ጳጉሜ 3 ፣ 2013

“ቀፊራ” እድሜ ጠገቡ የድሬዳዋ ገበያ

City: Dire Dawaባህል የአኗኗር ዘይቤታሪክማህበራዊ ጉዳዮች

የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገንደቆሬ፣ ሰኢዶ፣ ቀፊራ የሚባሉ ሦስት የመገበያያ ስፍራዎች አሏቸው። ከእነዚህም ውስጥ በድሬደዋና አካባቢዋ በቅርብ እርቀት ከሚገኙ ከተሞች የተሰባሰቡ ሻጭ እና ሸማቾች የሚገናኙበት ግዙፍ እድሜ ጠገብ የመገበያያ ሥፍራ..

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

“ቀፊራ” እድሜ ጠገቡ የድሬዳዋ ገበያ
Camera Icon

Photo Credit: https://tyitelle.wordpress.com/

የድሬዳዋ ነዋሪዎች ሳምንቱን ሙሉ የሚገበያዩባቸው ገንደቆሬ፣ ሰኢዶ፣ ቀፊራ የሚባሉ ሦስት የመገበያያ ስፍራዎች አሏቸው። ከእነዚህም ውስጥ በድሬደዋና አካባቢዋ በቅርብ እርቀት ከሚገኙ ከተሞች የተሰባሰቡ ሻጭ እና ሸማቾች የሚገናኙበት ግዙፍ እድሜ ጠገብ የመገበያያ ሥፍራ  ቀፊራ ነው። ቀፊራ ገበያ ከተመሰረተ 100 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገርለታል።

ድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሞያ አቶ ደረጀ ታደሰ ገበያው “ቀፊራ” የሚል ስያሜውን ያገኘው “ቀፊር” ከሚል የአረበኛ ቃል መሆኑን ነግረውናል። ቀፊር “ዘብ” የሚል አቻ ትርጓሜ አለው። እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ የገበያው ውጫዊ አጥር የአርመኖች የምህንድስና ጥበብ ውጤት ነው። ይህ የኪነ-ሕንፃ ጥበብ የተገነባው እኤአ 1942 ሲሆን ስድስት መግቢያዎች አሉት። የኪነ-ሕንፃ ግንባታው ከሀረር ጀጎል ግንብ ጋር የተቀራረበ ይዘት አለው። በቅርጽና በዓይነት ጀጎልን የሚመስለው ማራኪ ግንብ አንድ መቶ ዓመታትን እንዳስቆጠረ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። በድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም በቅርስነት የተመዘገበው “ቀፊራ” ማራኪ ዕይታ ያለው ነው።

ለከተማዋ የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው “ቀፊራ” የተለያየ ባህል፣ ሐይማኖት፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ሲያገበያይ የሁለት ትውልድ ዕድሜ ያህል ዘልቋል።

ቀፊራ በተለይ በበአላት መዳረሻ ቀናት ላይ በገዢ እና ሻጭ ትርምስ ይጨናነቃል። የግብይት ሂደቱ እንደደመቀ ከማለዳ እስከ ምሽት በሚዘልቅበት ቀፊራ ተፈልጎ የሚታጣ የሸቀጥ ዐይነት እንደሌለ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።  

አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ የእህል ዓይነቶች (የቅባት እህሎች፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣…)፣ በቆሎ እሸት፣ ኩድራ (የሽንኩርት አይነቶች፣ ቲማቲም ድንች…)፣ ከዛፍ የሚገኙ ጭሳጭሶች (ወይራ፣ ብክብካ…)፣ ከሰል፣ እንጨት፣ ባህር ዛፍ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ቅቤ  እና የመሳሰሉት በስፋት የሚገኙበት ሰፊ የገበያ ስፍራ ነው።

Photo Credit: Munib, https://twitter.com/munib3m

በማኅበራዊ ህይወት ተሳስረው፣ በኪሳራቸው ተዛዝነው፣ ከትርፋቸው ተካፍለው በጋራ መኖር ያውቁበታል የሚባልላቸው የቀፊራ ነጋዴዎች አብዛኞቹ የእድሜያቸውን ግማሽ ያሳለፉት እዚሁ ቀፊራ ውስጥ ነው። “ቀፊራ” ተወልደው፣ “ቀፊራ” አድገው፣ “ቀፊራ” ውስጥ በንግድ ሥራ የተሰማሩም ይገኛሉ።

ወ/ሮ ቅድስት ተፈራ የተባለች ቀፊራ ውስት በርበሬ ትነግዳለች። “ቀፊራን የማውቃት ከመወለዴ በፊት ነው” ትላለች። ይህንን ያለችው ነፍሰጡር እናቷ ከቀፊራ ውሎ መልስ እንደወለደቻት ስለነገረቻት ነው። ቅድስት ቀፊራ ውስጥ ስላለው ማኅበራዊ ህይወት ተናግራ አትጠግብም። “የውሸት ተጣልተን አናውቅም። ጸባችንም ፍቅራችንም የእውነት ነው። ሰው ነንና እንጋጫለን፤ እግርና እግርም ይጋጫል ይባል የለ? ቂም መያዝ ግን አናውቅበትም። ስንታረቅ ታረቅን ነው። እኔና ጎረቤቴ ከ30 ዓመታት በላይ አብረን ሰርተናል። አሁንም ፍቅር ነን” ስትል ሐሳቧን ገልጻልናለች።

“ቀፊራ በጅምላም ሆነ በችርቻሮ ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦች መገኛ በመሆኑ ሁሉም ይመርጠዋል” የምትለው ወ/ሮ በላይነሽ ተሾመ ለገበያ የሚቀርቡት ሸቀጦች ዐይነት እና ብዛት ብቻ ሳይሆን ገጠሩን ከከተሜው ማስተሳሰሩ የገበያው ተጨማሪ ድምቀት እንደሆነ ነግራናለች።

ፋጡማ ሰኢድ በቀፊራ ውስጥ ቅመማ ቅመም ነጋዴ ነች። ቀፊራ ያለው የሌለውን የሚያግዝበት፣ የበረታው የደከመውን የሚያበረታታበት፣ ደስታና ሐዘናቸውን ተካፍለው የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈ የራሱ ማኅበረሰብ ያለው ነው ትላለች። “ቀፊራ ውስጥ ኪሳራ አለ እንጂ የሚከስር ሰው የለም” ብላናለች።

ልሸምት ብሎ ከቀፊራ ጎራ ያለ ጥርሱን ሳይከድን ከጨዋታው ቀምሶ፣ ከገበያው አዳርሶ ነው ወደቤቱ የሚመለሰው ስትል የገለፀችው ቀፊራ የወር አስቤዛ ልትገዛ መጥታ ያገኘናት ወ/ሮ ፈቲሀ ቃሲም ናት። በወር አንድ ጊዜ እዚህ ሳትረግጥ እንደማትቀር ትናገራለች። እንደ ወ/ሮ ፈቲሀ ገለፃ አብዛኛው የድሬደዋ ነዋሪ ቋሚ የመገናኛ ስፍራው ቀፊራ እንደሆነና በወር ሁለት ሦስቴ እንደሚመጣ እና በየሰፈሩ የሚገኙ ጉልት ቸርቻሪዎች ከቀፊራ እየሸመቱ እንደሚቸረችሩ ገልፃልች።

“መስተንግዷቸው ልዩ ነው ጨዋታ አዋቂዎቹ የቀፊራ ነጋዴዎች” የምትለው ወ/ሮ ብርሀኔ መኮንን “የቋንቋ ልዩነት መኖሩ ከመግባባት ሳይገድበን በምልክትም ቢሆን ተግባብተን ልክ የረጅም ዓመት ትውውቅ እንዳለው ሰው ተሳስቀን ተጨዋውተን እንለያያለን” ትላለች። ወ/ሮ ብርሀኔ ከአማርኛ ቋንቋ ብቻ ውጭ የምትሰማውና የምትናገረው የሐገር ውስጥ ቋንቋ ባይኖርም ከኦሮምኛ እና ከሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዴዎች ጋር ያለቋንቋ ተግባበብታ የፍላጎቷን ሸምታ እንደምትመስ ገልፃለች። የዚህን ምክንያት ስታስረዳ “ነጋዴዎቹ የመገበያየት ጥበብ የገባቸውና ፍቅርን የተሞሉ ስለሆኑ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥታለች።

የቀፊራ ነጋዴዎች በስድስቱ ትልልቅ በሮች በሚያስገባው ገበያ የየራሳቸው ቦታ (መደብ) አላቸው። የግብይት ሂደቱ ሲጠናቀቅ እቃቸው ተሸምኖ በሚገባ ታስሮ ይቀመጣል። በር የሌለው ሱቅ ያላቸው የኩድራ ነጋዴዎች የሚበዙ ቢሆንም “እቃዬ ይዘረፍ ይሆን” የሚል ስጋት የለባቸውም።

የቀፊራ ሽንኩርት ነጋዴ የሆነችው ወ/ሮ መፍቱሀ አሊ እንደሚሉት ከበሮቹ ውጪ ከውስጠኛዎቹ ያልተናነሰ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች ይገኛሉ። ቦታቸውን ለመለየት  ቀጭን እንጨት ይተክላሉ። በቀላሉ የሚነቀለው ድንበር መለያ እንጨት የጸብ መንስኤ ሆኖ እንደማያውቅም መስክረዋል።

አስተያየት