ነሐሴ 24 ፣ 2014

ከከተማዋ ሶስት እጥፍ የሚበልጠው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና

City: Dire Dawaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ 300 ሰራተኞች ይዞ ስራ የጀመረው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በቀን እስከ 35 መኪኖችን አምርቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከከተማዋ ሶስት እጥፍ የሚበልጠው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና
Camera Icon

ፎቶ፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት (የምስራቅ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አንድ አካል የሆነው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ማዕከል ምረቃ)

የንግድና የኢንዱስተሪ ማዕከል የነበረችው ድሬዳዋ የቀድሞ ስሟን የሚያድስ መልካም ዜና ስምታለች። አጠቃላይ ስፋቱ 4 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ደረቅ ወደብን አጠቃሎ የያዘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና ፕሮጀክት በ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በጀት እየተገነባ ይገኛል። 

በስፋቱ የድሬዳዋ ከተማን በሶስት እጥፍ የሚበልጠው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ ምርቶች የሚራገፉበት፣ የሚስተናገዱበት ወይም የሚገጣጠሙበት እና ወደ ውጭ እንደገና የሚላኩበት ሲሆን ለኢንዱስትሪ ፓርክ በግብዓትነት የሚሆኑ ምርቶች የሚዘጋጁበት ማዕከል ነው። 

“የነፃ የንግድ ቀጠናው ዋነኛው መነሻው ከታሪፍ ነፃ የንግድ ልውውጥ በማድረግ በጎረቤት ሀገሮች መካከል ውድድርን የሚያበረታታ የንግድ መስመር መዘርጋት ነው። ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የስራ እድሎችን በመፍጠር የስራ አጥ ቁጥርን ይቀንሳል። ከሀገር ውስጥም ከውጪም ከተለያዩ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የተለያዩ ምርቶች የሚገበያዩበት ማዕከል ስለሚሆን ይህን ተከትሎ የሚመጣ የኢንቨስትመንት ፍሰት ይጨምራል” የሚሉት ድግሞ ዶ/ር ሙሉጌታ ግርማ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የገበያ ጥናት (የማርኬቲንግ ማኔጅመንት) መምህርና ተመራማሪ ናቸው። 

ታዲያ ይህን ግዙፍ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ከኢትዮጵያ ጋር ለማስተሳሰር የተመረጠችው ከተማ ድሬዳዋ ነች። ይህን ለማስተግበር በድሬዳዋ ከፍተኛ የሆነ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ መንደር ያላት፣ የባቡር፣ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን አጣምራ የያዘች ከተማ መሆኗ ለዚህ የንግድ ማዕከልነት እንድትመረጥ አድርጓታል።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በአለም ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲሆን 55 የአፍሪካ ህብረት አገራትን እና 8 ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦችን ያካተተ ሲሆን ከጥር 29 እስከ 30/2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባካሔደው 18ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና የመመስረት ስምምነትን አፅድቋል። የአፍሪካ ሀራትም ነፃ የንግድ ቀጠናን በሚመሰርቱበት ጊዜ ይህንን ስምምነት መሰረት በማድረግ እንደሆነ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ አለም አቀፍ ፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሱራፌል ጌታሁን ይገልጻሉ።

ከአዲስ ዘይቤ የድሬዳዋ ሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ሙሉጌታ ግርማ ኃሳባቸውን በመቀጠል “የታክስ ጥቅሙ በቀጥታ ለፌደራል መንግስት ገቢ የሚሆን ቢሆንም፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተካፋይነት ድርሻ ሊኖረው የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ከሚፈጠረው የስራ እድል እና ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ የተለያዩ አካልት በግላቸው ከሚጀምሩት የንግድ ስራ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ” ሲሉ ይገልጻሉ። 

ነፃ የንግድ ቀጠናው ለድሬዳዋ እድገት ያለውን ድርሻ በተመለከተ ዶ/ር ሙሉጌታ ሲናገሩ “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በኮንስትራክሽን ግብዓት ምርቶች ላይ በስፋት ይሰራል ተብሎ ስለሚጠበቅ አሁን ላይ ያለውን የተዛባውን የንግድ ስርዓት መልክ ያስይዛል። በኢንዱስትሪዎች መካከል ፉክክር እንዲኖር በማድረግ በጥቂቶች የተያዘውን ገበያ ወደ ተፎካካሪ የገበያ ስርዓት በመቀየር ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ ይኖረዋል” በማለት ያስረዳሉ።

ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ እንደትሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘትም ሆነ ለመስጠት የተቀላጠፈ አሰራር እንዲሁም የተሟላ መሰረተ ልማት መኖር እንዳለበትና  በተጨማሪም በአካባቢው ላይ ሊነሱ የሚችሉ የፀጥታ ስጋቶችን ቀድሞ የመለየትና መቆጣጠር እንደሚገባ ዶ/ር ሙሉጌታ ያሳስባሉ “የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንደዚህ አይነት ትልልቅ ፕሮጀክቶች አይደረጉም። ሌላው በአስተዳደሩ ሊታሰብበት የሚገባው የመሰረተ ልማቶች ጉዳይ ነው። ነፃ የንግድ ቀጠና ስራውን ለማቀላጠፍ የተሟላ መሰረተ ልማት ሊኖር ይገባል” ሲሉ ገልፀዋል።

በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አንቀፅ አምስት ላይ አባል ሀገራት ማሟላትና ማድረግ ስላሉባቸው ጉዳዮች በግልፅ ተቀምጧል። እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሱራፌል አስተያየት በስምምነቱ ከተደነገጉ ኃላፊነቶች አንዱና ዋነኛው በአባል ሀገራት መካከል ግልፅነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ተመጣጣኝ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ማድረግ ነው።

በዚህ ሀገራዊ እና አህጉራዊ የንግድ ግንኙነት ውስጥ የውጭ ሀገር ምርቶች መዳረሻ የምትሆነው ድሬዳዋ፤ በሀገር ውስጥ የተመረተ ማንኛውም ምርት ተጓጉዞ ወደ ድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ይመጣል። ከዚያም በባቡር፣ በአየር ወይም በመኪና ለውጭ ገበያ ይላካል። በዚህ እንቅስቃሴ ከግንባታው ጀምሮ ምርት በማምረት ብሎም በማጓጓዝ ሂደት ውስጥ ለብዙ ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ነፃ የንግድ ቀጣናው ለከተማዋ እድገት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ የፓናል ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የሙከራ ፕሮጀክት በፍጥነት ወደ ስራ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል። “በኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የዓለም አቀፍ ንግዱን ለማሳለጥ በመሰራት ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሎጂስቲክ ምክር ቤት በፕሮግራም ደረጃ ፀድቋል” ብለዋል። 

ሚኒስትሯ በንግግራቸው በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች አጠቃላይ ንግድ፣ ሁሉን አቀፍ የሎጂስቲክ አገልግሎትና የአምራች ዘርፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም በጎረቤት ሀገራት እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያዊ ነጋዴዎችንና ሌሎችንም በመሳብ ወደ ነፃ ንግድ ቀጠናው ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተው ኢንዱስትሪው ለከተሞች ዕድገት፣ ለስራ እድል መስፋፋት፣ ለኑሮ ውድነት መቀነስ እና ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ነሃሴ 8/2014 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ድሬዳዋ ተገኝተው ነፃ የንግድ ቀጠናውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባለሀብቶች በድሬዳዋ በተገነባው ነፃ የንግድ ቀጠና በመሳተፍ ራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ነፃ የንግድ ቀጠናው ትንሿን ኢትዮጵያ የሚፈጥር ነው። ድሬዳዋ ባቡርንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለማስገባት የመጀመሪያ ነች። ዛሬም ትንሿን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ታድላለች" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ድሬዳዋ የኢትዮጵያ ጁቡቲ ምድር ባቡር ዝርጋታን ተከትሎ ተመስርታ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራ ፤ በኋላም የድሬዳዋ ሲሚንቶ፣ የኮካኮላ ፋብሪካ፣ የድሬዳዋ ምግብ ኮምፕሌክስ እና የሌሎች የምርት ተቋማት መቋቋም ድሬዳዋን የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገዋት ቆይተዋል።

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በፈር ቀዳጅ ኢንዱትሪነት 'ኤል አውቶ' ኢንጂነሪንግ የተባለ ኩባንያ በቀጠናው በ700 ሚሊዮን ብር ያስገነባው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ነሐሴ 14 ቀን 2014 ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

ፋብሪካው በቀን እስከ 35 መኪናዎች በመገጣጠም ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ለሀገር ዕድገት የድርሻውን ይወጣል ተብሏል። ይህ የመኪና መገጣጠሚያ ለ 300 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ 

የኤል አውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ቶኩቻ አለማየሁ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ምርቶችን በጅቡቲ ነፃ የንግድ ቀጠና በኩል ገቢና ወጪ ስታደርግ እንደነበር እና ነፃ የንግድ ቀጠናው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እቃዎች ምንም አይነት የጉምሩክ ታክስና ሌሎች ስነስርዓቶች ሳይፈጸምባቸው አስመጪዎች በቀጥታ ከተመረተበት አገር የሚያስገቡበት ወደብ መሆኑን ተናግረዋል።

አስመጪዎች ያስገቡትን ጥሬ እቃም ሆነ ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሚፈልጉበት ቦታም ሆነ ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር አጓጉዘው ለመሸጥ እንደሚያስችላቸው በመጠቆም በቀጣይም ነጻ የንግድ ቀጠናውን ለማጠናከር ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሰፊ መሬት በመረከብ የማስፋፊያ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈፃሚው ዋል። 

በተጨማሪም አቶ ሲራጅ አብዱላሂ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በምስራቅ አፍሪካ ሊተገበር የታሰበውን ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ በማገዝ የቀጠናውን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ያጠናክራል” ብለዋል። 

ቀደም ሲል በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ዶ/ር አርከበ እቁባይ እና አቶ ታፈረ ተስፋቸው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪ ሆነው መሾማቸውን አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል።

አስተያየት