እሪ በሉ እሪ በሉ!
ለምኒልክ ንገሩ፣
እሪ በሉ እሪ በሉ!
ለወሌ ንገሩ፣
መንገሻ ለቀቀ፣ ተከፈተ በሩ፡፡
እንዲህ የተባለው ከዓድዋው ጦርነት ፩ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር፡፡ የሰሜኑ ደጀን ልዑል ራስ መንገሻ ዮሐንስ፤ በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ የደረጀ የጣሊያን ጦር ድንገት ቢዘምትባቸው፤ በቅጡ አልተዘጋጁምና ማፈግፈግ ግዴታቸው ሆነ፡፡ ይህን የተመለከተው የወቅቱ አዝማሪም ከላይ የሰፈሩትን ስንኞች በመሰደር፤ የሀገሪቱ በር መከፈቱንና ከማዕከል ፈጣን እርዳታ ማስፈለጉን በማያሻሙ ቃላት ገለፀ፡፡
እርግጥ በዚህ ትንኮሳ መንገሻ ተሸንፈው አልቀሩም፤ ጣሊያንም ገፍቶ አልመጣም፡፡ ሆኖም ግን ያ ትንኮሳ፤ ትንኮሳ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ ይልቁንም በዓመቱ ለተከሰተው ለአይቀሬው ታላቅ ጦርነት እንደ ማሟሟቂያ፣ እንደ መንደርደሪያ ነበር እንጂ፡፡ ስንኞቹም የአንድ ሰሞን ሁነትን ብቻ የሚጠቁሙ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም ማእከላዊውን ገዢ በአንድ አገረ ገዢ የማይመለስ፤ ከባድ ጠላት መጥቶልሃልና ተዘጋጅ የሚሉ የትንቢት ቃላት ነበሩ፡፡
የዓድዋ አዝማሪ
አንድ መቶ ሃያ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የዓድዋ ጦርነት፤ የኢትዮጵያን እና የጣሊያንን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለምን የፖለቲካ አስተሳሰብ የተገዳደረ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህ ታላቅ ድል ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በመዝመት ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ሴቶች የወደቀውን አቅኚ፣ የተራበውን አጉራሽ ሆነው መስዋዕት ሆነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ይብዛም ይነስም ጀግኖች ተመዝግበዋል፡፡
በዚህ ታላቅ ድል መሰንቆና ክራራቸውን አንግበው፤ የዘማቹን ወኔ በድፍረት ሲሞሉና ሲያነሳሱ፣ የወደቀውን ሲያጽናኑ፣ ያሸነፈውን ሲያሞግሱና ያጠፋውን ሲወቅሱ የነበሩ አዝማሪዎች ግን አልተመዘገቡም፡፡ እነርሱ ስለ ሁሉ ተናግረው፤ ስለእነርሱ የተናገረ ግን እምባዛም አልተገኘም፡፡ ስንኞቻቸውን የመዘገቡ ጥቂት የታሪክ መርማሪዎች ግን አልታጡም፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን፤ በትምህርትና ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር የተዘጋጀ የትምህርት ቤት መዝሙር የተሰኘ መጽሔት፤ “በአጼ ምኒልክ ጊዜ ለዓድዋ ጦርነት የተዘመረ መዝሙር” በሚል የሚከተለውን አስፍሯል፡፡
ግሩም ግሩም ጃንሆይ፣ ምኒልክ ግሩም
እንዳንተ ያለ ንጉሥ፣ እንዳንተ ያለ ጌታ፣
ዓድዋ ላይ ተሻግሮ፣ በሰይፍ የሚመታ፣
በሰይፍ አመታቱን፣ አሻግረው ቢያዩት፣
ግሩም ነው እያሉ፣ ግሩም ነው እያሉ፣
አደነቁለት!
ተክለፃድቅ መኩሪያ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ ለምኒልክና ለእቴጌ ጣይቱ፣ ብሎም ለመኳንንቱና ለወታደሩ ሁሉ የተዘፈነውና የተገጠመው ግጥም ብዙ መሆኑን ገልጠው፤ ነገር ግን የአብዛኞቹ አዝማሪዎች ስም በውል እንዳልታወቀ ያስረዳሉ፡፡ በስም ከተመዘገቡ አዝማሪዎች መካከል የወሎው ዐይነ ስውር አዝማሪ ሀሰን አማኑ አንዱ ነው፡፡ የጣይቱ ብጡል የቅርብ ተከታይ እንደሆነች የሚነገርላት አዝማሪት ጣዲቄም፤ በስም ከሚታወቁት ጥቂት አዝማሪዎች መካከል እንዷ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሀሰን አማኑ የምኒልክን ድል አድራጊነት ለመግለጽ፣ ከተቀኛቸው ስንኞች መካከል፤
ሸዋ ነው ሲሉት፣ ዓድዋ የታየው፣
ሺ-እናሺ መላሽ፣ ወንዱ አባ ዳኘው፣
ወዳጁም ሳቀ፣ ጠላቱም ከሳ፣
ተንቀሳቀሰ ዳኛው ተነሳ፣
አራቱ አህጉር ለሱ እጅ ነሳ፡፡
የሚሉ ስንኞች ይገኙበታል፡፡ የምኒልክ ድል ጣልያንን ያንበረከከ ብቻ ሳይሆን፤ የመላውን ዓለም ዕይታ የቀየረ ጭምር መሆኑን ልበ ብርሃኑ ሰው ልብ ያለ ይመስላል፡፡ “አራቱ አህጉር ለሱ እጅ ነሳ” ሲል፤ ከድሉ በኋላ ምኒልክን በጦር ሳይሆን በሰላም (በዲፕሎማሲ) ለመወዳጀት የተሽቀዳደሙትን ኃያላን በሚገባ ያስታውሳልና፡፡
የጦርነቱን አጠቃላይ ሁኔታና የምኒልክን መሀሪነት፤ በአንድነት ያንሰላሰለ ሌላ ስም አልባ አዝማሪ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡
አባተ በመድፉ አምሳውን ሲገድል፣
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል፣
የጎጃሙ ንጉሥ ግፋ በለው ሲል፣
እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ብርሃን፣
ዳዊቷን ዘርግታ ስማእኒ ስትል፣
እንዲህ ተሰርቶ ነው የዓድዋው ድል፡፡
ካለ በኋላ፤ ምኒልክ የተማረኩ ጣሊያኖችን በምን አኳኋን ይይዙ እንደነበር ለመግለጽ ደግሞ እንዲህ ይቀጥላል፡፡
ተማራኪው ባዙቅ ውሃ ውሃ ሲል፣
ዳኛው ስጠው አለ ሰላሳ በርሜል፣
እንደ በላኤሰብ እንደ እመቤታችን፣
ሲቻለው ይምራል የኛማ ጌታችን፡፡
ባህር ተሻግሮ መጥቶ ቀስ በቀስ እንደ ፍልፈል መሬት እየማሰ ዓድዋ የደረሰው ጣሊያን የኋላ ኋላ አይሆኑ ሆኖ መሸነፉ አልቀረም፡፡ ይህን የተመለከተው አዝማሪም፤
ባህር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጅ፣
እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጅ፣
አትረጋም አገር ያለ ተወላጅ፡፡
በማለት የሀገርን ሉአላዊነት በእብሪት መዳፈር መጨረሻው እንዲህ ያለን የሽንፈት ጽዋን መከናነብ መሆኑን ያስረዳል፡፡ አገር ለተወላጆቿ ብቻ የተገባች እንጂ፣ ባህር ተሻግሮ ልግዛ ለሚል ስግብግብ ቅኝ ገዢ እንደማትሆን ያስረግጣል፡፡
በጦርነቱ ይገጠምላቸው፣ ይዘፈንላቸው የነበሩት አጼውና መኳንንቱ ብቻ አልነበሩም፡፡ ሀገሬን ብሎ የዘመተው ሁሉ የአዝማሪዎቹ ግጥም ይከተለዋል፡፡ ሲደክም ያበረታዋል፣ ሲገድል ያሞግሰዋል፡፡ ሲያዝን ያጽናናዋል፡፡ ከየጎራው ተሰብስበው፣ በየሜዳው ወድቀው የቀሩ አያሌ ሰማዕት ኢትዮጵያውያንን የተመለከተው አዝማሪ እንዲህ በማለት ሀዘኑን አጋርቷል፡፡
ለዚያ ለወታደር መች ያዝንለት አጣ፣
አሞራ እንኳ ወርዶ ፊቱን ነጭቶ መጣ፡፡
አዝማሪነት ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጉዞ ተነጥሎ የሚታይ ሙያ አይደለም፡፡ ባለሙያዎቹም የማኅበረሰቡ የዘመን ፍሬዎች ናቸውና ቢከበሩም ባይከበሩም፤ ታሪክ ቢፃፍላቸውም ባይፃፍላቸውም ከደስታው ጋር ተደስተው፣ ከሀዘኑ ጋር አዝነው ህዝቡ አንደሆነው ሆነዋል፣ ህዝቡ እንደኖረው ኖረዋል፣ አሉ፣ ይኖራሉም፡፡ ዓድዋ ላይ ሽንፈትን የተከናነበው ፋሺስት ጣሊያን 40 ዓመታትን ቆጥሮ ለበቀል ሲመለስ አዝማሪዎችም በመሰንቋቸው ከአርበኞቹ ጋር ዳግም ተፋልመዋል፡፡ የአዝማሪዎቹን ሚና በሚገባ የተረዳው ወራሪም፤ አያሌ አዝማሪዎችን ሰብስቦ በግፍ ፈጅቷል፡፡
ከትናንት እስከ ዛሬ
ከዓድዋ ድል ማግስት ኢትዮጵያ የዓለምን ዐይንና ጆሮ በእጅጉ መሳብ ችላለች፡፡ ኢትየጵያን በጦር ማንበርከክ እንደማይቻል የተረዱት የወቅቱ “ኃያላን” አማራጫቸውን ወደ ሰላም በማዞር ለዲፕሎማሲያዊው ግንኙነት መሽቀዳደም ይዘዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሩሲያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነበረች፡፡ የወቅቱ የሩሲያው ዛር ኒኮላይ ሁለተኛ፤ መልዕክተኞቻቸውን ሲልኩ ታዲያ፤ ከእጅ መንሻዎቻቸው መካከል 40 የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይገኙበት ነበር፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሳሪያወች በጊዜው ለአፄ ምኒልክ የሚያስደስቱ ስጠታዎች ባይሆኑም፤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ግን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገራቸው አልቀረም፡፡
ከዚህ የሚጀምረው የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ትውውቅ፤ በተለይ ከአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ በሀገር ቤት ዘፋኞች ዘንድ በእጅጉ እየዳበረና እየተለመደ መጥቷል፡፡ አዝማሪነትም ከወትሮ ደረጃው ከፍ ብሎ፣ ቅቡልነቱ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በውጭ የሙዚቃ መሳሪያዎች ታጅበው የሚዘፍኑ ዘፋኞችም ስማቸው ወደ ድምፃዊነት ጎራቸውም ከዘመናዊያን ተርታ ተሰልፏል፡፡ ጥያቄው ታዲያ ዘመናዊዎቹ ድምፃዊያን ቀድሞም በዓድዋ፣ ቀጥሎም በማይጨው ሀገር ስለተዳፈረው ወራሪ ምን አሉ? ነው፡፡ ትናንት እንደ ማኅበረሰብ ዝቅ ተደርገው ዕየታዩ ስለ ሀገራቸው ግን ከፍ ብለው የተፋለሙ አዝማሪዎችን ያህል ተረካቢዎቹ ድምፃዊያን ዓድዋን እንዴት አስታወሱት? የአምስት ዓመቱንስ ወረራ እንዴት ከተቡት? ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
ዓድዋን ብለው ከዘፈኑ ጥቂት ቀደምት ድምፃውያን መካከል የባህል ድምፃዊው አድማሱ ግዛው አንዱ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ጀግኖች” በተሰኘው ቆየት ባለ ሙዚቃው እንዲህ ይላል፡-
የዓድዋ ጦርነት እንደምን ነበረ፣
ነጩ ገደል ገብቷል እየደነበረ፡፡
በሰላም ጥያቄ ተመለስ ቢሉት፣
አላስችለው ብሎ አለቀ ጠላት፡፡
ደግሞም ጣሊያን ከሄደ በኋላ፤ ቂም ቆጥሮ ስለመምጣቱ ለመግለጽ በዚሁ ዘፈን እንዲህ የሚሉ ስንኞችን አክሏል፡፡
ከሄደም በኋላ ተመልሶ መጣ፣
ቂሙን በማስታወስ በቀሉን ሊወጣ፡፡
ከቀደሙት ድምፃዊያን ስለ ዓድዋም ሆነ ስለ አምስቱ ዓመት መከራ የረባ ዘፈን ማግኘት አለመቻል ያስገርማል፡፡ ያልዘፈነው የለም የሚባልለት ጥላሁን ገሰሰ፤ ዓድዋን ብሎ ራሱን የቻለ ዘፈን ባያስቀርጽም፤ ከብዙ ሀገራዊ ዘፈኖቹ መካከል በጥቂቶቹ ውስጥ ዓድዋን ማንሳቱ ግን አልቀረም፡፡ “የጀግኖች ደም ጥሪ” በሚለው ወኔ ቀስቃሽ ስራው ቀጣዮቹ ስንኞች ተካተዋል፡፡
የዓድዋው ምኒልክ የሮም ባለ ዝና፣
ታየኝ ዘርአይ ድረስ ኢትዮጵያዊው ጀግና፡፡
“አጥንቴም ይከስከስ” በሚለው ዝነኛ ዘፈኑ ደግሞ እንዲህ ሲል ይደመጣል፡፡
የሀገሬ ጀግኖች ሴት ወንዱ ታጠቁ፣
ከእንግዲህ ለጠላት አንተኛም ንቁ፡፡
ጀግንነት እንደሆን የአባቶቻችን ነው፣
ሕብረታችን ፀንቷል ድል መምታት የኛ ነው፡፡
ወደ ዘመናችን እንምጣ፡፡ ከቅርብ ጊዜዎቹ ዘፋኞች መካከል ዓድዋ ላይ ማን ተቀኘ? እንማን ዘፈኑ? ብለን ስንጠይቅ፤ አሁንም እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ መልሳችን ጥቂት ብቻ ነው፡፡ በዚህ ትውልድ ስለ ዓድዋ ከዘፈኑ ድምጻውያን መካከል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በተለይ የጂጂ ዓድዋ ከሁሉ የላቀ ነው፡፡ ስንኞቹ ዓድዋን ከአንድ ዘመን ክስተት በላይ ከፍ አድርገው ያንሳፍፉታል፡፡ ዓድዋ የሰውነት ልክ ማሳያ፣ ማንም የማንም የበላይ ሳይሆን፤ ሁሉም በእኩል፣ ለእኩልነት የተፈጠረ ስለመሆኑ በተግባር የተገለጠበት ድንቅ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ዛሬ የነጭና የጥቁር የበላይ የበታች ትርክት፤ እንደ ባቢሎን ግንብ ተደርምሶ፤ ዓለም ለተጎናፀፈችው የነፃነት ትንፋሽ የዓድዋው ድል መሰረት ነበር በማለት፡፡
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ፣
የሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል፤ ከደምና ከአጥንት፡፡
የቴዎድሮስ ካሳሁን “ጥቁር ሰው” ስንኞችም ዓድዋን ከኢትዮጵያ ሰማይ ጥላ አርቆ ያስቀምጠዋል፡፡ ዓድዋ የጥቁሮች ሁሉ አንፀባራቂ ድል፣ ምኒልክም የጥቁሮች ሁሉ ንጉሥ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ድሉም የመላው አፍሪካና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ነው ይላል፡፡ እንዲህ በማለት፤
ኑ ዓድዋ ላይ እንክተት
ያ የጥቁር ንጉሥ አለና፣
የወኔው እሳት ነደደ
ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና፡፡
ዓድዋ-በዚህ ዘመን ድምጻዊያንም ሆነ በቀደሙት ዘፋኞች በወጉ ያልተዜመለት ታላቅ ድል ነው፡፡ የያኔዎቹ አዝማሪዎች በየአውዱ የተቀኙለትን ሩብ ያህል እንኳ፤ በዘመናዊዎቹ ድምጻውያን ዘንድ ገና በወጉ የተዳሰሰ አይመስልም፡፡ ከሁሉ በላይ የአሁኖቹ በጥቂት ስራ ከፍ ብለው የመጠራታቸውን ያህል፤ የትላንትናዎቹ ከያኒያን ግን በአብዛኛው፤ ስማቸው እንኳ ለታሪክ አለመጠቀሱ ይበልጥ ያሳዝናል፡፡ የእነዚህ ስም አልባዎች ስመጥር ስራዎች ግን ገና እልፍ ዘመን ተሻግረው ያስተጋባሉ፡፡ ለዛሬዎቹም ቢሆን አልረፈደም፡፡ ተግቶ ለሚያልም ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓድዋ ጀግኖች!