የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እጥረት እንዳማረራቸው የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በመንግሥት የሚመደቡት የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችም ሆነ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር ከተገልጋዩ ሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ለሰዓታት ትራንስፖርት በመጠበቅ ለእንግልት መዳረጋቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከደራርቱ ጎዳና ተነስተው መዳረሻቸው ቦሎ፣ ቦሌ፣ ቦኩ እንዲሁም ዳቤ ክፍለ ከተማ የሆነው ነዋሪዎች ‹‹በተለይ በሥራ መውጫ እና መግቢያ ሰዓታት ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰብን ነው፡፡ ለአላስፈላጊ ወጪም ተዳርገናል›› ብለዋል፡፡
የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር በተለምዶ ፖስታቤት ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ረዣዥም የትራንስፖርት ሰልፎች እና ቀድሞ ለመሳፈር የሚደረግ ግፊያ ተመልክታለች፡፡
ከተሰላፊዎቹ መካከል ሐሳባቸውን የሰጡት ወ/ሮ አጸዱ ጎሽሜ በአካባቢው ትራንስፖርት ቀድሞ በመያዝ ሽሚያ ምክንያት ይፈጠር የነበረው ግፊያ በፊት ከነበረው መቀነሱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ተራ አስከባሪዎች ትራንፖርት ጠባቂው በአግባቡ እንዲሰለፍ አድርገውታል፡፡ የጠፋው መጓጓዣው ነው፡፡ ሕዝቡ ለእንግልት ተዳርጓል፡፡ እንደ እኔ ላለው አቅመ ደካማ ደግሞ ችግሩ ድርብርብ ነው›› ብለዋል፡፡
የአዳማ ከተማ የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ አቶ አብዲሳ ደደፎ በሰጡት ምላሽ የታክሲ ባለንብረቶች የተመደቡበትን የስምሪት መስመር ጠብቀው አለመስራታቸው ሕብረተሰቡን ለእንግልት እንደዳረገ ያነሳሉ፡፡ መስተዳድሩ የወሰደውን መፍትሔ በተመለከተም
‹‹የከተማው መስተዳድር 12 የከተማ አውቶብሶች አቅርቧል፡፡ እርሱም በቂ ነው ብለን አናስብም፡፡ ወደፊት ሌሎች የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ለመጨመር እቅድ ይዘናል›› የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በአሁን ሰዓት በአዳማ ከተማ 46 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው 13 የከተማ አውቶብሶች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በቀን ውስጥ በአማካኝ ከ10 ጊዜ በላይ ምልልስ በማድረግ ከ20ሺህ እስከ 30ሺህ ተሳፋሪዎችን እንደሚያመላልሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡