የካቲት 24 ፣ 2013

"ቄጣላ" የጥዑመ ዜማ ትውን ጥበብ

ባሕል

የሲዳማ ብሔር ራሱን የሚገልጽባቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉት፡፡ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ፣ ደስታ እና ሐዘኑን

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

 "ቄጣላ" የጥዑመ ዜማ ትውን ጥበብ

የሲዳማ ብሔር ራሱን የሚገልጽባቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉት፡፡ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ፣ ደስታ እና ሐዘኑን የሚገልጽባቸው መንገዶች እና የአለባበስ ስርአቱ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ በሰፊው ከሚታወቅባቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ስነ-ቃሉ፣ ስርዓተ አምልኮው፣ እሳቤዎቹ፣ አልባሳቱ፣ አጊያጊያጡ፣ የሀገረ-ሰብ እምነት ስርዓተ-ክዋኔው፣… ማኅረሰቡን ከሌሎች የሚለዩት የአኗኗር ዘዬዎቹ ናቸው፡፡


‹‹ቄጠላ›› በመባል የሚታወቀው የጥዑመ ዜማ ትውን ጥበብ (ጭፈራ)ም የሲዳማን ብሔር ከሚለዩት ባሕላዊ ክዋኔዎች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡


የ‹‹ቄጣላ›› ጭፈራ በዓመት አንድ ጊዜ፤ የሲዳማ ብሄር የፍቼ ጨምበላላ አውዶችን ተንተርሶ ይከወናል፡፡ ክብረ-በዓሉ በስልታዊ የአካል እንቅስቃሴ ታጅቦ በጥዑም ዜማ ምስጋና የሚቀርብበት፣ መልዕክት የሚተላለፍበት የማራኪ ትዕይንት መድረክ ነው።


የ‹‹ቄጣላ›› ጭፈራን ሴቶችና ሕጻናት እንዲጨፍሩ ባህሉ አይፈቅድም፡፡ የጭፈራው ተሳታፊዎች ወጣት ወንዶች፣ ጎልማሶች እና አዛውንቶች ናቸው፡፡


የበዓሉ ተሳታፊዎች፡- ‹‹ጎንፋ›› እና ‹‹ቡሉኮ›› የተሰኙ ከሸማ የተሰሩ የባህል አልባሳት ይለብሳሉ፣ ጋሻ እና ጦር ይይዛሉ፣ በስልታዊ እንቅስቃሴአቸውና በዝማሬአቸው የታዳሚን ቀልብ የሚይዝ ትርኢት በጉማይሌ (በአደባባይ)፣ በገበያ ስፍራዎች በመገኘት በዓመት አንድ ጊዜ ያሳያሉ፡፡


የብሔረሰቡ ተወላጆች እንደሚሉት ‹‹ቄጣላ›› ጭፈራ፣ ዝማሬ፣ ውዝዋዜው ብቻ ሳይሆን መልእክቶችንም ማስተላለፊያ ነው፡፡ ዜማ በለበሱት ስንኞች መልእክቶች ይተላለፋሉ፡፡ በአጠቃላይ ‹‹ቄጣላ›› በስልታዊ እንቅስቃሴ እና የግጥም ቅብብሎሽ የሚከወን መልዕክት አዘል ጭፈራ ነው። በወኔ የታጀበ ረጋ ያለ የአካል እንቅስቃሴ ስልት አለው፡፡ አባት አዛውንቶች ጋሻና ጦር ይዘው፣ ግራ እግራቸውን በማስቀደም ቀኙን እያስከተሉ፣ ወደፊት ሄድ መለስ እያሉ፣… የሚከውኑት የጥዑም ዜማ ቅብብሎሽ ሲሆን፤ በፈረስ ግልቢያ ይደምቃል፡፡ የጭፈራ ስርአቱ የሚጠናቀቀው በአባቶች ምርቃት ነው፡፡


የብሄሩ ተወላጅ እና በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምሽን ቢሮ የፎክሎር ጥናት እና ልማት ባለሙያ የሆነው አቶ ጥበቡ ላሊሞ


"ቄጣላ አባቶች ሰብሰብ ብለው በፍቼ ጨምበላላ አውዶች ላይ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉበት፣ ጥሩ የሠራውን የሚያሞግሱበት፣ ጥሩ ያልሰራውን ኮንነው ከእኩይ ተግባሩ እንዲመለስ የሚያደርጉበት፤ በዜማዊ ስልት እንቅስቃሴ ታጅቦ የሚቀርብ አውዳዊ የአደባባይ ክንውን ነው" ሲል ገልጾታል።


የ‹‹ቄጣላ›› ጭፈራ ከ‹‹ፍቼ›› እና ‹‹ጨምበላላ›› የባህል ትውፊት አውዶች ባሻገር፤ እንደ ሀገር መሪ ያሉ የተከበሩ ሰዎች ሲመጡ፤ በእንግዳው የክብር አቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ ማድመቂያ ሆኖ እንደሚቀርብ የባህል ጥናት ባለሙያው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ አብራርቷል፡፡

አስተያየት