የዘመን መለወጫ ዜማዎች

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያነሐሴ 20 ፣ 2013
City: Addis Ababaባህል ሙዚቃታሪክ
የዘመን መለወጫ ዜማዎች

ብዙዎች “በዓላት በዘፈን ይደምቃሉ፤ ባህል በዜማ ይገለጣል” በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። የዜማ አይረሴነት እና ተወዳጅነት ባህላዊ ክዋኔዎች እንዳይሰለቹ ብቻ ሳይሆን ዘመናትን እንዲሻገሩ አድርጓል። በዓላት በናፍቆት እንዲጠበቁ የባህላዊ ክዋኔዎች አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደሆነም ይታመናል። በዓል፣ ባህል እና ዘፈን አንዱ ከአንዱ የሚሰናሰልና አንደኛው ያለ ሌላኛው ውበቱ የሚጎድል ሁነቶች ናቸው። ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው “ራሱን በሙዚቃ የማይገልጥ የዓለም ማኅበረሰብ የለም” የሚለው የተመራማሪዎች ድምዳሜ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሕዝቦች ልዩ ልዩ ባህሎች ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ባሉት ቀናት ዝናባማውን ክረምት የሚሸኙ፣ ጸሐያማውን በጋ የሚቀበሉ፣ የዘመን መለወጥን የሚያበስሩ በዓላት ይከበራሉ፡፡ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ጫፍ የሚከበሩት በዓላት ከቤት ውጭ የሚከበሩ (የአደባባይ) በመሆናቸው እና ጭፈራ ወይም ዜማ ያላቸው መሆኑ ያመሳስላቸዋል፡፡

አዲስ ዓመትን እና የአዲስ ዓመት ዋዜማን አስታከው የሚከበሩ በዓላት ከነሐሴ ወር አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እስከ ጥቅምት መባቻ ድረስ ይዘልቃሉ። ወንዶች ብቻ ከሚጫወቱበት ደብረታቦር /ቡሔ (ነሐሴ 12 እና 13) ክብረ በዓል ጀምሮ ሁለቱም ጾታ እስከሚሳተፍበት መስቀል (መስከረም 17) ድረስ የየራሳቸው ታሪካዊ አመጣጥ፣ ሐይማኖታዊ ትርጓሜ፣ ባህላዊ እሴት፣… አላቸው።

ከማይዳሰሱ መንፈሳዊ ቅርሶች ውስጥ የሚካተቱት እነኚህ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጨዋታዎች አብዛኛውን ጊዜ ለትዳር ባልደረሱ ወጣቶች ይዘወተራሉ። በመላው ዓለም የክርስትና እምነት መሰበክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መከበር እንደጀመሩም ይታመናል። ጨዋታዎቹ ከባህላዊ እሴትነታቸው ባለፈ በአማኞች ዘንድ ስርአተ አምልኮ ሲፈጸምባቸው እንደቆየ የእምነቶቹ ምሁራን ያስረዳሉ። የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ በዓላቱን መነሻ የሚያደርጉት ጨዋታዎች የማኅበረሰብን ትስስር ሲያጠናክሩ፣ ባሕላዊ አልባሳትን እና ቁሳቁሶችን ሲያስተዋውቁ እና ሲጠብቁ ለበርካታ ዓመታት ስለመቆየታቸው ይመሰክራሉ።

ኢትዮጵያ የራስዋ ባሕረ-ሀሳብ አላት። በዚህ የራስ ዘመን አቆጣጠር መሰረት የአስራ ሦስት ወራት ባለፀጋ የሆነችው ኢትዮጵያ  ከነሐሴ ወር አጋማሽ እስከ ጥቅምት መባቻ ድረስ በልዩ ልዩ ትውፊታዊ በዓላት ከዳር ዳር ትደምቃለች።

ሜዳ፣ ጋራና ሸንተረሮቿ በአደይ አበባ እና በእሸታማ አዝርዕት ሲያሸበርቁ፣ ዘመን መለወጫዋን ያስቡታል። ወንዝ፣ ውቂያኖስ፣ ኩሬዎቿ፣… ሰማይን ጨምሮ ከሰነበተባቸው የክረምት ዝናብ፣ ድፍርስ ወንዝ እና ውሃ ሙላት መውጣት ይጀምራሉ።

በዚህ ወቅት የሰው ልጅም ከከረመበት ድካሙ ተላቆ ከፍ ወዳለ የአስተሳሰብ ልህቀት ለመሸጋገር ሲታትር ይስተዋላል። በአዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ፣ በጠነከረ ተስፋ፣… አዳዲስ ውጥኖች ይሰናዳሉ። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በዚህ የለምለም ወር የራሳቸውን ልዩ ባህል በማንገሥ ዘመናቸውን ይለውጣሉ፡፡

ቺሜሪ

የጋምቤላ ሕዝቦች ዘመናቸውን የሚያድሱት ባሮ ወንዝ በመሰብሰብነው፡፡ በወንዙ ዳርቻ ሆነው የትላንትናን ክፋት፣ ቂም እና በቀል ትተው አዲስ ሐሳብ በመጨበጥ በዓሉን ያከብራሉ። በክብረ በዓሉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ይመርቃሉ። በዚህ ወቅት ልጆች “ቺሜሪ፣ ቺሜሪ” እያሉ የበዓሉን ድባብ ያደምቁታል። የቺሜሪ ጨዋታ በዋናነት የሚቀነቀነው በመስቀል ደመራ ሰሞን ነው። ልጆች ወደ ባሮ ወንዝ እየተሯሯጡ የሚዘፍኑት የብስራት ዜማ ነው። የቺሜሪ ሌላኛው ትርጉም ተከስቶ የነበረ ወረርሽኝም ሆነ ሌላ የበሽታ ዐይነት “ከሀገር፣ ከሰፈር ውጣ” እንደ ማለት ነው። በዚህ የአዲስ ዓመት መጀመርያ ወር ህፃናት እንዳይታመሙ፣ እናቶች እንዲመቻቸው ‘ቺሜሪ’ እንደ መልካም ምኞት መግለጫ ነው ማለት ይቻላል።

መስቀል የክልሉ ተናፋቂ እና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ነው። የመስቀል ደመራ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ በመስከረም 15 ይከበራል። በአንድ የደብር ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ በጋምቤላ ክልል ከገጠር እስከ ከተማ ባሉ አድባራት ሁሉ ደመራው ይደመራል። በዚህ የደመራ ሰሞን፣ ሰዎች ወደ መደበኛ ስራቸው በፍጥነት አይመለሱም። ዘመድ ከዘመዱ፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ በአንድነት ተሰባስቦ የተለያየ የባህል ምግብ፣ አለባበስ እና የአጨፋፈር ባህል ይዘው ወደ ባሮ ወንዝም ሆነ በተመረጡ የክልሉ መዝናኛ ቦታዎች ሄደው ይጨዋወታሉ።     

ይህ ከመስከረም 18  የጀመረው የበዓል ጨዋታ እስከ ጥቅምት መባቻ ድረስ በደመቀ የባሕል ጨዋታ ይዘልቃል።

መስቀል አጋመ

አዲግራት ውስጥ በምትገኘው አጋመ የመስቀል በዓል በደመቀ ሁኔታ ከሚከበርባቸው የሐገራችን አካባቢዎች ውስጥ አንዷ ናት። አዲግራት በቀድሞ አጠራሯ የአጋመ አውራጃ፣ በአሁኑ ደግሞ የምሥራቅ ትግራይ ዞን ዋና ከተማ ናት። የከተማዋ በተራራማ ስፍራ ላይ የተመሰረተች ሲሆን፣ ከኤርትራ በቅርብ ርቀት ትገኛለች። ከተማዋ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ትግራይ ውስጥ ከነበሩ ከተሞች የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ እንደነበራት መረጃዎች ያመላክታሉ።

በአጋመ እንደ አዲስ አበባው መስቀል አደባባይ ሁሉ የመስቀል ደመራ የሚከበርበት የተለየ ስፍራ አላት። ቦታው በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ በግዝፈቱ ተወዳዳሪ እንደሌለው የሚነገርለት የተተከለ ግዙፍ የሚያበሩ አምፖሎች ያሉት መስቀል ይገኛል። በዚህ የበዓል ወቅት የበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ የባሕል ምግቦች በየዓይነቱ ይቀርባሉ። ከህፃን እስከ አዋቂ በባህል ልብስ አሸብርቀው ወደ በዓሉ መከበሪያ ቦታ “አጋመ” ይሄዳሉ። በጉዟቸው ወቅትም ሆነ በክብረ-በዓሉ ጊዜ መስቀልን የሚያወድሱ፣ የዘመን መለወጥን የሚያመላክቱ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ዜማዎች ይዜማሉ፡፡

ጋሮ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት አምስት ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ የሆነው የሺናሻ ማኅበረሰብ በመተከል ዞን ከሚገኙት የድባጢ፣ ቡለን፣ ወንበራ፣ ዳንጉር፣ ግልገል እና አሶሳ አካባቢዎች ላይ በብዛት ተሰራጭተው ይገኛሉ። የሺናሻ ማኅበረሰብ አባላት ማንነታቸውን የሚገልጹባቸው ከሌላው ማኅበረሰብ ልዩ የሚያደርጓቸው ቅርሶች አሏቸው። ከማይዳሰሱት የማኅበረሱ ቅርሶች ውስጥ ክብረ-በዓላት ይገኙበታል። ከእነዚህ ክብረ በዓላት ውስጥ ጋሮ ወይም ዘመን መለወጫ ዋነኛው ነው።

በተለያዩ ምክንያቶች የትውልድ ቀያቸውን ለቀው የሚኖሩ የማኅበረሰቡ አባላት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ይሰበሰባሉ። የጋሮ በዓል ዶዎ፣ ኢንዶሮ፣ ኢንዲዎ በመባል የሚታወቁት ዋና ዋናዎቹ የሺናሻ ማኅበረሰብ ጎሳዎች ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተገናኝተው በሕብረት የሚያከብሩት ተወዳጅ በዓል ነው። ለትዳር የደረሰ አቻውን የሚመርጥበት፣ የተጣላ ይቅር የሚባባልበት፣ በአዲስ ተስፋ አዲስ ዓመትን ለመጀመር ዝግጅቱን የሚያጠናቅቅበትም ነው።

የጋሮ በዓል አከባበር ቅድመ ዝግጅት የሚጀመረው ለበዓሉ የሁለት ወራት እድሜ ሲቀር ነው። የማኅበረሰቡ ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች “ዳላሺ ዱባ”፣ “ጉሪ ዱባ”፣ “ግጪንጋ ዱባ”፣… የሚባሉትን ጨዋታዎች መጫወት ይጀምራሉ። ከቀን ሥራ እና ከምሽት እራት በኋላ ለበዓሉ በሚዘጋጅ “ጋሮ ጄባ” (አደባባይ) በመሔድ ይጨፍራሉ። ለጋሮ ጨዋታ የወጡ ወጣቶች በዚያው ተገናኝተው እንዲያድሩ አይፈቀድላቸውም። ምሽቱ ሲጀምር ወጥተው ሌሊት አጋማሽ ላይ ወደ መኖሪያቸው ይመለሳሉ።

ያላገባው ወጣት ያጫትን ልጃገረድ ዐይቶ ቤተሰቧን አጣርቶ ይመለሳል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው የሺናሻ ማኅበረሰብ አባላት ከጥንት ጀምረው የሚያከብሩት፣ የማንነታቸው መገለጫ የሆነው የጋሮ በዓል አከባበር በሦስት ክፍሎች የተከፈለ ነው።

የመጀመሪያው “ዳለሻ” የሚባል ሲሆን ከሐምሌ ወር መጀመርያ አንስቶ የሚከበር ነው። የአደዳዲስ እህሎችን ማለትም በቆሎ እሸት፣ ጎመን፣… የመሳሰሉት መድረሳቸውን አስመልክቶ የአዳዲሶቹ የምግብ ዐይነቶች መቀበያ እንደሆነ ይታመናል።

ነሐሴ ወር ሲጀምር የሚጀምረው የጨዋታ ዐይነት ደግሞ ከ“ዳንሻ” የሚከተለው ሁለተኛው የጨዋታ ዐይነት ነው። ስያሜውም “ቃጪ ዱባ (የጉልጓሎ ጨዋታ)” ይሰኛል።

ከትንሿ ወር ጳጉሜን ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ የሚጫወቱት የጨዋታ ዐይነት ደግሞ “ግጪንጋ” የሚል መጠሪያ አለው። ግጪንጋ (ጉሪ ዱባ) ሁሉም የብሔረሰቡ አባላት ክብ ሰርተው በጋራ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው። በዚህ ሁኔታ እስከ ጋሮ በዓል ዋዜማ ማለትም መስከረም 16 ድረስ ይዘልቃል። በጋሮ በዓል ዋዜማ ምሽት ሁሉም በየቤቱ ከአራት እስከ አስራ ሁለት የሚሆን እርጥብ ግንድ ያዘጋጃል። የሚዘጋጁት እንጨቶች የተለዩ ናቸው። ፍሬ የማያፈሩ እና ሲፈነከቱ ውሃ የሚወጣቸው መሆን አለባቸው። እንጨቶቹን በእሳት በመለኮስ “እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰን” እያሉ ወደቤት ይዘዋቸው ይገባሉ። ቤት ውስጥ ካለው እሳት ጋርም ይቀላቅሏቸዋል። እንጨቱ ተቃጥሎ እስኪያልቅ ድረስ ወደ ውጭ አውጥቶ መጣል አይቻልም። እንደዚያ መሆኑ መጪው ዘመን ለቤቱ ደስታ፣ ፍቅር፣ ሰላም እንደሚያመጣ ይታመናል።

ከዋዜማው አንስቶ ደግሞ ባማረ የባህል ልብስ እና በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይታጀባል። በባህል ትዕይንቶች እና ጨዋታዎች ከሁለት ወራት በላይ የሚቆየው የጋሮ በዓል መስከረም 18 ይጠናቀቃል። ክብረ በዓሉ ከመጠናቀቁ  በፊት ያሉት ተከታታይ ሦስት ቀናት ጭፈራ የማይቋረጥባቸው ናቸው። ቀን ሌሊት ሳይባል ሁሉም ተወላጅ በጋራ ሆኖ ተከታታይ የጨዋታ ስነ-ስርአት ያከናውናል። በመጨረሻው ቀን ተሰሚነት ያላቸው የሐገር ሽማግሌዎቸ ለሐገር እና ለወገን በሚሰጡት ምርቃት የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል። ቀጣዩ ዘመን የሰላም የደስታ እንዲሆን፣ አዝመራው ፍሬአማ፣ አገሩ ጥጋብ፣ ቀዬው ሰላም እንዲሆን፣ የተወለዱት እንዲያድጉ፣ የተረገዘው እንዲወለድ፣ ያላገቡ እንዲያገቡ፣… ተመኝተው በዓላቸውን ያጠናቅቃሉ።

የጋሮ በዓል ሌላው መገለጫ እርድ ነው። ለእርድ የሚሆነውን ከብት የማዘጋጀት ሐላፊነቱ የአባቶች ነው። አባቶች ዋናው በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናቶች በሚቀሩበት ጊዜ ሰንጋ ያዘጋጃሉ። እናቶች ደግሞ የምርቃት መርሃግብሮች በሚከናወኑበት ጊዜ የሚበላ እና የሚጠጣ ያሰናዳሉ። ወጣቶች ለደመራ የሚሆነውን እንጨቶች ያዘጋጃሉ።

መስከረም አስራ ስድስት የሚደመረው ደመራ መስከረም አስራ ሰባት ከሌሊቱ አስር እስከ አስራ አንድ ሰዓት ይለኮሳል። ደመራው ሲጠናቀቅ አባቶች ይመርቃሉ። ከ“ዶዎ”፣ ከ“ኢንዶሮ” እና “ኢንዲዎ” ጎሳዎች የእድሜ ባለጸጎች ተመርጠው ይመርቃሉ።

የጋሮ በዓል ለወራት መቁጠሪያነትም ያገለግላል። ሺናሻዎች፡- ሻዊያ፣ ጌድዋ፣ እያሉ ወራቶቻቸውን ይቆጥራሉ። ሻዊያ ማለት የመኸር ወቅት ማለት ሲሆን የጋሮ በዓል የሚጀምርበት ነው።

ጊፋታ

የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ አለው። “የዓመቱ የመጀመርያ ወር ጊፋታ” ተብሎ ይጠራል።  ትርጉሙም ከዘመን ዘመን መሻገር፣ “ባይራ” ወይም ታላቅ የሚል ፍቺ ይሰጠዋል።

ዘመን አቆጣጠሩ የተለየ ሥም ባይሰጠውም፣ ወርሃ መስከረም በጠባ ከአስራ አራት እስከ ሃያ ቀናት መካከል በሚውለው እሁድ አዲሱን ዓመት ይቀበሉታል። በየዓመቱ ከመስከረም አስራ አራት እስከ ሃያ ባሉት ቀናት መካከል የሚውለው እሁድ የአዲስ ዓመት ቀን ሲሆን፣ ስሙም “ሹሃ ወጋ” ወይም የእርድ እሁድ ይባላል።

ወላይታዎች አስራ አንድ ወራት በሥራ ካሳለፉ በኋላ የመጨረሻውን አንድ ወር ለበዓሉ ያውሉታል። የመጀመሪያው አስራ አምስት ቀን በበዓሉ ዝግጅት የሚያልፍ ሲሆን፤ ተከታዩ አስራ አምስት ቀን ደግሞ በመዝናናት እና በመጫወት፣ በመብላት እና በመጠጣት የሚያልፍ ነው።

የበዓሉ ዝግጅት የሚጀመረው በወርኃ ሃምሌ በሚደረገው የ“ጉልያ” ሥርዓት ሲሆን በዚህ የዝግጅት ወቅት ወላጆች ለልጆቻቸው ለ“ጊፋታ” በዓል ማክበሪያ “ጉራዱዋ” የተባለውን ምግብ ያዘጋጃሉ።

ለክብረ-በዓሉም ወንዶች ለአስራ አምስት ቀን የሚሆን የማገዶ እንጨት ያከማቻሉ። ለከብቶችም የሚበቃ ሳር በበቂ አዘጋጅተው ያቀርባሉ። የበዓል ሥጋ ወደ ቤት ለማምጣት ለአስራ አንድ ወራት የሚቆጥቡት ተቀማጭ ገንዘብም የወንዶች ድርሻ ነው።

ሴቶች በበኩላቸው ለቆጮ የሚሆን እንሰት በጊዜ ይፍቃሉ። የወላይታ ዳጣ፣ በርበሬ እና መጠጦች እንደ ቦርዴ፣ ጠጅ፣ ጠላ እና ወተት በትልቅ ጋን እና እንስራ ያዘጋጃሉ። ለልጆች ስጦታ መስጫ ሎሚ ገዝተው በእንስራ ያጠራቅማሉ። ለቂጣ የሚሆን የበቆሎ እና የማሽላ ዱቄትም ያዘጋጃሉ።

በተጨማሪም የጊፋታ በዓል እየተቃረበ ሲመጣ በተከታታይ ያሉት ሦስት ሳምንታት ስያሜያቸው “ሀሬ ሀይቆ”፣ “ቦቦዳ” እና “ጎሻ” ይሰኛል። “ሀሬ ሀይቆ” የሚባለው የጳጉሜን ወር ሲሆን “አህያ ፈጅ” ሳምንት ይባላል። የዚህም ምክንያት አህያ ለበዓል ዝግጅት የሚሆን ዕቃ ከቤት ወደ ገበያ የምታመላልስበት፣ በበረታ ጭነት የሚትደክምበት ሰሞን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው።

ከመስከረም አንድ እስከ ሰባት ያለው ሳምንት ደግሞ “ቦቦዳ” ሲባል  ትርጓሜውም ሆድ ሞርሙር ማለት ነው። መሞርሞር ራበኝ፣ ሞረሞረኝ ማለት ነው፡፡ ምግብ አሰኘኝ፣ መብላት ፈለኩ እንደ ማለት፡፡ የስያሜው ሰበብ ጊዜው ከሥራ እና እንግልት አረፍ ተብሎ የሚበላበት፣ የሚጠጣበት ጊዜ በመሆኑ የተሰጠ ነው፡፡

ፊቼ ጫምባላላ

ፊቼ ጫምበላላ የሲዳማ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ነው። ፍቼ እና ጫምባላላ የማይነጣጠሉ ናቸው። ፊቼ የአሮጌው ዘመን መጠናቀቅ ዋዜማ ሲሆን፣ ጫምባላላ ደግሞ የአዲሱ ዘመን መባቻ ነው።

የፊቼ እና ጫምባላ ታሪካዊ አመጣጥ መቼ እንደሆነ ባይታወቅም፣ በሲዳማ “በሀቤላ” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከነበሩት “ፊጦራ” የሚባሉ ሰው በሴት ልጃቸው “ፊቾ” አማካኝነት መጀመሩን መረጃዎች አመላክተዋል።

ፊቾ የምትባለው ልጅ አግብታ የበዛ ሀብት ባገኘች ጊዜ፣ በባህሉ መሠረት ቤተሰቦቿን የተለያዩ የባህል ምግቦችን በመያዝ በየዓመቱ “ቀባዶ” ተብሎ በሚጠራው ቀን ትጠይቃቸው ነበር። በዚህ የቤተሰብ ማዕድ የተረፈውን ምግብ ተሰብስበው ይመገቡና የዚህ ዓይነት ጥጋብ ዞሮ ይምጣ እያሉ ይዘፍናሉ።

ከዚህ የቤተሰብ ጨዋታ በኋላ የፊቾ ጥየቃ በዘላቂነት መታወስ እንዳለበት በመግለጽ አባቷ አቶ ፌጦራ በየዓመቱ ደስታ የምትፈጥረው ልጃቸው የምትመጣበት ቀን የሲዳማ ፌቼ ወይም የዘመን መለወጫ ተብሎ እንዲከበር መወሰኑን ጥናቶች ያስረዳሉ።

የፊቼ አንድምታ የዘመን መለወጫ ድልድይ አዲሱ ዓመት የበረከት የደስታ እና ፍሥሐ ይሁንልን እንደማለት ነው። ከዋዜማ ለጥቆ ያለው ቀን አዲስ ዓመት ወይም ጫምባላላ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ስለአለፈው ዓመት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ስለቀጣዩ ደግሞ የመልካም ምኞት መግለጫ ነው።

መስቃላዮ

በደቡብ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የመስቀል በዓል አከባበር ማለትም ከጉራጌ መስቀል በዘለለ፣ መስቀል በጋሞም የተለየ ባሕል አቅፎ ይገኛል። መስቀል በጋሞ የአዲስ ዓመት ብስራት መንገርያ ነው። እነርሱ "ማስቃላ ዮዮ!" ይሉታል። ሲተረጎም እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረን ነው። ይህ የሚባለው በመስቀል ሰሞን ነው። መስቀል የደስታ ማብሰሪያ በዓል ስለሆነ ከመስቀል በፊት የተፈጠረ ችግር ካለ መስቀልን አይሻገርም ይባላል።

ከደመራ መልስ የአካባቢው ሽማግሌዎች በዓመቱ ውስጥ ሀዘን የተከሰተባቸውን ቤቶች እየዞሩ ለመጨረሻ ጊዜ አብረዋቸው ያስተዛዝናሉ። በመጨረሻም፣ አባቶች “ሞት ታሪክ ይሁን” በማለት ምክር ይሰጣሉ።

መስቀል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ለእንስሳትም በዓል ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው “ካሎ” ወይም የጋራ የግጦሽ ቦታ ነው። “ካሎ” በየዓመቱ ከግንቦት የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ እስከ መስከረም ሁለተኛ ሳምንት እንስሳት የማይሰማሩበት ጥብቅ የጋራ ግጦሽ ነው።

ሁሉም የጋሞ አካባቢ መንደሮች “ካሎ” አላቸው። በመሆኑም መስቀል የፍጥረት ሁሉ በዓል ነው ተብሎ ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪ መስቀል የሙዚቃ በዓል ነው። በመስቀል ሰሞን ሁሉም የካሎ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው በሙዚቃ ይዝናናሉ።

በተጨማሪም መስቀል ሲመጣ፣ ሰዎች ከነበረ ቂማቸው ተላቀው ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመሻገር ይሰናዳሉ። መስቀል የይቅርታ እና የፍቅር በዓል ነው። ስለዚህ፣ የተጣሉ ሰዎች ሳይታረቁ መስቀልን ካለፉ እንደ ነውር ይታይባቸዋል። በተመሳሳይ መስቀል ጎረቤታሞች ከአንድ ገበታ የሚካፈሉበት በዓል ስለሆነ፣ ቂም ይዞ ወደ ቀጣይ ዓመት መሻገር “ጎሜ” ስለሚባል በሽማግሌዎች መሪነት የእርቅ ሥነስርዓት ይካሄዳል።

እንደ ሲዳማ ፊቼ ጨምበላላ፣ ወላይታ ጊፋታ እና ጋሞ መስቃላዮ የመሳሰሉት የዘመን መለወጫ ዓይነቶች መሰረታቸው ለምለሙ ጊዜ ነው። ዓላማቸውም የተጣላ ታርቆ አዲሱን ዓመት በፍቅር እና በዕድገት ብልፅግና ለማዘመን ነው። ስለዚህም፣ ዘመን መለወጫ የበርካታ ባሕሎች መንፀባረቂያ ነው ማለት ይቻላል።

አዳብና

አዳብና በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ በጉጉት ከሚጠበቁ እና በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ወጣት ወንዶች እና ሴቶችን የሚያሳትፈው ክብረ-በዓል የሚጀምረው በዓዲስ ዓመት ዋዜማ ነው፡፡ የመስቀል በዓል እየተቃረበ ሲመጣ ደግሞ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በየአካባቢው የቆመውን ግዙፍ ደመራ ከበው በማዜም እና በመጨፈር በዓሉን ድምቀት ይሰጡታል፡፡

አዳብና የተለያዩ አጨፋፈሮች አሉት፡፡ ወንዶች እና ሴቶች በጋራ ክብ ሰርተው ወንዶች በጉሮሯቸው በሚያወጡት ልዩ ድምጽ እና ጭብጨባ፣ ሴቶች በከበሮ እና በጭብጨባ ያጅቡታል፡፡ ሰፊው ክብ መሐል የገቡት ጥቂት ወጣቶች ደግሞ ልዩ ጭፈራ ያሳያሉ፡፡ ያልደከመው የደከመውን እየተካ ረዘም ላለ ሰዓት ጭፈራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ቅኔ ለበስ የሆኑ ሽሙጥ እና አድናቆት ያዘሉ ግጥሞችን በማውጣት ሁለቱም ጾታዎች ይሳተፋሉ፡፡

የአዳብና ጨዋታ ላይ ወንዶች ብቻ የሚጫወቱት “አጋት” የሚሰኝ ጨዋታም አለ፡፡ “አጋት” ከፊትለፊት ቀጥ ብሎ የቆመን ተጫዋች ሌላ የጨዋታው ተሳታፊ ወደ 20 ሜትር ርቆ በመንደርደር ዘሎት እንዲያልፍ የሚደረግበት የጨዋታ ዐይነት ነው፡፡ ዘላዩ ተጫዋች የቆመውን ሰው እጅ እና ትከሻ ሳይነካ ማለፍ የተሳነው እንደሆነ እርሱም በተራው ቋሚ ይሆናል፡፡ እንዲህ እያለ የወንዶቹ አጋት ይከናወናል፡፡

የአዳብና በዓል አከባበር ቅድመ ዝግጅት የሚጀመረው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ነው፡፡ ሴቶች በአንድ ላይ ተሰብስበው “አዬ አዬ ሆ- አዬ አዬ ሆ- አዬ ንብለ” የሚል ዜማ በማዜም እንግጫ ይነቅላሉ፡፡ አደይ አበባ ይሰበስባሉ፡፡ ጸጉራቸውን በልዩ ሁኔታ በመሰራት አምረው ደምቀው ለመታየት ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ አዲስ ልብስ እና ጌጥ ያዘጋጃሉ፡፡ ወንዶችም ባቆሙት ደመራ ዙሪያ ከበው ይጨፍራሉ፡፡ ይህ የጭፈራ ስነ-ስርአት ታዳጊዎችን ስለ አዳብና በዓል እና የአጨፋፈር ሂደት ለማስተማርም ጠቀሜታ ላይ ይውላል፡፡

አዳብና ያላገቡ ወጣቶች ለትዳር የሚተጫጩበት ነው፡፡ ጎረምሳው በጨዋታው እና በጭፈራው መካከል ቀልቡ ያረፈባትን ኮረዳ ይጠጋታል፡፡ በያዘው አለንጋ የቀሚሷን ጫፍ መታ ያደርጋል፡፡ ቀሚሷ የተነካባት ኮረዳ መመረጧን ትረዳለች፡፡ ተመራጯ እንስት ከድርጊቱ በኋላ ልትሽኮረመም፣ ልትደሰት ወይም ልትቆጣ ግፋ ካለም አምርራ ልታለቅስ ትችላለች፡፡ ወንድየው የወደዳትን ኮረዳ ሁናቴ ተመልክቶ በጓደኞቿ አማካኝነት ሎሚ ወይም ማስቲካ ይልክላታል፡፡ ሴቲቱ የወደዳትን ወጣት እሷም ወዳው ከሆነ ስጦታውን ትቀበላለች፡፡ ካልተቀበለች ግን የትጭጭት ሂደቱ እዚህ ላይ ያበቃል፡፡

ስጦታውን ተቀብላ ይሁንታውን የሰጠችው ወንድ ተመሳሳይ ጎሳ አይጋባምና የሴቲቱን ጎሳ ያጣራል፡፡ ከዚያም ለቤተሰቦቹ ተናግሮ ለቤተሰቦቿ ሽማግሌ ይላካል፡፡

የጋብቻ ጥያቄው ይሁንታ የሚያገኘው የሽማግሌዎቹ ልመና አወንታዊ ምላሽ አግኝቶ ጥሎሽ (ቸግ) ከተጣለ በኋላ ነው፡፡ ከ“ቸግ” በኋላ የጋብቻ ጥያቄው ህጋዊ ይሆናል፡፡ ወጣቶቹ በሰርግ እስኪጋቡ ድረስም እጮኛሞች ሆነው ይቆያሉ፡፡ በየዓመቱ አዳብና ላይ እየተገናኙ እንዲጫወቱ የሚፈቀድላቸው ሲሆን በእጮኝነት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ መቆየት ይችላሉ፡፡ ስጦታ እየተለዋወጡ የሚጨዋወቱበት የአዳብና በዓል ላይ መታደም የሚያቆሙት ከሰርጋቸው በኋላ ነው፡፡ ወጣቶቹ ከሰርጋቸው በኋላ የሚመጣውን የአዳብና በዓል ለመጨረሻ ጊዜ አክብረው አዳብና መሄድ ያቆማሉ፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe for the past five years. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed.