ነሐሴ 24 ፣ 2014

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመኖሪያ ፈቃድ ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች እየተንገላቱ መሆኑ ታወቀ

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ስደተኞቹ ሱዳን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም “ዲፕሎማሲያችን የተበላሸ በመሆኑ ምንም ማድረግ አንችልም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመኖሪያ ፈቃድ ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች እየተንገላቱ መሆኑ ታወቀ
Camera Icon

ፎቶ፡ ከስደተኞቹ ለአዲስ ዘይቤ ከተላኩ ፎቶዎች

በሱዳን በተለይም በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች እንግልት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀምብን ነው ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸውን ገለፁ።

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦችም ከፀጥታ አካላቱ ጋር ይመሳጠራሉ በሚል ስጋት ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ እና በሰሜናዊ ሱዳን በካርቱም ኦምዱርማን በተባለች ከተማ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀው “የፀጥታ ኃይሎቹ ምክንያት ህገ ወጥ ስደተኞች ናችሁ የሚል ነው። ነገር ግን እኔ በምኖርበት ከተማ እንኳን ከግብፅ፣ ቻድ፣ ኤርትራና ሌሎችም ሀገራት የመጡ በርካታ ህገ ወጥ ስደተኞች ቢኖሩም ጭካኔያቸው በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ የበረታ ነው” ብሏል።

ህገ ወጥ ስደተኛ የሚባሉት በድንበር በኩል ወደ ሀገሪቱ የገቡ እና የመኖሪያ ፈቃድ (በሱዳን/ በአረብኛ- ኢቃማ) የሚባለውን ያልያዙ ናቸው። የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ፓስፖርት ቢያስፈልግም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፓስፖርት ጥያቄን በፍጥነት ማስተናገድ አልቻለም ሲሉ ዜጎቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

“አሁን አንተን እያናገርኩ ካለበት ከአምስት ደቂቃ በፊት በሁለት አይሱዙ ሙሉ ኢትዮጵያዊያን ከአንድ እንደ ክፍለ ከተማ ካለ ቦታ መወሰዳቸውን ሰምቻለሁ። እኔ በግል የማውቃቸው ሶስት አራት ሰዎችም ታስረዋል” ሲል የኦምዱርማን ነዋሪው ሁኔታውን አስረድቷል።

ከዚህ ቀደም ለሱዳን ኢሚግሬሽን አሻራ መስጠት አለባችሁ ተብሎ አሻራ ቢሰጥም ከአሁኑ እንግልት አልታደገንም የሚሉት ዜጎች “የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፓስፖርት የሚያስከፍለው ነገር ካለ እስካሁን አናውቅም ነገር ግን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሱዳን ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ከ400 እስከ 800 ዶላር ክፍያ ይጠይቃል” ብለዋል። 

ከኤምባሲው በታች ሆነው በየአካባቢው ከሚገኙ ኮሚዩኒቲ መስሪያ ቤቶችም ጊዜያዊ መታወቂያ አውጡና ፓስፖርት ከኤምባሲው ትወስዳላችሁ ቢባልም “ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ የሱዳን ፓውንድ (ከ550 እስከ 700 ብር ገደማ) ክፍያ ይጠየቃል፤ ከዚያ ሲያልፍም በሙስና ካልሆነ መስተናገድ ከባድ ሆኗል” ሲል ካርቱም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል። ለአዲስ ዘይቤ ሃሳቡን ያካፈለ አንድ ስደተኛ ለኤምባሲው የፓስፖርት ጥያቄ ካቀረበ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ማለፉን ገልጿል።

“ኢትዮጵያውያን ታስረው የት እንደሚወሰዱ እንኳን አናውቅም፤ ሴቶች እስር ቤት ይታጎራሉ። እዚያ ምን እንደሚሆኑ አናውቅም። የትኛው እስር ቤት እንደሚወሰዱ ስለማናውቅ መጠየቅም አልተቻለም። የፀጥታ አካላቶቹም ቢሆኑ ዝርፊያ የሚፈፅሙ ሲሆን ጉቦ ተቀብለውና ስልኮች ቀምተው የሚለቁም አሉ” ሲሉ ስደተኞቹ ስጋታቸውን አጋርተዋል። 

በስፋት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ነው የተባለው እስር እና “አፈሳ” ከአንድ ወር በፊት የጀመረ ቢሆንም ከትላንት ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እጅግ ተባብሷል። “ከሁሉም በላይ የእኛ ፍላጎት ሰብዓዊ መብታችን ቢያንስ እንዲከበር ኤምባሲው ስራ እንዲሰራ ነው። የፀጥታ ኃይሎች የተያዙ እስረኞችን 200 የሱዳን ፓውንድ (ከ18 ብር በላይ) ያለምንም ደረሰኝ ጉቦ በሚመስል መልኩ ያስከፍላሉ፤ እንደዚያም ሆኖ በድጋሚ ተይዘህ በተመሳሳይ ሁኔታ ክፍያ ትጠየቃለህ” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ስደተኞቹ ያስረዳሉ። 

አዲስ ዘይቤ በሱዳን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያኑ “ለኤምባሲው ጥያቄ ስታቀርቡ የተሰጣችሁ ምላሽ ምንድን ነው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ዲፕሎማሲያችን ስለተበላሸ ምንም ማድረግ አንችልም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም አብዛኛው ዜጋ በስፋት የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ባለመሆኑ ብሶታቸው ሰሚ ማግኘት እንዳልቻለና ለሚያውቋቸው የሚድያ ሰዎች መረጃዎችን ቢልኩም ሽፋን ማግኘት አለመቻላቸውን በመግለፅ የተሰማቸውን ቅሬታ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ለአዲስ ዘይቤ አካፍለዋል።

በአሁኑ ወቅት በደህንነት ምክንያትም ድንበር በመዘጋቱ እንጂ በመተማ በኩል በእግራቸው ለመመለስ የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

አስተያየት