ነሐሴ 25 ፣ 2014

ስራ ያቆሙት የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች እና 'አጎዋ'

City: Bahir Darኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችከተማ

ምርት ለመጀመር ከ 4,000 በላይ ሠራተኞችን ለመቀበል ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች 500 ገደማ ሰራተኞች ብቻ ይዞ ሥራ ጀምሮ ነበር።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ስራ ያቆሙት የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች እና 'አጎዋ'
Camera Icon

ፎቶ፡ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን (በስምንት ሼዶች ስራ የጀመረው የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ)

ፋጡማ ኢብራሂም በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እየሰራች ባለችበት ሰዓት በድንገት የፋብሪካው የስራ ሃላፊዎች መጥተው “ለምርት የሚሆን ጥሬ እቃ የለም። ለማስመጣት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞናል” በማለት ስራው መቋረጡን ተናገሩ። “ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ተመልሰን ስራ እንደምንጀምር ነግረውን ነበር። ነገር ግን ስራ ከአቆምን ይሄው ሶስት ወር ሆኖናል” ትላለች ፋጡማ።

የአዲስ ዘይቤ ሚድያ የባህር ዳር ሪፖርተር ስራ ያቆሙትን የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ቅሬታ ይዞ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር እንዲህ አጠናቅሮ አቅርቧል። 

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገራችን ከተቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሥራ ሦስተኛው ሲሆን ለአማራ ክልል ደግሞ ከደብረ ብርሃን እና ከኮምቦልቻ በመቀጠል ሦስተኛው ነው። ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ መስከረም 27/2013 ዓ.ም ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ መመረቁ ይታወሳል። 

በምርቃ ወቅት ፓርኩ በ2 ፈረቃ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር 10 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጾ ነበር። በአሁን ሰዓት ኢንዱስትሪ ፓርኩ 8 የተሟላ ቁሳቁስ ያላቸውን የማምረቻ ቦታዎች የያዘ ሲሆን እያገባደድነው ባለው ዓመት 2014 ዓ.ም ላይ አጋማሽ ሥራ ጀምሯል።

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በያዝነው ዓመት ምርት ለመጀመር ከ 4,000 በላይ ሠራተኞችን ለመቀበል የልየታ ስራ ሰርቶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች 500 ገደማ ሰራተኞች ብቻ ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል። 

በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እስካሁን “ሆፕ ሉን” የተባለ የሆንግ ኮንግ ኩባንያ ለጨርቃ ጨርቅ እና ጋርመንት ምርት ስምንት ሼዶችን (የማምረቻ ዳሶችን) የወሰደ ቢሆንም ስራ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ በአንድ ሼድ ብቻ ሠራተኞችን አሰልጥኖ ምርት ማምረት ጀምሮ ነበር። ምርቶቹንም ወደ አሜሪካና አውሮፖ በመላክ የኤክስፖርት ስራውን ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል።

‘ሆፕ ሉን’ በተባለው ድርጅት ውስጥ በተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ከነበሩት ሰራተኞች አንዷ ትግስት ይርጋ ናት (ስሟ የተቀየረ) ። ትግስት ለአዲስ ዘይቤ ኃሳቧን መግለጽ ስትጀምር “ለስራ ዋስትና ስለሌለኝ ስሜን መግለፅ አልፈልግም” ትላለች። 

“በድንገት ምንም አይነት መረጃ ሳይሰጠን ሳንዘጋጅ ነው ስራ ያቆምነው። 'ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ስራ ትጀምራላችሁ' ተብለን ነው ስራ ያቆምነው” ትላለች ትግስት በቅሬታ።

ሆፕ ሉን የተባለው የጋርመንት (የተዘጋጁ ሙሉ ልብሶች ) አምራች ድርጅት ከወራት በፊት ከ500 መቶ ሰራተኞችን ይዞ ወደ ስራ ቢገባም፤ ለጥቂት ወራት ከሰራ በኋላ ስራ አቁሟል። በመሆኑም ሰራተኞቹ ላለፉት ሶስት ወራት ስራ ከመፍታታቸውም በላይ “ወደ ስራ ላይመልሱን ይችላሉ” የሚል ስጋት አላቸው።

በወቅቱ ከስራ ኃላፊዎቻችን እንደተነገረን “ጥሬ እቃ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት አልቻልንም። አሁን የሀገሪቷ ወደ ውጭ ምርታችን መላክ አልቻልንም”በሚል ምክንያት እንደሆን የምትናገረው ትግስት። በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት የጥሬ እቃ እጥረት ገጥሟቸው  እንደነበርም አልሸሸገችም።

ፋጡማ ይብራሂም በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሆፕሉን ካምፓኒ ሰራተኛ ናት። እንደ ፋጡማ ማብራሪያ “በድንገት ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ስራ ትጀምራላችሁ ተብለን ስራ አቆምን። ከዛሬ ነገ እያልን ስንጠብቅ ሶስት ወር ሞላን” ትላለች። “ስራ ለማቆም በወቅቱ የተሰጠን ምክንያት 'ለምርት የሚሆን ጥሬ እቃ የለም ለማስመጣት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞናል' የሚል ነበር” ትላለች።

ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ ድርጅቱ ሲደወል ስልክ እንደማይነሳ እና ወደ ግቢም ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ መከልከላቸውን ሰራተኞቹ ገልጸዋል። ምንም እንኳን ደሞዝ ዘግይቶም ቢሆንም እንደተከፈላቸው ተናግረው “ምንም ዓይነት መረጃ ስለሌለን በስራችን ለመቀጠል ስጋት ላይ ነን” ይላሉ።

እንደ ፋጡማ ገለፃ “ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ስራ አቁሞ ሊወጣ ነው የሚል መረጃ ደርሶን በተወካያቸው አማካኝነት ለክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አመልክተን ነበር። 'ድርጅቱ ጊዚያዊ ችግር ገጥሞታል፤ ስራ ሙሉ በሙሉ የሚቆም ከሆነ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት የእናንተ ጉዳይ ይታያል' የሚል ምላሽ” ተሰጥቶናል ብላለች።

“ድርጅቱ ስራ የሚያቆም ከሆነ የሚገባንን የስንብት ክፍያ ሊከፍለን ይገባል” ትላለች ፋጡማ ኢብራሂም። ነገር ግን አሁን ከድርጅቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት በመቋረጡ ማሽኖችን ነቅሎ ቢወስድ እንኳን መረጃ ማግኘት እንደማይችሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

እንደ ሰራተኞቹ ማብራሪያ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አሰሪ ድርጅቱን እንዲጠይቁላቸው ቢማጸኑም፤ በመንግስት የተመደቡ የፓርኩ አስተዳዳሪዎች “ለሚዲያ መረጃ አልሰጥም!” በማለታቸው ጉዳዩ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሊያገኝ አልቻለም። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተርም በበኩሉ የኢንዱስትሪ ፓርኩን የስራ ኃላፊዎች በስልክና በአካል በመሄድ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በሌላ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸው አቶ ዘውዱ ደሳለኝ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የስራና ስልጠና መምሪያ የስራ ስምሪት ቡድን መሪ ናቸው። አቶ ዘውዱ “የባህር ዳር የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ስራ ማቆማቸውን እንዲሁም ደሞዝ እየተከፈላቸው እንድሆነም መረጃ ደርሶናል” ብለዋል።

“ነገር ግን ሰራተኞቹ ወደ መምሪያው መጥተው ቅሬታ አላቀረቡም” ያሉት  አቶ ዘውዱ ደሳለኝ፤ ድርጅቱ ስራ የማይጀምር ከሆነ የሰራተኞችን ጥቅማ ጥቅም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት እንዲፈጽም ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞች በስራ ዋስትና ስጋት እና በሌላም ምክንያት ስማቸውን ከመግለጽ ቢቆጠቡም፤ በድንገት ስራ ለማቆማቸው መነሻው የአሜሪካን መንግስት ውሳኔ (ኢትዮጵያን ከአጎዋ መስረዟ) መሆኑን በጋራ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ሆፕሉን ካምፓኒ ምርቱን በዋነኝነት የሚያቀርበው ለአሜሪካ ገበያ መሆኑን በማስታወስ።

አሜሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ምርታቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሰጠችውን ዕድል (አጎዋ) በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን አግዳለች። ሀገራችን ከዚህ የንግድ ስርዓት ለመታገዷ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። 

አጎዋ (የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ) ምንድን ነው?

በግርድፍ ትርጉሙ የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ ወይም አጎዋ (The African Growth and Opportunity Act) በአሜሪካ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉና ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ዕድል ወይም ችሮታ ነው።

አጎዋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በግንቦት 18/2000 በአሜሪካ ኮንግረንስ ፀድቆ የተጀመረ ነው። ይህ የንግድ ዕድል ሥርዓት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2000 እስከ 2008 እንዲተገበር ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ እስከ 2015 እንዲራዘም ማድረጋቸው ይታወሳል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2000 ላይ ይፋ በተደረገው የቀረጥ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ 38 የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለሁለት አስርት ዓመታት የተለያዩ ምርቶችን (በስፋት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን) ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ለመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በአሜሪካው መሪ በጆ ባይደን አስተዳደር በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች በኋላ ከአጎዋ ዕድል ተሰርዛለች። በኢትዮጵያ ያለው ችግር አሳሳቢ እንደሆነ የምትገልጸው አሜሪካ አገሪቱ በ60 ቀናት ውስጥ የሚጠበቅባትን ቅደመ ሁኔታዎች የምታከናውን ከሆነ ወደ አጎዋ ዳግም ልትመለስ እንደምትችል አስታውቃ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ መሰረት በአጎዋ ዕድል አማካኝነት ኢትዮጵያ ለ200 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ይገልፃል። የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ተጠቃሚዎች 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርተው ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች መካከል አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ዋነኞቹ ናቸው። የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከ30 ሺህ በላይ ሠራተኞች በመያዝ ቀዳሚ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ከአስር ወራት በፊት የተነጠቀችው የአጎዋ ዕድል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ያገኙ ዜጎች ላይ ጫና በማሳረፉ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማስከተሉም ባሻገር በጦርነት፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሌሎችም ምክንያቶች የተፈተነ ላለው ምጣኔ ሀብቷ ተጨማሪ መሰናክል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አስተያየት