ነሐሴ 29 ፣ 2013

በከተማዋ ወጣቶች የማይታወቁት የወጣት ማዕከላት

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮች

የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር በከተማዋ ተዘዋውሮ ወጣቶችን ባነጋገረበት ወቅት በከተማዋ ተወልደው ካደጉ ወጣቶች መካከል የወጣት ማዕከላቱ የት አካባቢ እንደሚገኙና የሚሰጡትን አገልግሎት በተመለከተ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ታዝቧል፡፡

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በከተማዋ ወጣቶች የማይታወቁት የወጣት ማዕከላት

4 ክፍለ ከተሞችና 14 ቀበሌዎች ያሏት አዳማ የወጣት ማዕከላቶቿ ቁጥር ከወጣቶቿ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆኑም እነኚህንም ማዕከላት መኖራቸውን እና ምን እንደሚሰሩ የማያውቁ ብዙ ናቸው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ሥር የሚተዳደሩ 3 ወጣት ማዕከላት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በሥራ ላይ ናቸው። ሦስተኛውና በደጋጋ ቀበሌ በተለምዶ አጠራሩ 16 ቁባ መስጊድ አካባቢ የሚገኘው ማዕከል ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለወታደሮች ማረፊያነት እያገለገለ ይገኛል።

አሁን ባለው ሁኔታ በደረጃ A የሚገኘው የቁጥረ 1 ማእከል በቀን እስከ 1,000 ሰው አገልግሎት ይሰጣል፡፡  ከ400 ሺህ ኗሪ ሲሶው  ወጣት ለሆነባት አዳማ እርግጥ ሁለት የወጣት ማዕከል ይበቃል የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡

የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር በከተማዋ ተዘዋውሮ ወጣቶችን ባነጋገረበት ወቅት በከተማዋ ተወልደው ካደጉ ወጣቶች መካከል የወጣት ማዕከላቱ የት አካባቢ እንደሚገኙና የሚሰጡትን አገልግሎት በተመለከተ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ታዝቧል፡፡

የፎቶግራፍ ባለሙያ የሆነው ወጣት አብዱልሂፊዝ ፈድሉ “ወጣት ማዕከሎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ አገልግሎታቸውን የማወቅ እድል ግን አልገጠመኝም” ብሎናል፡፡ “ማዕከላቱ ወጣቶች አልባሌ ቦታዎች ላይ እንዳይውሉ ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አውቃለሁ፡፡ ሄጄ ግን አላውቅም፡፡ ምናልባት በመኖርያ አካባቢዬ ስለሌሉ ይሆናል” የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

ሌላዋ ወጣት ቃልኪዳን እንዳለ በከተማዋ ማርያም ሰፍር ተወልዳ እንዳደገች ነግራናለች፡፡ ስለ ወጣት ማዕከላቱ ላነሳንላት ጥያቄ “ወጣት ማዕከላት መኖራቸውን አላውቅም” የሚለውን አጭር መልስ ሰጥታለች፡፡

ማዕከላቱ በወጣቶች ላለመታወቃቸው በርካታ ምክንያቶች መዘርዘር ቢቻልም፤ ለትራንስፖርት አመቺ የሆነ ሥፍራ ላይ አለመገንባታቸው፣ የአካባቢያቸውን ወጣት የሚስቡ ስትራቴጂዎች ስለሌላቸው እና ራሳቸውን የማስተዋወቅ ሥራ ባለመስራታቸው እንደሆነ ከአስተያየት ሰጪዎቻችን ሰምተናል፡፡ ከማዕከላቱ በቅርብ ርቀት ሱስ አስያዥ ነገሮች የሚሸጡባቸው ጤናማ ያልሆኑ መዝናኛዎች መኖራቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በቅኝቱ ታዝቧል፡፡

ቀደም ባለው መጠሪያቸው “ወጣት ማእከል” ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ “የወጣት ማበልጸጊያ” የሚል ስያሜ ያገኙት ማእከላቱ እንደ ቼዝ፣ ዳማ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ ያሉ የቤት ውስጥ ጨዋታዎች (Indoor games)፣ ቤተ-መጻሕፍት ይኖሯቸዋል፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስን እና የሜዳ ቴኒስን የመሰሉ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ እንዲችሉ ይጠበቃል፡፡

በአሁን ሰዓት በአገልግሎት ላይ የሚገኘው በሀንጋቱ ቀበሌ በተለምዶ ጨርቃጨርቅ አካባቢ የሚገኘው የአዳማ ከተማ አስተዳደር ቁጥር 1 ‹‹የወጣቶች ማበልጸጊያ›› ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በአሁን ወቅት የመጻሕፍት እና ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት፣ የነጻ ኢንተርኔት ዋይፋይ አገልግሎቶች ለወጣቶች ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም በግቢው የእግር ኳስ፣ መረብ ኳስ እና የማስ ስፖርት አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

ሌላው በውስጡ የአዳማ ሳይንስ ካፌም ይገኛል። ሳይንስ ካፌው ኢንተርኔት ጋር በተያያዙ 20 ኮምፒውተሮች ለወጣቶች አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በሰኔ 2/2013ዓ/ም የከተማው የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተመረቀ ቢሆኑም በማእከሉ ውስጥ ግን የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የወለል እና በር እና መስኮት አጨራረስ ችግር ይታያል፡፡ ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ባሳ ተቋራጩ ስራውን ሳይጨርስ አስረክቦ መውጣቱን ነግረውናል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሰባት ወራት ተዘግተው ባሳለፍነው ታህሳስ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት ሁለቱም ማዕከላት በተጠቃሚዎቹም ሆነ በሰራተኞቻቸው ምንም ዓይነት ኮቪድ -19 መከላከያ ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም፡፡

ተማሪ እስራኤል ዳምጠው የቦሌ ክ/ከተማ ነዋሪና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በቁጥር 1 ማዕከል የቤተመጸሐፍት እና ዋይ-ፋይ ኢንተርኔት አገልግሎቶች እንደሚጠቀም ይናገራል። የካፌው አገልግሎት አለመኖሩን አንድ የማዕከሉ ጉድለት መሆኑን አነስቷል፡፡

የቁጥር 1 ማዕከል ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ባሳ ካፍቴሪያውን በማኅበር ለተደራጁ ሴቶች እና ወጣቶች ተሰጥቶ እንደነበርና ስራው ስላላዋጣቸው ጥለው መውጣታቸውን ይገልጻሉ።

በጨፌ ቀበሌ አመዴ ገበያ ጀርባ የሚገኘው የአዳማ ቁጥር 2 የወጣቶች ማበልጸጊያ ማዕከል የቤተ-መጸሐፍት እና የሜዳ ጨዋታዎች አማራጭን በዋናነት በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህም ማዕከል እንዲሁ አገልግሎት መስጫ አካባቢዎቹ ንጽህና እንዲሁም የበር እና መስኮቶች ብልሽት ይታይበታል፡፡

የቁጥር 2 ማዕከል ኃላፊ ወ/ሮ ታየች የሺጥላ በአካባቢው የሚጣለውን ቆሻሻ ለመስቀረት ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር እየሰሩ እንደሆነና በቀጣዩ ዓመት ማእከላቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እቅድ መያዙን ነግረውናል።

አስተያየት