ሚሊዮን ፈቃዱ ቃሊቲ አካባቢ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት የሚያገለግል አይነ ስውር ወጣት ነው። ከአንድ አመት በፊት ከቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት የተበረከተለት እጅግ ዘመናዊ የአይነ ስውራን መርጃ መሳሪያ ህይወቱን በተለየ ሁኔታ እንዳቀለለት ይናገራል።
ከመሳሪያው ስላገኘው ጠቀሜታ አስተያየትቱን የጠየቅነው ሚሊዮን ሲናገር፣ “ይህ መሳሪያ ሰዎች በአይናቸው ብቻ አይተው ሊያደርጓቸው የሚችሏቸውን ነገሮች አይነ ስውራን ማድረግ ከማስቻሉ አንፃር ብዙ ጥቅም ሰጥቶኛል። ለምሳሌ የሰው እርዳታ ሳልፈልግ ሱፐር ማርኬት ሄጄ የምፈልገውን እቃ እንድመርጥ፣ ቀለማት መለየት እንድችል፣ በተለይ ደግሞ በአይነ ስውራን ዘንድ ከፍተኛ ተግዳሮት የነበረውን የገንዘብ ኖቶችን በቀላሉ የመለየትና የመሳሳት ችግርን አቃሏል። ከዚህ ባለፈ ንባብን በተመለከተ ለአይነ ስውራን ከፍተኛ ነፃነትን አጎናፅፏል” ይላል።
ይህ ለኢትዮጵያዊ አይነ ስውራን በቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት በኩል የተለገሰው OrCam MyEye ኦርካም ማይ አይ በመባል የሚጠራው ይህ መሳሪያ ለአይነ ስውራን መርጃ አለም ላይ ከተፈጠሩ መሳሪያዎች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እመርታ ያሳየ እንደሆነ ይነገራል። ይህ መሳሪያ እ.አ.አ የ2019 ምርጥ ፈጠራዎች አንዱ በመባል በታይም መፅሄት ችሮታ ተለግሶታል። መሳሪያው ከአንድ አዋቂ አውራ ጣት ከፍ ያለ መጠን ሲኖረው ከፊት ለፊት ከፍተኛ ጥራት ያለው ካሜራ እንዲሁም የድምፅ ማስተላለፊያ አለው። አንድ አይነ ስውር መሳሪያውን ሲጠቀም ካጠለቀው መነፅር ጎን በማጣበቅና እላዩ ላይ ያለውን ቀልፍ በመጫን ስራ ያስጀምረዋል።
መሳሪያው አይነስውራን በአካባቢያቸው ያለ ማንኛውንም እይታ በቀላሉ እንዲረዱ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን በመሳሪያው እይታ ውስጥ የገባን ማንኛውንም ቁስ ሆነ ፅሁፍ ምንነት በተገጠመለት የድምፅ ማስተላለፊያ ለተጠቃሚው ይናገራል። በዚህም እጅግ በቀላሉ ማንኛውም ነገር ላይ የሰፈረን ፅሁፍ ማንበብ እንዲችሉ፣ ሰዎችና ፊቶችን እንዲለዩ፣ በራሳቸው ግብይት እንዲፈፅሙ የሚያስችል ሲሆን በአጠቃላይ አይነ ስውራን ያለ ማንም እርዳታ ውጤታማ ህይወትና ስራ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ባለፈው አመት በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የእደላ ፕሮግራም ላይ ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ደሴ ከተሞች ለተመረጡ 2000 አይነ ስውራን መሳሪያው በቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት ተለግሷል። በስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው መሳሪያውን በአንድ ጊዜ ለሁሉም አይነስውራን ማዳረስ ባይቻልም አሁን የስጦታው ተካፋይ የሆኑትን አይነ ስውራን ደስታ ለሳምንታት መመልከታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ኦርካም ማይ አይ አሁን ባለው አለም አቀፍ ገበያ ላይ በየደረጃው ከ3500 እስከ 4500 ዶላር (ከ175,000 እስከ 235,000 ብር) በሚደርስ ዋጋ ለሽያጭ የቀረበ ሲሆን የመሳሪያው አምራች የሆነው OrCam የተባለው ተቋም መሳሪያውን በኢፌድሪ ቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በኩል ለአይነስውራን ኢትዮጵያዊያን በስጦታ ያበረከተ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ለማወቅ ችላለች።
መሳሪያው ለተመረጡ አይነስውራን በይፋ ከመሰጠቱ በፊት የተለያዩ ስልጠናዎችና ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትብብር ሲካሄዱ ቆይተዋል። መሳሪያው በሁለተኛ ዙር ለተጨማሪ አይነስውራን የተሰጠ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ በእንግሊዝኛ የተጻፉ ጽሁፎችን ብቻ ያነብ የነበረው ተሻሽሎ የአማርኛ ጽሁፍም እንዲያነብ ተደርጓል።
መሳሪያው ምን አይነት አገልግሎቶች ይሰጣል
ዋነኛው የመሳሪያው ትሩፋት በማንኛውም ነገር ላይ ሰፍሮ የሚገኝን ጽሁፍ አይነ ስውራን በቀላሉ እንዲያነቡት ማድረግ ነው።
አንድ አይነ ስውር መጽሀፍ፣ ኮምፒዩተር አልያም ሌሎች ነገሮች ላይ የተጻፈን ጽሁፍ ማንበብ ሲፈልግ ጽሁፉ ያረፈበትን ነገር በካሜራው ትይዩ እንዲሆን ቀና በማድረግ ጽሁፍ ያለበትን ስፍራ በጣት ይዞ በመቆየትና መሳሪያውን በመንካት ምስል ማንሳት ይጠበቅበታል።.መሳሪያው አመቺ በሆነ ቦታ ላይ በቂ ብርሀን ካገኘ ተስተካክሎ የተቀመጠን፣ ግርግዳ ላይ ወይም የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈን ማንኛውም ጽሁፍ ያለምንም እርዳታ ምስል በማንሳት በድምጽ ማንበብ ይጀምራል። ይህ መሳሪያ በ40 ሀገራት ለሚኖሩና አማርኛን ጨምሮ ከ26 በላይ ቋንቋ ተናጋሪ አይነ ስውራን ዜጎች መዳረሱን ከተቋሙ ድረ ገጽ ማወቅ ተችሏል።
ፅሁፍ ከማንበብ ጋር ስለተያያዘ ጠቀሜታው ሚሊዮን ሲናገር “በዚህ ረገድ ሰዎችን አንብቡልኝ ከማለትና በድምፅ የተነበቡ መፃህፍትን ከመፈለግ በቀላሉ ከንባብ ጋር እንድዛመድና ማንኛውንም መፅሃፍ መርጬ እንዳነብ መሳሪያው ረድቶኛል። መፅሃፍት ላይ ከሰፈረ ፅሁፍ ባሻገር፣ ለምሳሌ ሬስቶራንት ሄጄ ሜኑውን አንብቤ ምግብ ማዘዝ፣ የማስታወቂያ ፅሁፎችን፣ የምግብም ሆነ የመድሃኒት ሽፋኖች ላይ ያሉ መረጃዎችና መመሪያዎችን በመሳሪያው በቀላሉ እያነበብኩ ነው” ይላል።
ሌላው የመሳሪያው አገልግሎት የሰው ፊት ለይቶ ግለሰቡን ማሳወቅ ነው። የመሳሪያው ተጠቃሚ የሚያውቀውን ሰው ፊት በመሳሪያው ካሜራ ምስል በማንሳት በራሱ በተጠቃሚው ድምጽ ምስሉ የተነሳውን ሰው ስም ይናገራል። በዚህ ጊዜ መሳሪያው ይህንን የተጠቃሚውን ድምጽና የተነሳውን ሰው ምስል አንድ ላይ ይመዘግብና በሚቀጥለው ጊዜ ሰውዬው በተጠቃሚው ፊት ሲቆም የተቀረጸውን ድምጽ ያጫውታል። በተጨማሪም ያለምንም ሂደት ከፊት ለፊት የቆመን ሰው ጾታና ቁጥር ለይቶ ያሳውቃል።
“ሰው መለየትን በተመለከተ፣ ለምሳሌ አንድ ጓደኛዬን የሆነ ቦታ ቀጥሬው እንድንገናኝ የግድ እሱ እኔን ማየት አይጠበቅበትም። መምጣቱን ቀድሜ አውቄ ለሰላምታም ሆነ በወቅቱ ያለኝን ስሜት ለመግለፅ (reaction) በመሳሪያው እርዳታ ቀድሜ መዘጋጀት ችያለሁ” በማለት ሚሊዮን አስተያየቱን ይሰጣል።
በተመሳሳይ መንገድ አስቀድመው በዝርዝር የተሰጡትን እንደወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መስኮት፣ የቆመ ዛፍ፣ ደረጃ፣ ግርግዳና ሌሎችንም የሚታዩ ነገሮችን ለይቶ ያሳውቃል። መሳሪያው ተጠቃሚው በተለምዶ እጁን አንስቶ ሰአት በሚታይበት አኳኋን ከመሳሪያው ካሜራ ፊትለፊት ሲያደርግም ሰአት መናገር ይችላል።
መሳሪያው ምን ቀረው
ኦርካም እነዚህ ፈርጀ ብዙ አገልግሎቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው አንዳንድ ክፍተቶችም እንደሚስተዋሉበት ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ። መሳሪያውን ካገኘ ወዲህ ብዙ ማትረፉን የሚገልጸው የህግ ባለሙያው ይስሀቅ አበራ “አንዳንድ ጊዜ በቂ ብርሀን ኖሮም እንኳን ከፊት ለፊት ያለውን አንድ የመጽሀፍ ገጽ አያስጨርስም፣ ያቆራርጣል” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።
ኦርካም ማይ አይ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ ለተጠቃሚ አይነ ስውራኑ የድምፅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ሲሆን የአማርኛው አገልግሎት በቅርቡ ከመጀመሩ አንፃር የተለያዩ ግድፈቶች ሳይስተዋሉበት አልቀሩም። ሚሊዮን በዚህ ነጥብ ላይ ሲናገር “የአማርኛውን አገልግሎት የመጀመሪያ የሙከራ ደረጃ ላይ (beta version) እንዳለ ነው የምቆጥረው። ግድፈቶች ይስተዋሉበታል፤ ሆኖም ግድፈቶች የሚባሉት ይህን ያህል የምታነበውን ነገር እንዳትረዳ የሚያደርግ አይደለም” ይላል።
በተመሳሳይ የመሳሪያው ተጠቃሚ የሆኑትና በአቃቤ ህግነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ እዝራ ደረጀም “በተለይም መሳሪያው አማርኛ እንዲያነብ ተደርጎ መሻሻሉ ትልቅ እመርታ ነው” ይላሉ። “ከምንም በላይ እራሴን ችዬ የውሳኔ መዝገቦች ማንበብ መቻሌ ትልቅ እፎይታ እየሰጠኝ ቢሆንም፣ መሳሪያው የአማርኛ ሆሄያትን ገድፎ የማንበብ ክፍተት አይቼበታለሁ” ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም የማንበቢያ ሶፍትዌሮችን የመጠቀም ልምድ እንዳለው የሚናገረው ሚሊዮን እነዚህ ግድፈቶች ሌሎች ተመሳሳይ የማንበቢያ አገልግሎቶች ላይ የሚታይ በመሆኑ በቀላሉ መቀረፍ የሚችሉ እንደሆኑ ይገልፃል። “በዚህ ስራ ላይ ከተሳተፈች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ባለሙያ ጋር በነበረኝ ቆይታ፣ የተቀዱት ድምፆች ወደ መሳሪያው ተገጣጥመው የተጫኑ እንደሆነና እንደ ፊደል መግደፍ፣ ማለፍ፣ የቶን፣ ፊደላትን የማጥበቅና የማላላት ችግሮች የተፈጠሩት በዚህ ምክንያት ሊፈጠሩ እንደቻሉ ማወቅ ችያለው” በማለት ያስረዳል።
በተጨማሪም መሳሪያው በቂ ብርሀን ባለበት ስፍራ የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሙሉ በሙሉ አይነስውር የሆኑ ተጠቃሚዎች የሚበቃውን ብርሀን ለመመጠን መቸገራቸውና የእጅ ፅሁፍ አለማንበቡ ሌሎች የሚነሱ ክፍተቶቹ ናቸው።
መሳሪያው ለኢትዮጵያውያን አይነ ስውራን አገልግሎት ላይ ከዋለ ገና አንድ አመት ከመሆኑ አንፃር የሚነሱት ክፍተቶች የሚጠበቁና በጊዜ ሂደት በቀላሉ መሻሻል እንደሚችሉ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ያምናሉ።
“የሚጠቀሱት ችግሮች እንዳሉ ሆነው በዚህ አጭር ጊዜ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ በዚህ ደረጃ ለአገልግሎት መብቃቱን አደንቃለሁ። ለምሳሌ ሌሎች ተመሳሳይ የማንበቢያ አገልግሎቶች ላይ ያለው አርቴፊሻል ድምፅ እንዳይኖር የሰው ድምፅ እንዲሆን መደረጉ ራሱ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። ከተነሱት ነጥቦች በተጨማሪ የምሰጠው አስተያየት ቢኖር መሳሪያው ላይ ካለችው አንድ ሴት አንባቢ እንደ አማራጭ የሚሆኑ ሌሎች አንባቢዎች ቢኖሩ አገልግሎቱን የበለጠ ያበለፅገዋል ባይ ነኝ” በማለት ሚሊዮን ያለውን ጥቆማ ይሰጣል።
በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሙሉና በከፊል አይነ-ስውራን መኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጤና ተቋም WHO ሪፖርት ያሳያል። ከእነዚህ መካከል 3/4ኛው ሙሉ በሙሉ አይነ-ስውራን የሆኑና በሀገሪቱ ጎልቶ በሚታየው የተደራሽነት ችግር ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ከጽሁፍ ውጤቶች ተጠቃሚ አይደሉም።
ኦርካም ማይ አይ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ ለሆኑ እንዲሁም በትምህርትና በእለት ተለት ህይወታቸው አያሌ ተግዳሮት ላለባቸው ኢትዮጵያዊ አይነ ስውራን የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል። የመሳሪያውን ተደራሽነትም ለማስፋት የቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት የጀመረውን ሰናይ ተግባር እንደሚቀጥልበት ተስፋ እናደርጋለን።