን መለወጫ) ባሉ ክብረ በዓላት ወቅት የመጀመሪያውን ገበታ በቤቷ በመቁረስ ሀቋን መጠበቅ ይኖርበታል።

“ሀላሌ”ን በስነ-ቃል 

በእድሜ የገፉ የማኅበረሰቡ ተወላጅ የሆኑ አዛውንቶች የሀላሌን አስፈላጊነትና የሀላሌን መርህ አለማክበር የሚያስከትለውን መዘዝ ለማመልከትም በስነ-ቃሉ ለልጅም ለአዋቂም ምክር ይለግሳሉ። የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት አንድ ማኅበረሰብ በጉዳዮች ላይ ያለውን እሳቤ እና ፍልስፍና የሚያስተላልፈው በስነ-ቃል ነው፡፡ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ አሁን ላይ በደረሰው ስነ-ቃል አማካኝነት የሚተላለፈው መልእክት በትውልዶች ቅብብሎሽ በነበረው ተቀባይነት አማካኝነት የዳበረ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ የሲዳማ ብሔር የአኗኗር ዘይቤ ስለሆነው ስለሀላሌ ከተነገሩ ስነ-ቃሎች መካከል ተከታዮቹ ይገኙበታል፡፡

ü  "mitu ayiddi halaale gudanno mito ayidde halaalu gudanno"

      (ገሚሱ ሀላሌን ያስጨርሳል፤ ገሚሱን ሀላሌ ይጨርሰዋል)

ü  "hoonchu haqqinna halaalu keeshshirono difugudanno"

     (የጥድ እንጨት እና ሀላሌ ቢቆዩም አይበሰብሱም)

አስተያየት