ነሐሴ 20 ፣ 2013

ለሀገር አቀፍ ተፈታኞች ቅድመ ፈተና ‘ሞዴል’ የሚሰጠው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ

City: Addis Ababaትምህርትወቅታዊ ጉዳዮች

ከ3 ወራት በፊት የተከፈተው “ፈተና ኔት” የተሰኘ መጠሪያ ያለው የቴሌግራም ገጽ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል የመግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በዕውቀት እና በስነ-ልቦና ዝግጅትን ማገዝ አላማው ያደረገ ነው፡፡

Avatar: Mahlet Yared
ማህሌት ያሬድ

Mahlet is an intern at Addis Zeybe who explore her passion for storytelling

ለሀገር አቀፍ ተፈታኞች ቅድመ ፈተና ‘ሞዴል’ የሚሰጠው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ

አሉታዊ ሐሳቦች በፍጥነት እንዲሰራጩ ዕድል በመፍጠራቸው የሚተቹት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ለበጎ ዓላማ ሲውሉም ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚዘወተሩትን እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ቲክቶክ ያሉ ማኅበራዊ ትስስር ድረገፆችን በመጠቀም “ቢዝነሳቸውን” ያሳደጉ፣ በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን ዕውቀት ለሌሎች ያጋሩ፣ የተቸገሩ ወገኖች እርዳታ እንዲያገኙ ያስቻሉ፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ያገናኙና የመዝናኛ አማራጭ የፈጠሩ ብዙዎች አሉ፡፡

ከ3 ወራት በፊት የተከፈተው “ፈተና ኔት” የተሰኘ መጠሪያ ያለው የቴሌግራም ገጽ (ቻናል) በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ ተከታዮች ያገኘ፣ ማኅበራዊ ሚድያውን ለበጎ ዓላማ ካዋሉት መካከል የሚመደብ የቴሌ ግራም ቻናል ነው። የቻናሉ ዓላማ ወደ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል የመግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ማገዝ ነው፡፡ እገዛው የዕውቀት (የንባብ) ዝግጅትን እና የስነ-ልቦና ዝግጅትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ተማሪዎቹ ለፈተናው ያላቸውን ዝግጅት በሚወስዱት ቅድመ ፈተና ገምግመው ራሳቸውን እንዲመለከቱ ሲያደርግ፤ በአነቃቂ ንግግሮች እና በታዋቂ ሰዎች ምክር ደግሞ ተፈታኞች የቅድመ ፈተና ፍርሃት፣ ጭንቀትና ግራ መጋባትን እንዲያስወግዱ የሚረዱ ምክሮችን ያጋራል። 

ፈተና ኔት ከዋናው ፈተና በፊት አንድ ወር ቀደም ብሎ በራሱ አባላት ያዘጋጀውን ፈተና የቴሌግራም “ቻናሉ” አባል (ሰብስክራይበር) ለሆኑ ተማሪዎች በኢንተርኔት ይሰጣል፡፡ እንደ ሐሳቡ ጠንሳሾች እምነት የዋናውን ፈተና “ሞዴል” ተጠቅሞ የሚሰናዳው ፈተና ወላጆችን እና ተፈታኝ ተማሪዎችን በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ባሳለፍነው ወር ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ ሥራ መጀመሩን በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች ያሳወቀው ፈተና ኔት ለተመዝጋቢ ተፈታኞች ፈተናውን የሚሰጠው ከመስከረም 10 ጀምሮ ባሉት 4 ተከታታይ ቀናት መሆኑን አያይዞ አሳውቋል። 

የፈተና ኔት ሃሳብ ጠንሳሽና የቡድኑ መስራች ቢንያም ከፋለ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ ሲሆነ ለዚህ ተግባር ያነሳሳውን ምክንያት ለአዲስ ዘይቤ ሲያስረዳ፡ “ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ ተማሪዎች ለፈተና የሚዘጋጁባቸው አማራጮች የላቸውም፡፡ ትምህርት ቤታቸው ከሚያዘጋጅላቸው የሞዴል ፈተና ውጭ የሚዘጋጁበት መንገድ የለም፡፡ ይህ መሆኑ ያሉበትን ደረጃ ከሌሎች ተማሪዎች አንጻር እንዳይመዝኑ እንቅፋት ሆኗል፡፡ “ፕላትፎርሙ” ለእነዚህ ተማሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስበናል” ይላል፡፡ 

በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሐገር አቀፍ ተፈታኞችን ደረጃ ሊያሳይ በሚችል መልኩ የተሰናዳው ፈተና ለሶሻል ተማሪዎች ከኢኮኖሚክስ በስተቀር ሁሉንም የሃገር አቀፍ ተፈተታኞች ፈተናዎች ይሰጣሉ፡፡

የፈተና ኔት ስራዎችን ቢንያምን ጨምሮ 12 ባለሙያዎች ይሳተፉበታል። የጥያቄዎቹ ብዛትና ደረጃቸው እንዲሁም አቀራረባቸው የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን እንዲመስል በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዳዘጋጁት ቢንያም ይናገራል፡፡ ክፍያ ፈጽመው ለመፈተን የተዘጋጁ ተማሪዎችን እና በሺዎች የሚቆጠሩትን የቻናሉ ተከታዮች ለመለየት እንዲያስችል የተዘጋጀ ቦት እንዳለ እና ችግር እንደማይፈጠር ቢንያም ያክላል፡፡ 

ፈተናው ከዋናው የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በአንድ ወር ቀደም ብሎ የሚሰጥ ሲሆን ውጤት የሚገለጸው በፈተናው የመጨረሻ ቀን ይሆናል፡፡ በውጤት አሰጣጡ ከ575 በላይ ለሚያመጡ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች እና ከ600 በላይ ለሚያመጡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች የማበረታቻ ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ለሚያመጡ ለ3 ተማሪውች ድርጅቱ ታብሌት ይሸልማል።  

አስራ ሁለቱ የቡድኑ አባላት የሥራ ክፍፍል ያላቸው ሲሆን የድርሻቸውን በመወጣት ስራው እንዲቀላጠፍ በመትጋት ላይ ናቸው፡፡ የሦስቱ የቡድኑ አባላት ተማሪዎችን በማነቃቃት በኩል ያለውን ድርሻ የሚወጡ ሲሆን፤ ሁለቱ የአስተባባሪነት ሥራ ይሰራሉ፡፡ የቀሩት ሰባት አባላት ፈተናዎችን በማውጣት እና በማረም ያገለግላሉ፡፡

ወጣት ቢንያም ከፈተናው በተጨማሪ ስለሚኖረው ማነቃቂያ ሲያስረዳ “በርካታ ተማሪዎች በቂ የፈተና ዝግጅት ቢያደርጉም፤ ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ስለማይኖራቸው ውጤታቸው ይበላሻል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ተፈታኞች ከዋናው ፈተና አንድ ሳምንት በፊት የባለሙያ እገዛ እንዲያገኙ እናደርጋለን” ይላል፡፡

ተማሪዎቹ ፈተናቸውን በራስ መተማመን መንፈስ እንዲሰሩ ያስችላል የተባለውን የማነቃቂያ ንግግርና የልምድ ልውውጥ ከሚሰጡት መካከል የ“ጎበዝ ተማሪ” ዩትዩብ ቻናል መስራችና የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር የሆነችው ሶስና አብዮት፣ የ“ቀሰም አካዳሚ” የቴሌግራም ቻናል መስራች አቶ ቻላቸው አሰፋ፣ የ“የኛ” ራድዩ ድራማና ቶክ ሾው አዘጋጅ የነበረችውና የሕይወት ክህሎት አሰልጣኟ ወጣት እቴነሽ አሰፋ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በ2012/13 ዓ.ም. የማትሪክ ፈተና ወስደው ከ600 በላይ በማምጣት ምርጥ 10 ውስጥ የገቡ ተማሪዎች ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ፡፡ በየአንድ ቀኑ ልዩነት በሳምንት 4 ቀን ጧት የሚለቀቀው የማነቃቂያ ንግግር “በቴሌግራም ቻናሉ” በድምጽ ቅጂ ይሰራጫል፡፡

ሐገር አቀፍ ፈተናውን የመውሰድ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በቴሌ ብር፣ ሲቢኢ ብር፣ አሞሌ ወይም በአዋሽ፣ በንግድ፣ በአቢሲንያ ባንኮች በተከፈቱ አካውንቶች ክፍያ መፈጸም ይገባቸዋል፡፡ በመረጡት አማራጭ የ25 ብር ክፍያ የፈጸሙ ተማሪዎች ሁሉንም የቻናሉን አግልግሎቶች ማግኝት ይችላሉ፡፡ የማነቃቂያ ንግግሮቹን ጨምሮ በማኅበራዊ ሳይንስ ወይም በተፈጥሮ ሳይንስ የተዘጋጁት ሁሉም ፈተናዎች ይላኩላቸዋል፡፡ 

የፈተና ኔት የቴሌግራም ቻናል 50,000 ያህል ተፈታኞች እንደሚያስተናግድ ግምታዊ ቁጥር አስቀምጧል የሚሉት አዘጋጆቹ ይህ ጽሑፍ እስከተሰናዳበት ቀን ድረስ 200 ያህል ተፈታኞች ክፍያውን ፈጽመው የፈተናውን ቀን በመጠባበቅ ላይ ስለመሆናቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡ ከተመዝጋቢዎቹ መካከል 25% የሚሆኑት ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ ተማሪዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል። 

የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎችን በመስጠት በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ስራውን የጀመረው “ፈተና ኔት” የ8ኛ እና የ10ኛ ክፍልን ጨምሮ ሁሉንም ሐገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎችን የመስጠት እቅድ እንዳለው መስራቾቹ ይናገራሉ። የቴሌግራም ቻናሉን ወደ ሶፍትዌር በማሳደግ የሞባይል መተግበሪያ የማበልጸግ ሐሳብ መኖሩንም አክለዋል። ዓመቱን ሙሉ በሚኖረው የትምህርት እንቅስቃሴም አጋዥ ትምህርታዊ ዝግጅቶችን ለመስጠት ሐሳብ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

አስተያየት