ብራ፡ የአዲስ ዓመት አቀባበል በኦሮሞ ባህል

Avatar: Naol Getachew
ናኦል ጌታቸውጳጉሜ 1 ፣ 2013
City: Addis Ababaባህል ሙዚቃ
ብራ፡ የአዲስ ዓመት አቀባበል በኦሮሞ ባህል
Camera Icon

Photo: Team of shinoye

ለአዲስ አመት ብስራትና ድምቀት ከተሰሩ የተለያዩ ዘፈኖች አንዱ የስመ ጥሯ የኦሮምኛ ድምፃዊ እቴነሽ ግርማ “እንቁጣጣ ሺኖዬ” ተጠቃሽ ነው። በዚህ ዘፈን በአዲሱ ዘመን መግቢያ ላይ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሴቶች ስለሚጫወቱት የሺኖዬ ጨዋታ ታዜማለች። ታዋቂዎቹ ስንኞችም፡-

“Inquxaaxa shinoo ya shinooyyee

Qammee yaa masqalooyyee”

(እንቁጣጣ ሺኖ ያ ሺኖዬ

መስከረም ያ መስቀሎዬ)

ይህ ፅሁፍም በብራ ወቅት የኦሮሞ ሴቶች ስለሚጫወቱት ጨዋታ እና ስለሚከዉኗቸዉ ባህላዊ ስርዓት ይዳስሳል።

ወቅቱ የክረምት ጊዜ እያለቀ ወደ ፅጌ መሻገሪያ ላይ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ በዓላት እንደሚከበሩ ይታወቃል። እንደአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሁሉ የአዲስ ዘመን መጥባት በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራና ተወዳጅ የአከባበር ለዛ አለው።

ኦሮሞ የራሱ የሆነ የገዳ አስተዳደር ስርዓት፣ ሃይማኖት፣ ትውፊት፣ የተፈጥሮ ሐብት፣ ባህል እንዲሁም ከዋክብትንና ጨረቃን የተከተለ የዘመን አቆጣጠር ያለው ሕዝብ እንደሆነ ድርቢ ደምሴ “የኦሮሞ ማንነት ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው ይናገራሉ። ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ “GADA” በተሰኘው መፅሐፍ ላይ ስለ ዘመን መቁጠሪያው ሲፅፉ “ካላንደሩ የገዳ ስርዓት ምንጭ የሆነ ትልቅ ግኝት ነው። ይህም ሕይወታቸውን ፣ እምነታቸውን ፣ ባህላዊ ስርዓታቸውን፣ ፖለቲካቸውንና ኢኮኖሚያቸውን በከፍተኛ ደረጃ ሰድረው እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።” ይላሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ የጨረቃን ስርዓት በሚከተለው የዘመን አቆጣጠር ቀመር አንድ ወር 29.5 ቀናትን ይይዛል። አመቱም 354 ቀናትን በያዙ ጪካዋ ፣ ሳዳሳ ፣ አብራሳ፣  አማጂ ፣ ጉራንዳላ፣ ቢቶቴሳ፣ ጫምሳ ፣ ቡፋ፣ ዋጣባጂ፣ ኦቦራ፣ ዲካ እና ብራ የተባሉ 12 ወራት የተከፋፈለ ነው። 

ብራ

የኦሮሞ ማህበረሰብ የፀደይ መምጣትን ሲያበስር “ብራን በሪኤ” ይላል። መስከረም ጠባ ፣ አዲስ ዘመን መጣ ፣ ጭጋጉ አልፎ ብራ ገባ እንደማለት ነው። ወንዞች ስለሚጎድሉ የተነፋፈቀ ይጠያየቃል፤ ይሰባሰባል፤ ልጆች ይጫወታሉ፤ ወጣቶች ያጌጣሉ።

ዋጣባጂ፣ኦቦራ እና ዲካ የተባሉት (ወይም አሁን በስራ ላይ ላይ ባለው ካላንደር ዋጣባጂ ፣ አዶሌሳ እና ሃገያ ተብለው የሚጠሩት) ሶስት ወራት እንዳበለቁ ብራ የተባለው ወር ይተካል። በነዚህ ወራት ከሌሎቹ ወቅቶች በተለየ መልኩ የረዘመ የክረምት ጊዜ በመሆኑ ምክንያት የወንዞች መሙላት ዘመድ አዝማድ እንዳይገናኝ ያደርጋል። ድባቡም ጨፍጋጋና ረግረግ የበዛበት ይሆናል። የክረምቱ ወራት አልፎ ብራ ሲመጣ ዝናቡ ጋብ ይላል፤ አበቦችም ፈክተው መስኩን እንደ ስጋጃ ያለብሱታል።  

ኢንጊጫ/ ሺኖዬ

ይህ የአከባበር ስርዓት በሰላሌ አካባቢ “ቡቂሳ” በሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች ደግሞ ኢንግጫ ፣ ቁኒ ፣ ሺኖዬ ፣ ቁኒ ዳርባ ፣ ኢኢሊ ቡቂፈቹ እየተባለ ይጠራል። በየዓመቱ ልጃገረዶችና ያላገቡ ሴቶች ተሰብስበው ሁሉም ተውበው ዓደይ አበባን ወይም ቁኒ የሚባለውን ቄጤማ በመንቀል/በመቀንጠስና “የሺኖዬን ጨዋታ” በየጎረቤቶችና በየዘመዶች ቤት በመዞር የሚዘፍኑበት ነው።

“እኔ ባደኩበት የሰላሌ ኦሮሞ ባህል በበዓሉ ዋዜማ ሳይነጋ በጠዋት ቁኒ ለመቀንጠስ ወደ መስክ እንሄዳለን።” ይላሉ አዴ እመቤት ቶሎሳ። ወንድ ወጣቶች ደግሞ ለበአሉ ስጦታ የሚሰጧትን ሴት ለመመምረጥ ሽመላቸውን ይዘው ሴቶቹ አበቦችን ወደሚቀነጠሱበት እንደሚሄዱ ይናገራሉ። አዴ እመቤት እንደሚሉት በበዓሉ ላይ ሴቶች ከረሜላን ለወንዶቹ ሲሰጡ ወንዶች ደግሞ ሽቶን እንደስጦታ ይሰጧቸዋል።

በእቴነሽ ግርማ ‹‹እንቁጣጣ ሽኖዬ›› ዘፈን ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች እናገኛለን፡-

Buqqisaa Buqqifanna

Kunoo geenye barana

Heerumte Gurgudooni

Xixinnoo guddifanna

(ቄጤማ እንቀንጥስ

ይኸው ዘንድሮ ደረስን

ትልልቆች ስላገቡ

ትንንሾችን እናድርስ)

በዋዜማው የቀነጠሱትን ቄጤማ ወደቤት ይዘው በመሄድ እንደሹሩባ አድርገው ይጎነጉኑታል። ይህ የተሾረበው ሳርም “ኢንግጫ” ተብሎ ይጠራል። ልጃገረዶቹ በበዓሉ ቀን በየቤቱ እየዞሩ የተለያዩ ግጥሞችን እየተጫወቱ በሚዘፍኑበት ጊዜ ጉንጉኑን ሳር (ኢንጊጫውን) በየደረሱበት ቤት አምድ (ኡቱባ) ላይ ወይም ደግሞ በሩ ላይ ያስሩላቸዋል። አልያም ለቤቱ እመቤት በእጅ ይሰጣሉ። በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤቶችም የተለያዩ ግብዣ ያደርጉላቸዋል። ቂቤ ቀብተው፣ እርጎ አጠጥተው፣ ምግብ አብልተውና ምርቃቶችን ሰጥተው ይሸኟቸዋል ይላል አብዱልባሲጥ አብዱሰመድ

በርግጥ ይህ ባህል እንደአብዛኞቹ የኢትዮጵያ የበዓል ጨዋታዎች ለጨፋሪዎቹ እንደቀደመው ጊዜ ከመስጠት ይልቅ ገንዘብ ወደ መስጠት ተቀይሯል ።

ሻለቃ እቴነሽ ትቀጥልና፡-

Yaa shinoo yaa shinoyyee

Qaammee kan sirbuuf hawwe

Ayyaanni waggaa haaraa

Kunoo dhufe nan hawe

(ያ ሺኖ ያ ሺኖዬ

መስከረም ልዘፍን የተመኘሁት

ያዲስ ዓመት በዓል

ይኸው መጣ እንደተመኘሁት)

“በዓሉ ሴቶች ከማህበረሰቡም ሆነ ከባህል የሚደርስባቸውን ጫና በግጥምና ዜማ እያዋዙ የሚገልፁበትና ልጃገረዶቹም እርስ በእርስ የሚሞጋገሱበት ቀን ነው” ይላሉ የአፋን ኦሮሞ ፎክሎር መምህሩ ቁልቁሎ ኢጆ። ቀደም ባለው ጊዜ ወላጆች ሴቶችን ያለፍቃዳቸው ይድሯቸው ስለነበር ሴቶቹ ይህንን የነፃነት ቀን በመጠቀም ወላጆቻቸው ላይ ያላቸውን ቅያሜ እንዲህ በግጥም ይገልጻሉ፡-

Yaa muraa shunkurtii,

Birriit caala jettee haati ilmoo gurgurtii

Baddaa baddaa jedhuu, guggubataa kanaa

Abbaa abbaa jedhuu, gurgurataa kanaa

(የሽንኩርት ክፋይ መላ

እናት ልጇን ሸጠች - ብር ይበልጣል ብላ

ደጋ ነው ይላሉ - ይህን ያረረውን

አባት ነው ይላሉ - ልጅ የሚሸጠውን)

ይህንን የሴት መብት ትግል ምንጭ (The origins of Feminism Movement)  አደርገን መውሰድ እንችላለን ይላሉ ቁልቁሎ።

በኢንግጫ ቀን እንኳን ሰው እንስሳም መጥገብ አለበት። ለዚህም ሲባል ለተወሰኑ ጊዜያት የመስክ እርሻውን ምክንያት በማድረግ ወደ መስክ ወጥተው ግጦሽ እንዳይሰማሩ የሚደረጉት ከብቶች በዚህ ቀን ይለቀቃሉ። ይህ ቀን ሁሉም የሚጠግቡበት እንደመሆኑ አባወራው ኩታውን ደርቦ ከብቶችን ወደ መስክ ያሰማራቸዋል። አመሻሹን ወደ ቤት ሲመለሱም ዳቦ ይቆረሳል። ቤተሰብ ተሰብስቦ የተወቀጠ ኑግ ይመገባል፣ ጠላ ይጠጣል። ለዚህም ቢያንስ ከወር አስቀድሞ ዝግጅት ይጀመራል ይላል የፍቼ ከተማ ነዋሪው አቦምሳ ለማ። ከምግቡ በኃላም ወንዶች ወጥተው በኦሮምኛ ‹‹ዳሞቲ›› የሚባለውን ችቦ ያበራሉ።

ሐዊኔት ቦጃ ባህላዊ አከባበሩ በየዘመኑ እየቀዘቀዘ በመምጣቱ “Ilaa mee ijoolle aadaa keeyna bada jiru haa deebisnu - Shinooyyeen Aadaa keenya” (እየጠፋ ያለውን ባህላችን እንመልስ - ሺኖዬ ባህላችን ነው) የሚል በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ስለሺኖዬ ለማሳወቅ እንቅስቃሴ አድርገናል ትላለች። ስምንት በመሆን በሰላሌ ሴቶች ባህላዊ ልብስ “ሻማ ቡሬ” በማጌጥ በመስክ ላይ ቄጤማ በመያዝና የሽኖዬ ዘፈኖችን በመዝፈን ቪዲዮዎችንና ፎቶዎችን አጋርተዋል። “እንደ ሻደይ እና አሸንድዬ ትኩረት ስላልተሰጠው ለአንድ ሳምንት ያህል በየቤቱ እየዞርን በመጨፈር ባህሉን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን በምናገኘው ገንዘብ በገጠር ላሉ ልጃገረዶች ትምህርት እገዛ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ነው።” ትላለች የእንቅስቃሴው አባል ሐውኔት።

Image: Leila Qashu (2016)Toward an Understanding of Justice, Belief, and Women’s Rights: Ateetee, an Arsi Oromo Women’s Sung Dispute Resolution Process in Ethiopia.

አቴቴ ፋጫሱ

አቴቴ ሌላው “ብራ” ላይ ያገቡ ሴቶች የሚከውኑት የአዲስ ዓመት የበአል አከባበር ስርዓት ነው። መሰባሰባቸውን ፣ ስኬታቸውን ፣ አዲስ ዘመን መጨመሩን ወደ ዋቃ በሚደርስ ጸሎት፣ በባህላዊ ዝማሬዎች ፣ በምርቃትና ስጦታ መቀባበል የሚከበር እንደሆነ ሌኒን ኩቶ፣ አየሁ ባጫ እና ገመቹ ታዬ በጋራ በፃፉት ፅሁፍ ላይ ተጠቅሷል።

አቴቴ ፈጫሱ- ሲባል የቃሉ ትርጓሜ አቴቴን መዝራት ፣ መርጨት እንደማለት ነው። ያገቡት ሴቶች ንፁህ ቂቤን በማሰሮ ይዘው በእጃቸው በያዙት ለምለም ሳር ከቅቤው በመንከር  ሰዎችን ፣ ከብቶችንና ደመራ የሚደመርበትን ቦታ እየረጩ የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።

አቴቴ ዘፈን/ዝማሬ (ፋሩ) ነው። ለይላ ቃሹ ፒኤችዲ ማሟያ ጽሁፏ ግብዓት የተለያዩ የአርሲ አካባቢ ሰዎችን ስለ አቴቴ ቃለ መጠይቅ ባደረገች ጊዜ ያገኘችውን ምላሽ ስንመለከት አቴቴ ከዘፈን አይነጠልም። ብዙ አይነት አቴቴዎች ቢኖሩም ሴቶች ‹‹ረቢ እርዳን ፣ ዝናብን ደግሞ አዝንብልን ፣ ዝናብን ስለሰጠኸንም እናመሰግንሀለን እያልን የምናመሰግንበት ነው›› የሚሉ ምላሾችን ለይላ አግኝታለች።

Author: undefined undefined
ጦማሪናኦል ጌታቸው

Naol is a Journalist, who works as a fact-checker at HaqCheck, Addis Zeybe & its CSO partner Inform Africa. He is a graduate of French Literature and International Skills from Addis Ababa University.