“ኃይለማርያም ማሞ
ሰው አይድንም ታሞ”
ተብሎ የችግሩ ጥልቀት በአንድ ወቅት በስንኝ ቋጠሮ የተገለጸለት የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከሁለት ዓመት በፊት የድንገተኛ ህክምና አገልግሎቱን የሚሰጥበትን ህንጻ ቢቀይርም አገልግሎቱ ግን ከጥንቱ ፈቅ ሳይል ከርሟል።
እንደ ጅማ፣ አምቦ፣ ነቀምት እና ሌሎች ከተሞች በጥቂቱ ሁለት የመንግሥት ሆስፒታል ይኖራቸዋል። ለአራት መቶ ሺዎች መኖሪያ የሆነችው አዳማ የሪፈራልም ሆነ አጠቃላይ ህክምናውን እየሰጠ የሚገኘው የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ነው።
በሪፈራል ስርዓቱ ከሚመጡ ታካሚዎች በተቃራኒው የተሻለ ህክምና ፍለጋ ብዙዎች በራሳቸው (Self Referring) ወደ ተቋሙ ይሄዳሉ።
ተቋሙ በታለመለት ልክ በየቀኑ እስከ 90 ድንገተኛ ታካሚዎችን ባስ ሲልም ከዚህም እጥፍ ታካሚዎችን ያስተናግዳል።
በእናቷ ድንገተኛ ህመም ክፍሉን የጎበኘችው ወጣት ሃያት አህመድ የጤና ባለሞያዎቹን ስትገልጽ “የሰው ነብስ የማይጨንቃቸው ናቸው” ትላለች። ከድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች እስከ ሀኪሞች ድረስ እጅግ አስቸጋሪ ስነ-ምግባር እንዳላቸውና እንደተማረረች ትናገራለች። እንደ ወጣት ሃያት አባባል በመግቢያ በር ላይ የአስታማሚ መግቢያም ሆነ ሌላ ስርዓት ባለመኖሩ መድኃኒት ለመግዛት ወጥቶ ለመግባት የጥበቃ ሰራተኞቹ የሚደርሱት እንግልት በቀላል የሚታይ አይደለም። ምንም ዓይነት የመድኃኒት እና የአላቂ የንጽህና እቃዎች አቅርቦት ለተጠቃሚዎች አይቀርብም። የህክምና ባለሞያዎች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ከአስታማሚ የእጅ ጓንት እየተቀበሉ ሥራቸውን ይሰራሉ።
ከዚህ ቀደም የህክምና መገልገያዎች ከሚያቀርቡለት እንደ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ እና ቢፍቱ አዱኛ እቃዎቹን ባለማግኘቱ እንዲሁም በጨረታ የሚያቀርብ ባለመገኘቱ ተቋሙ ተጠቃሚዎች ገዝተው ያቅርቡ የሚል አቅጣጫ አስቀምጧል። ሆስፒታሉ ማቅረብ ያልቻላቸውን ቁሳቁሶች ቅጥር ጊቢው ውስጥ የሚገኝ መድኃኒት ቤት ለሽያጭ ያቀርበዋል።
“ሁሉንም ነገር ዶክተሮቹ ከሚጠቀሙበት የእጅ ጓንት አንስቶ እኛ ነን ገዝተን ምናመጣው። አንድ ጓንት 10 ብር ነው። በዕለቱ የሚያስፈልገው 10 ቢሆን 100 ብር ይሆናል” ያለችን ባለቤቷን ስታስታምም ያገኘናት አዳማ ዙሪያ የጠዴ ኗሪዋ ወ/ሮ ስምረት ግርማ ናት። ወጪው እጅግ ከፍተኛ እንደሆነና ባለቤቷ የአደጋ ኢንሹራንስ ባይኖረው እንደማትችለው ትናገራለች። ታማሚዎች ከእጅ ጓንት በተጨማሪ ለድንገተኛ ህክምና የሚያገለግሉ መድኃኒቶች፣ ስሪንጅ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ገዝተው እንዲያቀርቡ እንደሚገደዱ፤ ይህንን ያላሟላ ተገልጋይ አገልግሎቱን ማግኘት እንደማይችል የአዳማው ሪፖርተራችን ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው ተገልጋዮች ተረድቷል።
በብቸኛው ሪፈራል ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ክንውኖች የነጻ ህክምናውን በክፍያ እንዲሆን ያደርጋሉ፣ ተጠቃሚዎችን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋሉ የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል። በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ እንዲሰጡ የተጠየቁት አብዛኛዎቹ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለቃለመጠይቅ ፈቃደኛ አልሆኑም። ለዚህም “የደህንነት ስጋት አለብን›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከስድብ እና ማንጓጠጥ በዘለለ የተደበደቡ እና በጩቤ የተወጉ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ የማይባል እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተሮች፣ ነርሶችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ስማቸው እና የሥራ ክፍላቸውን እንድንደብቅላቸው ጠይቀውናል።
ስሜ አይጠቀስ ካሉን የተቋሙ ሰራተኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ወጣት “ችግሩ የሚጀምረው ከመግቢያው በር ነው” ይላል። “ሆስፒታላችን በሌሎች የሕክምና ተቋማት እንደሚደረገው በፖሊስ ኃይል የሚደገፍ ጥበቃ አይደረግለትም። ይህ ቀዳሚው ችግር ነው። ከሚፈቀደው በላይ አስታማሚ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ የሕክምና ባለሙያዎችን በማዋከብ ታማሚውን በተገቢው መንገድ እንዳይረዱ እንቅፋት ይሆናል›› የሚል እምነቱን አካፍሎናል። አስተያየት ሰጪአችን የጥበቃው መላላት ታማሚዎች እርዳታ እንዳያገኙ፣ ሐኪሞች በስጋት ስራቸውን እንዲሰሩ በማድረግ አይቆምም ባይ ነው። “ማንም ሰው የተረጋጋ የሥራ አካባቢን ይፈልጋል። ባልተረጋጋ የሥራ አካባቢ ውስጥ መቆየት የሚፈልግ አይኖርም። ሁላችንም እዚህ ያለነው ምርጫ አጥተን ወይም አማራጭ እስክናገኝ ድረስ ነው” ብሎናል።
የሕክምና ግብአቶች አለመሟላትን አስመልክቶ ያነሳንለትን ጥያቄ ሲመልስ “ኮቪድን ሰበብ ያደርጉታል” የሚል አጭር መልስ ሰጥቷል። “የላብራቶሪ፣ የአልትራ ሳውንድ፣ ኤክስሬይ አገልግሎቶች ከሌሎች ክፍሎች ጋር መጋራቱና ከሌሎቹ እኩል ወረፋ መጠበቁ ፈጣን አገልግሎት የሚፈለግበትን ክፍል ቀርፋፋ አገልግሎት እንዲሰጥ አስገድዶታል” የሚለው የህክምና ባለሙያው በተገልጋዮች ዕይታ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ድክመት ተብሎ የሚወሰደው ተግባር ከሐኪሞች አቅም በላይ በሆነ አሰራር የመጣ እንደሆነ ይናገራል። በተገልጋዮች በኩል ደግሞ በተለይም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት (ቅዳሜ እና እሁድ) የድንገተኛ ህክምና እርዳታ ለማግኘት የሆስፒታሉን በር የሚያንኳኩ ታማሚዎች አብዛኛዎቹን ምርመራዎች በግል ተቋማት እንዲያከናውኑ መደረጉ ለተጨማሪ ወጪ እና ለመጉላላት ዳርጎናል የሚል ወቀሳ አብዝቶ ይሰነዘራል።
የኦክስጅን አገልግሎት በሌሎች ሆስፒታሎች የሚሰጠው በግርግዳ ውስጥ በተቀበሩ መስመሮችና ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ መንገድ ነው። በሆስፒታሉ ግን ያለው አቅርቦት በሚገፉ ትልልቅ ሲሊንደሮች በመሆኑ በአገልግሎቱ ላይ የራሱ የሆነ እክል ፈጥሯል።
እንደ “ሞኒተር” ያሉ የህመምተኛን መረጃ በቀላሉ ማወቅ የሚያስችሉ መሳሪያዎች በጥገና ምክንያት ጥቅም እየሰጡ አይገኙም። “ካሉት 9 ሞኒተሮች ውስጥ 2 ብቻ ናቸው የሚሰሩት” የሚለው ሰራተኛው አገልግሎት ያቋረጠው ማሽን እንዲጠገን በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም መፍቶትሔ እንዳላገኙ ይናገራል።
የህክምና መስጫ ክፍሎች እና መተላለፊያ ኮሪደሮች ጥበት ለ10 ሚሊዮኖች ሪፈራል ማዕከል ለሆነው ተቋም ሊቀረፉ ሲገባቸው ያልተፈቱ ችግሮች ናቸው።
በተቋሙ ውስጥ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ብቻ ከ3ዓመት በላይ እንዳገለገለ የነገረን አስተያየት ሰጪአችን እንደሚያምነው፡- ሌላው የተቋሙ ችግር የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ነው። በቂ መጠን ያለው እና በዘርፉ የሰለጠነ ባለሞያ ባለመኖሩ የአገልግሎት መስጫ ጊዜው እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል።
“የባለሙያው ብዛት ከተገልጋዩ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አይደለም” የሚሉት የሱፐርቪዥን ቡድን አባል የሆኑት ሲስተር ትዕግስት ጉተማ ናቸው። እንደሀገር የድንገተኛ ህክምና ባለሞያ እጥረት እንዳለ ቢያነሱልንም ሪፖርቱን በሰራንበት ወቅት ግን በድንገተኛ ክፍሉ የነበሩት ሁለት ድንገተኛ ሀኪሞች በስራቸው ላይ አልነበሩም። ተቋሙ ካለው ሰባት የድንገተኛ ነርስ (Emergency and Critical Nurse) አንዳቸውም ድንገተኛ ክፍሉ ውስጥ እየሰሩ አይደለም።
ከጥበቃ እና ጽዳት ጋር በተያያዘ ያለው አሰራር በጨረታ ለድርጅቶች እንደሚሰጥ የሚናገሩት ሲስተር ትዕግስት ጉተማ ከዚህ በፊት የነበረውን የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ቢቀየርም ለውጥ እንዳልመጣ ትናገራች። ከጥበቃ፣ ከጽዳት፣ ከመሳሪያ ብልሽት እና ሌሎችም ጋር ያሉ ችግሮች ሪፖርት እንደተደረጉና የሆስፒታሉ አመራር እንደሚያውቀው ይናገራሉ። ከሆስፒታሉ አመራር ባለፈም ቦርዱም ሊያውቀው እንደሚችል ነግራናለች።
ይህንን ዘገባ ያሰናዳው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የድንገተኛ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ታደሰን በሚመሩት ክፍል ላይ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክተው ምላሽ እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ ቢሯቸው ውስጥ ባለመገኘታቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻለም። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር በሽር አብደላም ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሐሳባቸው ሊካተት አልቻለም።