የካቲት 24 ፣ 2013

“ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ዕጩ ሆኜ ተመዝግቤያለሁ፤ አቶ ልደቱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ይወዳደራል” - ይልቃል ጌትነት (ኢንጅነር)

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በቅርቡ ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)

“ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ዕጩ ሆኜ ተመዝግቤያለሁ፤ አቶ ልደቱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ይወዳደራል” - ይልቃል ጌትነት (ኢንጅነር)

በቅርቡ ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ከፍተኛ አመራሮች አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) እና አቶ ልደቱ አያሌው ይገኙበታል፡፡

“በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን አመራሮች በሙሉ አባልነት ስቀበል ያላቸውን ልምድ፣ እውቀትና ተሳትፎ ከፓርቲው በላይ ለሀገር ጠቃሚ መሆኑን በማመን ነው" ያለው ሕብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ “አቋሙን እንደሚያስቀጥሉ” መናገሩ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ በዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ ይወዳደሩ እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) “አዎ እወዳደራለሁ” ካሉ በኋላ “በዕጩነት እንደተመዘገቡ” ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
“ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን እኔና አቶ ልደቱ መቀላቀላችን የሚታወቅ ነው” ያሉት አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) “እኔ አዲስ አበባ፤ አራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 2/14፤ አራት ኪሎ አካባቢ በዕጩነት ተመዝግቤያለሁ” ሲሉ ነግረውናል።

“እኔ የምወዳደረው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው” ያሉን አቶ ይልቃል “አቶ ልደቱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት” ይወዳደራል ብለዋል። አቶ ልደቱ የሚወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ የት እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት መወዳደራቸው ግን እርግጥ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ከፍተኛ አመራሮች ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉት የነበሩባቸው ፓርቲዎች ሕጋዊ የፖለቲካ ሰውነት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሰረዙን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል።

የመጀመሪያ ዙር የዕጩ ምዝገባ በሚከናውንባቸው ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ለዕጩዎች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለ4 ቀናት ያህል እስከ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን ተከትሎ የዕጩዎች ምዝገባ በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።

አስተያየት