ጳጉሜ 1 ፣ 2014

አዲስ አመትን የሚያበስረው የጎጃም ልጃገረዶች የእንግጫ ነቀላ ባህላዊ ክዋኔ

City: Bahir Darባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

እንግጫ በክረምት ወቅት በአካባቢው በብዛት የሚበቅል የለምለም ሳር ዓይነት ሲሆን እንደ አደይ አባባ ሁሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የሚገኝ ተክል ነው

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

አዲስ አመትን የሚያበስረው የጎጃም ልጃገረዶች የእንግጫ ነቀላ ባህላዊ ክዋኔ
Camera Icon

ፎቶ፡ምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ (ለበዓሉ ሴቶች በሐበሻ ቀሚስ አምረውና ተውበው በመስክ ላይ እንግጫ እየነቀሉ)

በኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት መምጣትን ተከትሎ በርካታ ባህላዊ ሁነቶች በየአካባቢው ይከናወናሉ። አብዛኞቹ ባህላዊ ክዋኔዎች ከለምለም ሳር እና ከአበቦች መፍካት ጋር ተያይዞ በወጣት ልጃገረዶች የሚከናወኑ ዓመታዊ ክበረ በዓላት ናቸው። 

ከእነዚህ በአደይ አበባና በለምለም ሳር ታጅበው ከሚከበሩ በህላዊ ክዋኔዎች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ ሻደይ፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል እየተባለ የሚጠራው የጋራ ትርጉሙ “ለምለም ሳር” ማለት እንደሆነ የሚነገርለት የሴቶች ክብረ በዓል ይታወቃል።

ከዚህ አንፃር በጎጃም አካባቢ ደግሞ የሚከበረው የእንግጫ ነቀላ ክዋኔ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ቁኒ፣ ሺኖዬ፣ ቁኒ ዳርባ፣ ኢኢሊ የተባሉ በየዓመቱ ልጃገረዶች ተሰብስበው ዓደይ አበባን ወይም ቁኒ የሚባለውን ቄጤማ በመንቀል በየቤቱ በመዞር የሚዘፍኑበትን እንዲሁም በከተሞች በስፋት የሚታወቀውንና ለአዲስ ዓመት ሴቶች ልጆች “እንቁጣጣሽ” እያሉ የሚያከብሩትን በዓል መጥቀስ ይቻላል።

የእንግጫ ነቀላ አመታዊ ክዋኔን በተመለከተ የአዲስ ዘይቤ ባለደረባ ከባህርዳር የሚከተለውን አጭር ዳሰሳ አድርጓል።

የእንግጫ ነቀላ በጎጃም አካባቢ የአዲስ ዓመት መምጣትን ለማመላከት የሚደረግ ደማቅ ባህላዊ ክዋኔ ነው። ኢትዮጵያ የራሳቸው የዘመን መቁጠሪያ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። እንግጫ ነቀላም ክረምት አልፎ ዘመን በተለወጠ ቁጥር የአዲሱን ዓመት መዳረሻና መባቻ የሚያመላክት ባህላዊ ክዋኔ ነው።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያ አቶ በልእስቲ ውቤ በሰጡን ማብራሪያ የአንግጫ ነቀላ ባህላዊ ክዋኔ ከአሮጌዉ ዓመት የመጨረሻ ወር ነሐሴ መጀመሪያ ጀምሮ የሚከበር ባህላዊ ክዋኔ ሲሆን ለዓመታት ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለባህላዊ ክዋኔዎች በተሰጠው ትኩረት አከባበሩ ዳግም እያንሰራራ መሆኑን አቶ በልእስቲ ይናገራሉ። 

ይህ የልጃገረዶች በዓል በብዛት በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ይከወን የነበረ ቢሆንም እየደበዘዘና በከተሞች አካባቢም እየጠፋ በመሄድ ላይ መሆኑን ባለሙያው ይገልፃሉ። እንደ ምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለፃ እንግጫ በክረምት ወቅት በአካባቢው በብዛት የሚበቅል ለምለም ሳር ነው። እንደ አደይ አባባ ሁሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በየአካባቢው በብዛት ይገኛል።

የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ይካሄዳል። ሴቶች በዚህ የቅድመ ዝግጅት ወቅት “ጠመናይ” እና ቀበርቾ” የተባሉ ቤት ውስጥ የሚጨሱ ስራስሮችን ይሰበሰባሉ። በአካባቢው እንደ ጨፌ የሚጎዘጎዝ “ከሴ” የተባለ ጥሩ መዓዛ ያለዉ ተክል ይገኛል። በዚህ ወቅት በብዛት ከሚገኘው ከሴ፤ ከአደይ አበባ ጋር ተደባልቆ ይታጨዳል።

በበዓሉ ወቅት ሴቶች በሐበሻ ቀሚስ አምረውና ተውበው በመስክ ላይ በመሰባሰብ እንግጫ እየነቀሉ የሚከተለው ዜማ ያዜማሉ። 

እንግጫችን ደነፋ፣ ጋሻዉን ደፋ፣

እንግጫዬ ነሽ ወይ፣ እሰይ እሰይ፣

የቅዱስ ዮሀንስ የመስቀል የመስቀል፣

የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ፣

መልሰህ ውሰደው ጉዳይም አይሞላ።

ይህንን ዜማ የሰሙ የአካባቢው ጎረምሶች ወደ ልጃገረዶቹ ይመጣሉ። ከመካከላቸውም ለወደዳት ልጃገረድ ቀደም ብሎ ያዘጋጀውን የአንገት ማህተብ በመስጠት ለእጮኝነት የመጠየቅ ባህላዊ ስርአት ይከወን ነበር።

የእንግጫ ነቀላ ባህላዊ ክዋኔ አዲሱን ዘመን በጥሩ ስሜት ለመቀበል የሚደረግ መሆኑን አቶ በለእስቲ ይናገራሉ። አንደ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያው ገለጻ “ይህ ባህላዊ ክዋኔ ቤት ለቤት በመዞር ይከወን የነበረ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የአደባባይ ባህል እየሆነ መጥቷል” ይላሉ።

በጎጃም አካባቢ ልጃገረዶች ሰብሰብ ብለው የሚያከብሩት ይህ የእንግጫ ነቀላ ባህል የራሱ በሆነ ዜማና ግጥም ያለው ሲሆን በጭፈራም የታጀበ ነው። በእለቱ ከሚዜሙት የህዝብ ዜማዎች ውስጥ የሚከተሉት ግጥሞች ይገኙበታል።

የቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ፣

ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ፣

እቴ አደይ አበባ ነሽ፣

ውብ ነሽ፣ ውብ ነሽ።

አመሻሽ ላይ ልጃገረዶቹ የሰበሰቡትን የእንግጫ ሳር እየጎነጎኑ ጣራ ላይ ያሳድራሉ። በነጋታው ልጃገረዶቹ ከያሉበት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰዉ ቤት እየዞሩ በመጨፈር ጎንጉነው ደጅ ያሳደሩትን እንግጫ በየቤቱ ምሰሶ ላይ በማሰር አዲሱን አመት ያበስራሉ፣ ተስፋና ምኞታቸውን በዜማና ግጥም ይገልፃሉ።

በዘመን መለወጫ ዕለት እንግጫው “ለበረከትና ለረድዔት” በሚል ራስ ላይ፣ የሊጥ እቃ ላይና ሌማት ላይ ይታሰራል። የተጎነጎነዉ እንግጫም እስከ መስቀል በዓል ድረስ ይቆይና ከደመራ ጋር ይቃጠላል። አመዱንም ከህፃን እስከ አዋቂ ድረስ ይቀቡታል። ይህ ለጤንነት ሲባል በማህበረሰቡ በልማድ የሚከወን ነው።

የእንግጫ ነቀላ በዓል የፍቅር ተጓዳኝ መፈለጊያ እና የወደፊት የትዳር አጋር ለማጨት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር ክብረ በዓል ነው። በዚህ ወቅት ከሚዜሙ የፍቅር መግለጫ የህዝብ ስንኞችን መሰረት በማድረግ ከዓመታት በፊት ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ስለ አዲስ አመት እንግጫ ነቀላ በዓል ዘመን የማይሽረው ድንቅ ሙዚቃ ሰርታ ማስደመጧ ይታወቃል። በዚህም የእንግጫ በዓልና ሴቶች የሚያዜሙት ጨዋታ በትውልዱ እንዲታወስና በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ የግሏን አስተዋፅኦ አበርክታለች። 

ድምጻዊት እጅጋየሁ (ጂጂ) በ1991 ዓ.ም ባወጣችው 'አንድ ኢትዮጵያ' በተሰኘው የሙዚቃ አልበሟ ውስጥ 'አደይ አበባ' በሚል ርዕስ የሚከተለውን አዚማለች።

እቴ አደይ አበባ የሶሪት ላባ፣

እቴ አደይ ነው ብዬ ጤፍ አረሞ ውዬ።

አንተ የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ፣

ጤፍ አበጥራለሁ የሰው ግዙ ነኝ፣

የሰው ግዙ ሁኖ የሰው ግዙ መውደድ፣

እሳት በገለባ እፍ ብሎ ማንደድ።

እንግጫ ጎንጉኜ በአደይ በሶሪት፣

እንቁጣጣሽ ብየ ቤቱ ዋልኩለት።

መስከረም ለምለሙ፣ መስከረም ለምለሙ፣

ብሩህ እንቁጣጣሽ ደስታ ለዓለሙ። 

በዚህ የእንግጫ ነቀላ ክዋኔ ወቅት ችቦ (ደቦ ይባላል በአካባቢው አጠራር) ማብራት በወንዶች በኩል የሚደረግ አንዱ የበዓሉ አካል ነው። በአካባቢው ችቦ የሚዘጋጀው “ኮሸሽሌ” የተባለን የእንጨት ዓይነት ስብስቦ በማድረቅ ነው። በሀገራችን በብዙ አካባቢዎች ለአዲስ ዓመት መባቻ ችቦ ማብራት ከክረምቱ ጭጋገና ጨለማ ወደ ብርሃን መሽጋገርን ለማመልከትና የብሩህ ዘመን ተስፋን ለማብሰር እንደምልክት ሲያገለግል ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። 

እንግጫ ነቀላ እና መሰል የአዲስ ዓመት ብስራትን የሚያመለክቱ የወጣቶች ጨዋታና በመልካም ምኞት ዜማ የታጀቡ ክብረ በዓላት ዛሬም በየአካባቢው ባህል መሰረት እየተከበሩ ቀጥለዋል። በረዥም ዘመናት ሂደት ውስጥ በተለያየ መልክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረው እዚህ የደረሱት የአዲስ ዓመት ክብረ በዓላት ሊታወቁ፣ ሊጠበቁ እና በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አስራር ተሰንደው ሊቀመጡ ይገባል።

አስተያየት