ሐምሌ 23 ፣ 2013

ከዉጭ የሚገቡ የመዋቢያ ዕቃዎች ቅሸባ ይፈፀምባቸዋል?

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችጤና እና ውበት

የመዋቢያ እቃዎች ከፋብሪካ ሲወጡ ካላቸዉ መጠን ላይ እየተቀነሰባቸዉ እና የተለያየ ባዕድ ነገር እየተጨመረባቸዉ ምርቶቹን ማየት እየተለመደ መምጣቱን በመዋቢያ እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡

ከዉጭ የሚገቡ የመዋቢያ ዕቃዎች ቅሸባ ይፈፀምባቸዋል?

ከአከፋፋዮች ላይ ገዝተን ለደንበኞቻችን በችርቻሮ የምናቀርባቸው የመዋቢያ እቃዎች ከደንበኞቻችን ጋር እያጋጩን ነው፣ ሲሉ ከፋብሪካ ሲወጡ ካላቸዉ መጠን ላይ እየተቀነሰባቸዉ እና የተለያየ ባዕድ ነገር እየተጨመረባቸዉ ምርቶቹን ማየት እየተለመደ መምጣቱን በመዋቢያ እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡

"በሚታይ መልኩ የጎደሉ ቅባቶች፤ መጠናቸው የተቀነሱ ዊጎች፤ በተለያዩ ማቅጠኛ አልኮሎች የቀጠኑ ጥፍር ቀለሞችን ሳይቀር አከፉፉዮች ይሸጡልናል።” የሚለዉ መስቀል ፍላወር አካባቢ የሚገኝው የፕሪንሰስ የውበት ሳሎን ባለቤት ናትናኤል ዘውዱ ነው። "መጀመርያ ሰሞን ለዉጡ የመጣዉ ከፋብሪካዎቹ አንደሆነ አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ስራ አጋጣሚዎች ወደ ውጭ ሀገር የተጓዙ ደንበኞች የሚያመጡልን ደሞ ይለያል፤ ከዛም አልፎ ከቦታ ቦታ የሚሸጡት እቃዎችም የተለያየ መጠን እንዳላቸው መታዘብ ከጀመርን ቆየት አልን።” ሲል ያጋጠመዉን ይናገራል፡፡

ይህን ተከትሎ መጠናቸው አነስ የሚሉ አንዳንድ ምርቶች ያገኘንበትን ሱቅ "ይህን ነገር አላስተዋሉትም ወይ? ካስተዋሉትስ ምን ይላሉ?" ስንል ባለቤቷን ወይዘሮ ህይወት መለሰን ጠየቅን።

"እውነት ለመናገር አስተውለናል። እዚሁ እኔ ሱቅ ራሱ የማመጣቸው እቃዎች ተመሳሳይ ምርት ሆነው በመጠን ደረጃ የአንዱ ከአንዱ ተለይቶብን ያውቃል። የሚያስረክቡኝን አከፋፋዮች ስለሁኔታዉ ስጠይቃቸዉ ምርቶቹ ከውጪም ሲመጡ እንዲህ ነው የምርት ሂደታቸው መዛባት ሊሆን ይችላል እንጂ እኛ የምናውቀው ነገር የለም ሲሉ መልሰውልኛል።" በማለት ህይወት ትናገራለች፡፡

ከተለያዩ ማከፋፈያዎች እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥማት እና ከደንበኛ ስሞታ ሲበዛባት የተጭበረበረ ነገር አለ ብላ ለአካባቢው ፖሊስ ጥቆማዋን አቅርባ መልስ እየጠበቀች መሆኑንም መርካቶ አካባቢ የመዋቢያ እቃዎችን ስትሸጥ ያገኘናት ህይወት አጫዉታናለች፡፡

"የመዋቢያ እቃዎችን እንደሚጠቀም ሰው ስናገር ትክክለኛ እና የተጭበረበሩ ኮስሞቲክሶችን መለየት ከባድ አይደለም። እየተቀነሱ እና በባዕድ ነገር የተቀየጡ መዋቢያዎች ተሽጠውልኝ ልጠቀም ስል ግርታ ፈጥሮብኝ ያናገርኳቸው ሻጮች አሉ።" የምትለዉ ደግሞ የምርቶቹ ተጠቃሚ የሆነችው ሳራ ሞገስ ናት፡፡ "ነገር ግን ልክ ከኔ እኩል እንዳወቁ ወይም ምርቱ ተለውጦ ሊሆን እንደሚችል ነው ሚነግሩኝ። ይሄ ደሞ ማን ጋር ሄደን ምን መግዛት እንዳለብን ግራ እንድንጋባ ነዉ የሚያደርገን።” ስትል ታብራራለች።

“ሰውነታችንን የሚነካ ነገር ምንነቱ በማይታወቅ ባዕድ ነገር መቀየጥም ሆነ ከፍቶ ከላዩ ላይ በመቀነስ አንደገና ማሸግ በተጠቃሚዉ ጤንነት ላይ የሚያመጣዉን ጉዳት ችላ ማለት ይመስላል" የምትለዉ ሳራ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚኖረዉ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ትላለች፡፡

ይህንን ሌሎች ሱቆች ተዘዋውራ ተመሳሳይ ነገር የታዘበችው አዲስ ዘይቤ "ይህ ነገር እንዴት ነው?" ስትል ሁለት የአልባሳትና እና የኮስሞቲክስ እቃዎች አስመጪ እና አከፋፋይ አናግራ በቂ ምላሽ ባለማግኘቷ የአካባቢው ነጋዴዎች ጥቆማ አድርሰንበታል ወዳሉት የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት በዚህ ጉዳይ ያለውን መረጃ ጠይቃለች።

የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀልና ምርመራ ማስተባበርያ ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ አለሙም ስለጉዳዩ ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረው በክትትል ላይ እንደሚገኙም አሳውቀውናል።

"በእርግጥ ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ክሶች በሌሎች ዘርፎችም ይመጣሉ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ለተገልጋዮች ማቅረብ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ያለ ይሉኝታ በመደብር ሼልፎች ላይ ደርድሮ መሸጥ እና የተለያዩ ምርቶችን እየቀነሱ እና ከባዕድ ነገር ጋር እየቀላቀሉ መሸጥ እና መሰል ፀያፍ ተግባራት እኛ ጋር በብዛት ክስ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው። ሆኖም እነዚህ ተገልጋዮችን በማታለል የሚፈጸመው ድርጊቶች የአገራችንን የግብይት ሥርዓት በእጅጉ እየጎዱ በመሆናቸው ፖሊስ ጉዳዩ ላይ በትኩረት በመስራት ጠንካራ እርምጃ እየወሰደም ይገኛል" ሲሉ ያብራራሉ።

አክለውም "ከነዚህ የውበት መጠበቂያ እቃዎች ጋር በተያያዘም እንደዚሁ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ተቋማት እንዳሉ ጥቆማ ከደረሰን ጊዜ ጀምሮ በተጠረጠሩት አቅራቢ ድርጅቶች እና ራሳችን ባደረግነው አሰሳ ጭምር ጥብቅ ክትትል እያደረግን እንገኛለን። ሆኖም እነዚህ ድርጅቶች ከበቂ ማስረጃ ጋር ጥፋተኛ መሆናቸው ሲረጋገጥ የማጋለጥ እና የእርምጃ ስራ ይሰራል።" ብለዋል።

እነዚህ ባልተገባ መንገድ የሚፈጸሙ የግብይት ሥርዓቶች እየተንሰራፉ እና ደንበኛ ተኮር ሳይሆኑ፣ የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚፈጸሙ፣ ለሌሎች ደንታ ቢስነት የሚታይባቸው መሆናቸውን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

ሕገ ወጥ ተግባራት በተበራከቱ ቁጥር በበጎ ህሊና ለመሥራት የሚጥሩትንም እየበረዘ ይሄዳልና ሥነ ምግባር ያለው ለህሊናውም ጭምር የሚሠራ አገልጋይ ለመፍጠር ሕገወጦችን አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ህግ አስከባሪ ጋር እንዲደርስ ጠያቂ መሆን አለበት፡፡

አስተያየት