ጳጉሜ 2 ፣ 2014

ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የህትመት ተቋማት አንዱ የሆነው የድሬዳዋው ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት

City: Dire Dawaታሪክ

ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈረንሣይኛ-አማርኛ የመዝገበ ቃላት፣ የፈረንሳይኛ -ኦሮምኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፎችን እና ሌሎች ታሪካዊ ሰነዶችን አትሟል

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የህትመት ተቋማት አንዱ የሆነው የድሬዳዋው ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት
Camera Icon

ፎቶ፡ ዝናሽ ሽፈራው (የቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት ዕድሜ ጠገብ ማሽኖች)

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር መመስረትን ተከትሎ በርካታ የውጪ ሀገር ሰዎች ወደ ድሬዳዋ መጥተው በከተሙበት ዘመን መኖሪያ መንደራቸውን እና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን አቋቁመው ነበር። ለዚህም የመረጡት የከተማው ክፍል መሃል ከዚራን እንደነበር አሁን ድረስ በከዚራ ጎልተው የሚታዩት መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት ምስክሮች ናቸው። 

ከእነዚህ ታሪካዊ ቤቶችና አንጋፋ ተቋማት መካከል አንዱ ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት ነው። በ1908 ዓ.ም በላዛሪስት ሚሽነሪዎች የተቋቋመው ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት መሀል ከዚራ ከቅዱስ አውጎስጢኖስ ​​ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ይገኛል። ንብረትነቱም የቤተ-ክርስቲያኑ እንድሆነ ይታወቃል። 

ይህ ማተሚያ ቤት መጀመሪያ በሀረር ከተማ ተቋቁሞ የነበር ሲሆን የምድር ባቡር ድርጅት መመስረቱንና ብዙ ኢንዱስትሪዎች መቋቋማቸውን ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ ሊዛወር ችሏል። ለማተሚያ ያገለግሉ የነበሩት የተለያዩ ማሽኖች ከሀረር ከተማ በቄስ ቅዱስ አላዛር ኃሳብ አመንጪነትና በላዛሪስት ሚሽነሪዎች አማካኝነት በማስመጣት በድሬዳዋ ከተማ ማተሚያ ቤቱ ለመከፈት እንደበቃ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ። 

ስያሜውንም ከሀረር ወደ ድሬዳዋ ባመጡት ሚሽነሪዎች አማካኝነት እንዳገኘ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። ይህ ማተሚያ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለበርካታ አመታት ብቸኛ የምስራቅ ሀረርጌ ማተሚያ ቤት ሆኖ አገልግሏል። ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት የመጀመሪያ ጊዜያት ሀይማኖታዊ የሆኑ መፅሔቶችን ብቻ ያትም ነበር። በኋላ ላይ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንሳይኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ፈረንሳይኛ-ኦሮምኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፎችን እና ሌሎች ታሪካዊ ሰነዶችን አትሟል። 

በተጨማሪም ይህ ማተሚያ ቤት “ጦቢያ” የተሰኘውን ልቦለድ ማሳተሙ ይነገራል። ጦቢያ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል መሰረት ያደረገ በአፈወርቅ ገብረየሱስ የተደረሰ የመጀመሪያው በአማረኛ ቋንቋ የተፃፈ ልብ-ወለድ ነው። የመፅሃፉ ደራሲ አፈወርቅ ገብረየሱስ ትምህርታቸውን በጣሊያን ሀገር የተከታተሉ ሲሆን በኋላም በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

“ጦቢያ” ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በጣሊያን ሮም ከተማ ውስጥ ሲሆን ከዓመታት በኋላ በሀረር ከተማ በአላዛር ማተሚያ ቤት መልሶ መታተሙ ይነገራል።

በአሁኑ ሰዓት የአላዛር ማተሚያ ቤትን በኃላፊነት የያዙት አቶ አማኑኤል ዮሴፍ እንደሚናገሩት በወቅቱ መንፈሳዊ ስራዎችን ብቻ ይሰራ የነበረው የአላዛር ማተሚያ ቤት፤ በኋላ ላይ የምድር ባቡር ድርጅት ማስታወቂያዎችንና የተለያዩ መፈክሮችን ያትም እንደነበር ይገልፃሉ። እንደ አቶ አማኑኤል ገለፃ “ማተሚያ ቤቱ ከመንፈሳዊ ውጪ ያሉ ህትመቶችን በብዛት ማተም የጀመረው የደርግ መንግስት ከመጣ በኋላ ነው። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በወቅቱ በተለይ የገበሬ ማህበራትን የጽሁፍ ስራዎችን ማተሚያ ቤቱ ይሰራ ነበር። 

አቶ ዮሴፍ ጴጥሮስ በምድር ባቡር ድርጅት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን አሁን ላይ ወደ በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ተቋም ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ። እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ የምድር ባቡር እና የአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የህትመት ውጤቶች በአጠቃላይ በአላዛር ማተሚያ ቤት ይታተሙ እንደነበር ተናግረዋል። 

የምድር ባቡር የትራንስፖርት መረጃዎች፣ የባቡር ማዘዣ፣ ማስታወቂያዎች፣ የሚያስፈልጉ ወረቀቶች በሙሉ በአላዛር ማተሚያ ቤት እንደነበር ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ የአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የማስታወቂያ ስራዎችና የህትመት ውጤቶች በአጠቃላይ የሚታተሙት በአላዛር ማተሚያ ቤት እንደነበር ከአቶ ዮሴፍ ማብራሪያ መረዳት ተችሏል።

ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙት እድሜ ጠገብ የህትመት መሳሪያዎች በተለይ ማተሚያ ቤቱ እንደተቋቋመ የገቡት አብዛኞቹ ማሽኖች አሁን ላይ አገልግሎት አይሰጡም። ይሁንና አንዳንዶቹ ጥገና ቢደረግላቸው አሁንም አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ አቶ አማኑኤል ይገልጻሉ።

ማተሚያ ቤቱን ለአዲስ ዘይቤ ያስጎበኙት አቶ አማኑኤል እንደሚያስረዱት ማተሚያ ቤቱ በ1983 ዓ.ም ላይ ባልታወቀ ምክንያት ስራ ካቋረጠ በኋላ አገልግሎት መስጠት አቁሟል

አላዛር ማተሚያ ቤት በኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉት የህትመት ተቋማት የሚመደብ ሲሆን ስራ ጀምሮ እስካሁን ያለበት ህንፃም ትልቅና ታሪካዊ ከሚባሉት የድሬዳዋ ቀደምት ህንፃዎች መካከል ይመደባል። ህንፃው ከቀደምቱ እስከ ዘመናዊዎቹ ድረስ ያሉትን የማተሚያ መሳሪያዎች የያዘ በመሆኑ ያለፈበትን የህትመት ታሪክ ሂደት በቅደም ተከተል በራሱ መተረክ የሚችል እይታ አለው። 

Little Giant

ይህ ማሽን የአላዛር ማተሚያ ቤትን ለማቋቋም መጀመሪያ ላይ የገባ ማሽን ሲሆን ማሽኑን የኢንግሊዝ ሚሽነሪዎች ናቸው ያስገቡት። በወቅቱ ድሬደዋ ውስጥ በአብዛኛው እንግሊዛውያን ይኖሩ የነበር ሲሆን የድሬደዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ይገለገሉበት ነበር። ለማተሚያ ቤቱም ይህንን ማሽን በማስመጣት የራሳቸውን አስተዋፆ አበርክተዋል።

ይሄኛው ማሽን ደግሞ በጀርመን ላዛሪስቶች አማካኝነት የገባ ሲሆን ወረቀቶችን የማጠፍና የማጣበቅ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ይሰጥ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት አገልግሎት መስጠት ባይችልም በጊዜው ብዙ እንዳገለገለ ይነገርለታል።

Tempo

ይህ ማሽን ልክ መጽሐፍ ታትሞ ካለቀ በኋላ ለመቁረጥና ለመጠረዝ የሚያገለግል ማሽን ነው። ማሽኑን የጀርመን የላዛሪስት ሚሺነሪዎች ያስመጡት ነው። ማሽኑ በአሁኑም ሰአት አገልግሎት መስጠት ይችላል።

Heidelberg Einfarbig

ይህ የማተሚያ ማሽን በአላዛር ማተሚያ ቤት ከሚገኙት ማሽኖች ባጠቃላይ መጨረሻ ላይ የገባና ከሌሎቹ አንፃር ዘመናዊ የሚባል ማሽን ነው። ማሽኑን ፈረንሳዮች ያስገቡት ሲሆን በፍጥነት ለመስራት ያግዝ ነበር።

የቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት በኢ.ፌ.ድ.ሪ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና በድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት በቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኝ አንዱ የድሬዳዋ ቅርስ ነው።

የቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት በ2014 ዓ.ም 100ኛ ዓመቱን በደማቅ ስነ ስርዓት ካከበረውና በታህሳስ 1917 ዓ.ም ከተቋቋመው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እኩል በምስራቅ ኢትዮጵያ ብቸኛና የመጀመሪያ ሆኖ ለብዙ አመታት ሲያገለግል ቆይቷል።

ቅዱስ አላዛር ማተሚያ ቤት የሚገኘው ከድሬደዋ ቅዱስ አውግስጢኖስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚገኝ ግቢ ውስጥ ነው። ቤቱም ሆነ ማሽኖቹ ጥንታዊ ስለሆኑ የአሁኑ ትውልድ እንዲያውቃቸውና እንዲጎበኝ ምንም የተሰራ ስራ የለም። የእቃዎቹ አቀማመጥ ለመጎብኘት የሚጋብዝ ቢሆንም በተሻለ ፅዳትና በሚስብ መልኩ ቢቀመጥ ለጎብኚዎች ምቹ እንደሚሆን እሙን ነው። በተጨማሪም ለጎብኚዎች የተዘጋጀ የተደራጀ መረጃም አለመኖሩን አዲስ ዘይቤ ታዝባለች።

አስተያየት