በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት አስመልክቶ ቃለ-መጠይቅ ያደረግንላቸው ሰዎች ከሚሰጡት አስተያየት መካከል “ኑሮ ጣሪያ ነካ፤ ዕቃ ተወደደ፤ ጨመረ እንጂ ቀነሰ የለም” የሚሉ ቃላትን በአብዛኛው ይጠቀማሉ።
ለኑሮ መወደድ እንደ ምክንያት ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ከሰሞኑ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉና ይህም በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ማስገደዱ አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
በእርግጥ ለኑሮ መወደድ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ መኖሩ እንደ አንድ ምክንያት ሊቆጠር ቢችልም በሌላ በኩል ግን መጨመር እንጂ መቀነስ የማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የምርት አቅርቦት መቀነስ፣ የሰላም መታጣት እና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደ ምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።
ከሰሞኑ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ለኑሮ መወደድ እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡ ሰዎች በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ላይ ሲደረግ የነበረው ጭማሪ ቀላል አለመሆኑን ያስረዳሉ።
ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ወራት ውስጥ ብቻ በነዳጅ ዋጋ ላይ ማለትም በቤንዚን፣ ኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን፣ ኬሮሲን፣ ነጭ ናፍታ፣ ቤንዚን፣ ቀላል ጥቁር ናፍታ እና ከባድ ጥቁር ናፍታ ላይ በጠቅላላው በእያንዳንዳቸው ላይ በሊትር የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ሲደመር የ32 ብር ከ10 ሳንቲም ንረት ታይቷል።
በጥቅምት ወር የነበረው ዋጋ ከየካቲት ወር ጋር ሲወዳደር በተነፃፃሪ የ3 ብር ከ14 ሳንቲም አነስተኛ ጭማሪ ካሳየው ኬሮሲን ጀምሮ የ10 ብር ከ75 ሳንቲም ከፍተኛ ጭማሪ እስከታየበት የአውሮፕላን ነዳጅ ድረስ በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ የኑሮ ውድነቱን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሊያባብስ የሚችል የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል። ኑሮዋን በአዲስ አበባ ያደረገችው ስመኝ ከፍያለው “ከኮቪድ ቫይረስ ወረርሽኝ ግዜ ጀምሮ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት እንዳለ መታዘቧን” ትገልፃለች። “በተለይ ከሰሞኑ ከምግብ ሸቀጦች ጀምሮ እስከ ቤት ኪራይ ድረስ ጭማሪ ያልተደረገበት ነገር የለም” የምትለው ስመኝ “የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪውም ቢሆን ቀላል የማይባል እንደሆነ” ታነሳለች።
በሌላ በኩል የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን የሚያከፋፍለው ሙአዝ ሱለይማን “ለምግብ ፍጆታ ከሚውሉ አቅርቦቶች በተጨማሪ በሚሸጣቸው የንፅህና መጠበቂያዎች ላይም የዋጋ ጭማሪ መኖሩንና የማጓጓዣ ወጪውም ቢሆን ቀላል እንዳልሆነለት” ይናገራል። “በዋጋ ጭማሪው ምክንያት ዕቃ ስለተወደደ ዕቃዎቹን የሚያመጣበት ገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመውም” እንዲሁ።
ለኑሮ መወደድ እንደ ምክንያት ከሚቀመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የነዳጅ ዋጋ መናርን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው ፀጋዬ ገብረኪዳን (ዶ/ር) እንደሚሉት “በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ለመጨመሩ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል በዓለምአቀፍ ደረጃ ጭማሪ መደረጉ እና የኢትዮጵያ ገንዘብ (ብር) የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ በመምጣቱ” ይገኝበታል።
ለኑሮ መወደድ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የነዳጅ ዋጋ መናርን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የነዳጅ እና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት እና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ ቱሳ እንደሚሉት “ኢትዮጵያ ‘ዋጋ የማረጋጋት ፈንድ አስተዳደር አዋጅ' በሚል ስትመራ ቆይታለች።”
ዋና ዳይሬክተሩ ‘ዋጋ የማረጋጋት ፈንድ አስተዳደር አዋጅን' ሲያብራሩ “ይህ አካሄድ ድጎማ ከሚለው ሃሳብ ፈፅሞ የተለየ ሲሆን ለ2 አስርት አመታት ትርፍ እና ኪሳራ በማመጣጠን ሲሰራበት የቆየ ነው” ይላሉ።
“ለአመታት በኪሳራ ነበር ሽያጭ ሲካሄድ የነበረው” የሚሉት አቶ አህመድ “ምንም እንኳን በኮቪድ-19 ወቅት የነዳጅ ፍላጎት የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ላለፉት 2 ዓመታት ባለሥልጣኑ በህብረተሰቡ ላይ ያልጨመረው ግን ወጪ ያደረገው ተጨማሪ 24.5 ቢሊዮን ብር አለ” ብለዋል።
“በዚህ ላይ በታህሳስ ወር መጨረሻ የ1.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ጭማሪ በመታየቱና ይህ ደግሞ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዳ ስለሚችል 75 በመቶ መንግስት 15 በመቶ ደግሞ ለህብረተሰቡ በማካፈል ችግሩን ለመቅረፍ ተሞክሯል” ሲሉ አክለዋል።ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ “ታሪፍን አስመልክቶ ጭማሪ የተደረገው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ኪሳራ መሸከም ከሚችለው በላይ ስለሆነ ነው” ካሉ በኋላ “በጥር እና የካቲት የታየው የዋጋ ከፍ ማለት በዓለምአቀፍ ደረጃ የመጣ እንጂ መንግስት በህዝቡ ላይ ገንዘብ ለመጨመር ያለው ፍላጎት ተደርጎ እንዳይወሰድ አፅዕኖት ቢሰጠው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የካቲት 22 ፣ 2013
ቅናሽ ያልታየበት ኑሮ ፤ የነዳጅ ዋጋ ተጨምሮ
በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት አስመልክቶ ቃለ-መጠይቅ ያደረግንላቸው ሰዎች ከሚሰጡት አስተያየት መካከል