የካቲት 22 ፣ 2013

የኢትዮጵያ እና አሜሪካ የቃላት ውዝግብ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

“የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣት አለባቸው” - አሜሪካ “የፀጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግስት ኃላፊነት ነው፤ አያገባችሁም” - ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ እና አሜሪካ የቃላት ውዝግብ

“የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣት አለባቸው” - አሜሪካ
“የፀጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግስት ኃላፊነት ነው፤ አያገባችሁም” - ኢትዮጵያ

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ፤ የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም አንድ መግለጫ አውጥቷል። “በደል በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል” በሚል አርዕስት በወጣው በዚህ መግለጫ “አሜሪካ በትግራይ እየተባባሰ በመጣው ቀውስ ክፉኛ ሃሳብ ገብቷታል” ብሏል።


“በመጀመሪያ የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣት አለባቸው” ያለው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት እራሳቸውን ከኃይል እርምጃ አቅበው በትግራይ ድጋፍ የሚያሻቸው ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው መፍቀድ ይኖርባቸዋል” ሲል አትቷል።


ይህንን መግለጫ ተከትሎ በአንድ ቀን ልዩነት ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይ “የአማራ ክልል ኃይል ከትግራይ መውጣት አለበት” መባሉን ጠንከር ባሉ ቃላት ተቃውሟል።

“የአማራ ክልል ኃይል ከትግራይ መውጣት አለበት” በሚል በአሜሪካ በኩል የወጣው የመግለጫ ክፍል “የሚያስቆጭ” ነው ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “እንደ ሉዓላዊ አገር በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ በሚገኝ የትኛውም ክፍል የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አስፈላጊውን የደህንነት መዋቅር የማሰማራት ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት ነው፤ ይህም ግልፅ መሆን አለበት ብሏል።
 

“ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣት የማይናወጥ ቁርጠኝነት እንዳላት” ያስታወቀው ሚኒስቴሩ “ይህንን ዓለምአቀፍ ኃላፊነት እና ግዴታ መሰረት በማድረግ በአገሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች ውስጥ በመግባት ማድረግ ያለብንና የሌለብን ሊነገረን በፍፁም አይገባም” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

“የፌደራሉ መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሰላም እና ደህንነትን በማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ያስከብራል” ያለው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ፤ ይህንን ኃላፊነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ “በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ተልዕኮ መካሄዱን” አስታውሷል።
 

በሌላ በኩል “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ዓርብ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ላወጣው መግለጫ እውቅና እንሰጣለን” የሚለው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር “ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ፣ በክልሉ ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት በሚደረገው ሂደት ዓለምአቀፍ ዕርዳታን መንግስት እንደሚቀበል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ ለመሆኑ” የኢትዮጵያ መንግስት ቃል ገብቷል ብሏል።“ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት ወደ ተግባር እንዲቀየር በጋራ ሊሰሩ ያስፈልጋል” ሲል አክሏል።

“ዓለምአቀፍ አጋሮች በተለይም የአፍሪካ ኅብረት እና ክልላዊ የትብብር ኅብረቶች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት በትግራይ ያለውን ቀውስ በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር እንዲሰሩ እንጠይቃለን” የሚል ሃሳብም በመግለጫው ተካቷል።

“የተለያዩ ድርጅቶች በትግራይ ግድያ፣ በኃይል ማፈናቀል፣ ፆታዊ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተካሄደ እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል” የሚለው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ይህንን በፅኑ እንቃወማለን፤ እየተባባሰ የመጣው የሰብዓዊ ቀውስም በጥልቅ አሳስቦናል” ሲል አትቷል።    
 
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ “ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና 3 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር መድረስ መቻሉን” ጠቅሶ “70 በመቶ ድጋፍ በራሱ እያከናወነ” እንደሆነ ተናግሯል። “በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ያለገደብ ወደ ክልሉ ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ተፈቅዷል” ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “30 በመቶ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው” ብሏል።

“አሜሪካ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በነበራት ግንኙነት አመፅ ስለሚያበቃበት እና ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚደረግበት እንዲሁም ነፃ እና ገለልተኛ በሆኑ ዓለምአቀፍ አካላት ተፈፀሙ የተባሉ ጥሰቶች እንዲያጣሩ ማድረግ ስለሚኖረው ጠቀሜታ ንግግር አድርጋለች” ያለው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ጥፋት የፈፀሙ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲል አሳስቧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በምላሹ “መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ አጥፊዎች ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነት አለው” በማለት ገልጿል።

ይህንን የቃላት ውዝግብ ተከትሎ ጉዳዩ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃሳብ ምን እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ለሚኒስቴሩ ጥያቄ አቅርበን የነበረ ቢሆንም የፊታችን ረዕቡ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መግለጫ ስለሚሰጥ በዚያው ወቅት ጥያቄውን ማንሳት ይቻላል የሚል ምላሽ አግኝተናል።

አስተያየት