ነሐሴ 27 ፣ 2014

የጎዳና ህይወት በአዲስ አበባ ድልድዮች ስር

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ዝናብ የመጣ እንደሆነ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ድልድይ መሮጥ እና ድልድዩ ስር መጠለል የግድ ይሆናል፤ ያው የምሽት ቤታቸው እንደመሆኑም ይሄ የእኔ ቦታ ነው የሚል ንትርክ አይገጥማቸውም

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የጎዳና ህይወት በአዲስ አበባ ድልድዮች ስር
Camera Icon

ፎቶ፡ ኤልያስ ክፍሌ

በተለመደው አጠራር ጎዳና ተዳዳሪ ይባላሉ፤ 'ተዳዳሪ' የሚለው ቃል እድሜ ልካቸውን የሚኖሩ ያስመስለዋል ብለው የሚቃወሙ ግለሰቦች ደግሞ 'ጎዳና አዳሪዎች' የሚለውን ስያሜ ይመርጣሉ። አዲስ ዘይቤ ለማነጋገር የሞከረቻቸው ጎዳና አዳሪዎች አብዛኛዎቹ አጠራሩ ላይ ችግር የለብንም ቢሉም ጎዳና ለጊዜውም ሆነ በዘላቂነት “ብቻ መኖሪያችን” ነው በሚለው ይስማማሉ።

በበጋ ወቅት የሚለበስ እንኳን ሳይፈልጉ በመሸባቸው ቦታ ማደርን ይመርጣሉ፤ ክረምት ግን እንዲህ እንደዋዛ በመሸበት ማደር አይሰራም። ዶፍ ዝናብ፣ ጎርፍ፣ ውርጭ የማይደርስበት ቦታ መምረጥ የግድ ይላቸዋል። ለዚህ ደግሞ ከድልድይ በታች የተሻለ ቦታ አይገኝም ይላሉ፤ ጎዳና አዳሪዎቹ። የአዲስ ዘይቤ ትዝብትም ይህን ያረጋገጠ ነው።

የጎዳና አዳሪዎቹን እውነታ ለመታዘብ አዲስ ዘይቤ ከመገናኛ ወደ ሳሪስ በሚወስደው መንገድ የሚገኘው ተሻጋሪ ድልድይን እንዲሁም በጎተራ ማሳለጫ በሚገኘው ግዙፍ ድልድይ ስር ተጉዛ ሁኔታዎችን ለመቃኘት፤ ጎዳና አዳሪዎቹንም ለማነጋገር ሞክራለች። 

ከድልድዮቹ ስር ሌላ ህይወት አለ። እንደ ነገሩ በካርቶን እና ጣውላ የታጠሩ ክፍሎች የሚመስሉ ስፍራዎች አሉ፤ መሀላቸው ቀጫጭን ፍራሾች፣ ብርድ ልብሶችና አንሶላዎች አሉ። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሶፋዎች እና ምድጃዎችም ይታያሉ። 

ህፃናት ከነወላጆቻቸው አነስተኛ ቦታ ላይ ተሸክፈው ይታያሉ፤ ወጣቶች በብዛት አራትም አምስትም ከዚያም በላይ ሆነው ሙቀት ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ተጠባብቀው ይተኛሉ (ፈቃዳቸው ባለመሆኑ በምስል ለማስቀረት አልተቻለም)፤ ሌሎች የተወሰኑ ወጣቶች ደግሞ ንጋት ላይ እሳት አያይዘው በዙሪያው ተኮልኩለው ይጨዋወታሉ።

አብነት በጎተራ ድልድይ ስር ከሚያድሩ ጎዳና አዳሪዎች እና ወጣቶች መካከል ነው። ጓደኞቹ 'መልኬ' ብለው ይጠሩታል፤ ፀጉሩ ሲበዛ ሉጫ፣ ቁመቱ እንደዘንድሮ የሞዴሊንግ ባለሙያ ወጣቶች ዘለግ ያለ ነው፤ ስሙንም በዚያ ምክንያት እንደሰጡት ይናገራሉ። 

አብነት ወደ ጎዳና የወጣበትን ጊዜና ምክንያት ማስታወስ አልፈልግም በማለቱ አላጋራንም። ሆኖም ድልድልዮቹ በጎዳና አዳሪዎቹ ዘንድ ለምን ተመራጭ ሆኑ ለሚለው ጥያቄያችን፣ “እንዴ! ድልድዮቹ ለእኛ በአጭሩ ቤታችን ናቸው። እንዲሁ ዝምብለን በምናብ የሳልነው ቤት ሳይሆን እንደሀብታሞቹ በክረምት ከዝናቡና ብርዱ፤ በበጋም አልፎ አልፎ ከፀሀዩ የምናርፍባቸው ቤታችን ናቸው” ይላል።

በእርግጥ ብዙሀኑ ጎዳና አዳሪዎች የሚስማሙበት እና የሚያስገርመው ሀሳብ “ጎዳና አዳሪ በቀን አይተኛም” የሚለውን ነው። እንዴት ማለት እዚህ ጋር ተገቢ ነውና ይህን ጥያቄ አቀረብንላቸው። “አይደለም እኛ ጎዳና አዳሪዎች ኑሮ የሞላላቸው ራሱ እኮ ቀን ቀን አይተኙም ደግሞ ሆድ ባዶ ሆኖ እንቅልፉ ራሱ ከዬት ይመጣል?” ሲል አብነት ጥያቄውን በጥያቄ መልሷል። አብረውት የነበሩት ጓደኞቹም ይሄ የሁሉም እውነታ እንደሆነ ይመሰክራሉ።

ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፉት ግማሾቹ የተጣሉ የፕላስቲክ ምርቶችን፣ ከፊሎቹ ደግሞ ብረታ ብረት ለቅመው ይሸጣሉ። ይህን የሚያደርጉት ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ በልቶ ለማደር ቢሆንም የሰበሰቡት ገንዘብ እንዲቀመጥላቸው ሲሉ በየምግብ ቤት እየዞሩ 'ተመላሽ' መፈለግም የየእለት ተግባራቸው ነው። 'ተመላሽ' ማለት የምግብ ቤት ደንበኞች በልተው የተረፋቸው እና ተጠራቅሞ በፌስታል የሚሰጣቸው ምግብ ነው፤ ተመላሽ በነፃ የሚሰጧቸው ምግብ ቤቶች እንዳሉ ሁሉ በተወሰነ ፍራንክ የሚሸጡላቸው እንዳሉም ጎዳና አዳሪዎቹ ይገልፃሉ።

ይህንን የእለት ተዕለት ህይወት ሲያሳልፉም ድንገተኛው ዝናብ የመጣ እንደሆነ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ድልድይ መሮጥ እና ድልድዩ ስር መጠለል የግድ ነው። ያው የምሽት ቤታቸውም እንደመሆኑ ይሄ የእኔ ቦታ ነው፤ ይሄ የእኔ ድልድይ ነው የሚል ንትርክ አይገጥማቸውም። 

“ጎዳና አዳሪ ከጎዳና አዳሪ ጋር በፍፁም አይጋጭም፤ እንደውም ብዙ ጊዜ የምግብ ቤት ተመላሽ ተሳክቶለት የሚያገኘው ትንሽ ሰው ስለሚሆን ሲበሉ ካየህ ሄዶ መቀላቀል ነው” ሲል የሚገልፀው ደግሞ ሳሪስ አደይ አበባ አካባቢ በሚገኘው ተሻጋሪ ድልድይ ስር የሚኖር አንድ የ17 ዓመት ታዳጊ ነው።

ድልድይ ስር ከማደር ከባዱን ፈተና አብዛኛዎቹ ይጋሩታል፤ ምሽት ከመተኛታቸው በፊት ዝናብ የማያገኘው ቦታ ወይም ድንገት ከዘነበ ውሃ የማይደርስበት ቦታ መርጠው ቢተኙም የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ሌሊት ከባድ ዝናብ መጣሉ አይቀርም። ብዙውን ጊዜ ተኝተው ሲዘንብ ካልደረሰባቸው በስተቀር ከእንቅልፋቸው አይነቁም፤ የሚነቁት የሚወርደው ውሃ የተኙበት ቦታ ሲደርስ ብቻ ነው። ከዛ በኋላ ያለው አማራጭ ውሃ የማይደርስበት ቦታ ፈልጎ መቀየር ቢሆንም እንደዝናቡ ክብደት ደረቅ ቦታ ላይገኝ ይችላል። ያ ከሆነ ቁጭ ብሎ መጠበቅ እና ዝናቡ ረገብ ሲል ሌላ ቦታ መፈለግ የግድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቤዛዊት በጎተራ ድልድይ ስር የ4 ዓመት ህፃን ልጇን ይዛ ነው የምትኖረው። “እኔ ህፃን ልጅ ስላለችኝ አሁን አልሯሯጥም፤ ተመላሽም ምግብም ሆነ ሌላ የምፈልገውንም ነገር ሌሎቹ የእኔ ቢጤዎች ያመጡልኛል” ትላለች። ቤዛዊት በአንድ የድልድዩ ቋሚ ስር የቀሩትን ሶስት ጎኖች በጣውላ እና ካርቶን አጥራ ከልጇ ጋር የሚያርፉበትን አዘጋጅታለች። “ይሄን ክረምት እንግዲህ እዚህ ጎተራ ድልድይ ስር አሳልፈናል፤ የቀጣዩን ዓመት ክረምት ደግሞ የት እንደምናሳልፍ ፈጣሪ ያውቃል፤ ያው ቦታው ሊለያይ ይችላል እንጂ ከድልድይ ውጪ መጠለያ የለንም” ብላ “ድልድዮቹ ለእኛ ባለውለታ ናቸው ማለት እችላለሁ” በማለት የኑሯቸውን አስቸጋሪነት ታስረዳለች።

የክረምቱን አስቸጋሪ ዝናብ ከድልድዮቹ ስር ከማሳለፍ የተሻለ አማራጭ ባይኖራቸውም ሌሎች እንደሁኔታው የሚያሳልፉባቸው ሁኔታዎች አሉ። “አብዛኛዎቹ ባይፈቅዱልንም በረንዳ ያላቸው ፎቆች ስር የሚያድሩ አሉ። እንዳንዴ ተጀምረው ያላለቁ ህንፃዎች ላይም ይታደራል። በጣም አማራጭ የታጣ ቀን ፖሊስ ጣቢያ ለማደር ሲባል ፖሊሶች ያሉበት አካባቢ ወይም እስከሚያልፉ ጠብቀህ አውቆ ፀብ እና ግርግር መፍጠርም ይኖራል” በማለት ያነጋገርናቸው የጎተራ ጎዳና አዳሪዎች ነግረውናል።

ከቀትር በኋላ በስፋት ከድልድዮች ስር ያሉ ስፍራዎች በጫት ቃሚዎች ይዘወተራሉ። የጎዳና አዳሪዎችም አብዛኛዎቹ የተለያዩ ሱሶች ያሉባቸው በመሆኑ ብዙ አያስኮርፋቸውም። “እንደውም ገራባዉን [ከጫት ተርፎ የሚጣለውን] ሰብሰበን ዝናብ ያልነካውን ማታ ማታ አቀጣጥለን እንሞቃለን” የሚለው ደግሞ ወጣቱ ኢብሳ ነው። 

ከዚህም ባለፈ የእለት እንጀራቸውን ለማግኘት ከአንዳንድ ስጋ ቤቶች ቅንጥብጣቢ በማምጣት እና ከሌሎች ሱቆችና አትክልት መሸጫዎች ደግሞ ሊበላሹ የደረሱ ሽንኩርትና ቲማቲም ለምነው አምጥተው እሳት አንድደው ምግብ እንደሚሰሩ አብዛኛዎቹ አጫውተውናል። ምግብ አሰራራቸውን በተመለከተ አብነት ሲያስረዳ “ያው ጨው የሚታሰብ አይደለም። ቆርቆሮ እንደ ቢላዋ፣ ጣሳ ደግሞ እንደድስት ነው የምንጠቀመው። ያው ጎዳና ላይ ስትኖር በዙሪያህ ያሉትን ነገሮች መጠቀም የግድ ነው” ይላል።

ያው አሁን የክረምቱ መውጫም ደርሶ የለ፤ የጎዳና አዳሪዎቹ ድልድዮቹን እንደባለውለታ የሚቆጥሩበት ጊዜ ነው። ክረምት ሊወጣ ሲል ክረምቱን ሳይንገላቱ በማሳለፋቸው ተመስገን የሚሉት ጎዳና አዳሪዎቹ፤ ለመጪው ክረምት አሁን አይጨነቁም። ምንም ያህል ከባድ ዝናብ ቢጥል ያው ቀላሉ መፍትሔያቸው በአቅራቢያቸው ያለ ድልድይ ስር ማደር ነውና።    

አስተያየት