“የደብረታቦር በዓል ከዘጠኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡” ይላሉ ዶክተር ሮዳስ በጡመራ ገጻቸው፤ የሐይማኖቱ አባቶች እንደሚያስተምሩት በማቴ 17፡1-9 ላይ እንደተገለጸው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ስምንቱን ሐዋርያት ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዞ ወደ ታቦር ተራራ በመውጣት የሞተውን ሙሴን ከ1644 ዓመታት በኋላ አሥነስቶ፣ የተሰወረውን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ፣ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው እርሱ መኾኑን ብርሃኑ የገለጸበት ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡
የደብረታቦር በዓል ከነሐሴ 12 ምሽት እስከ 13 ይከበራል፡፡ የወንዶች ልጆች የሆያ ሆዬ ጭፈራ ግን እንደየ አካባቢው ይለያያል፡፡ ከነሐሴ የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ እስከ መስከረም አጋማሽ ወይም የመስቀል በዓል ድረስ ይዘልቃል፡፡ ደብረ ታቦር በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡
አቶ ሔኖክ ያሬድ የዐዲስ ዓመት ዘፈኖችን በተመለከተ ጽሑፋቸው ይህ ትውፊት በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅና በሰሜን ምዕራብ ይታወቃል ይላሉ፡፡ ሆያ ሆዬ በማንኛውም ጊዜ የሚዘወተር ባህላዊ ጨዋታ ሳይሆን ወቅትን ጠብቆ የሚከወን እንደመሆኑ፤ ከአደይ አበባ ጋር ያመሳስሉታል፡፡ በአገራችን የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት ‘ቡሄ’ የሚለውን ስያሜ አገኘች። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡
ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት
ቡሔ ካለፈ የለም ክረምት… እንዲሉ
በ‘ኢታንጀብል’ ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ጥራዝ ውስጥ፣ የሆያ ሆዬ በዓል መስከረም 1 ጀምሮ በ17 የሚጠናቀቅባት ላስታ መስከረም ላይ ምን እንደምትመስል ያብራራል፡፡ በመስከረም ላስታ ላሊበላ ዙሪያዋ ያምራል፣ አካባቢው ያብባል፣ እህሉ ይሸታል፣ አዝመራው ይደርሳል፣ ወንዙ ይጠራል፣ ፏፏቴው ይወርዳል፣ መሬቷ ታሸበርቃለች፣ ፍጥረት ትስቃለች፣ ምድር ትፈነድቃለች፤ የወጣቱ ልብም ይደሰታል፣ ፊቱ ያብባል፣ ገጹ ይፈካል፡፡ የላስታ ወጣት ይህን ስሜቱን ከሚገልጽበት ሕይወቱን ከሚያድስበትና ደስታውንም ከሚያካፍልበት አንዱና ዋናው “ሆያ ሆዬ” ነው፡፡
የሥነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) እና የነገረ ባህል (ፎክሎር) ተመራማሪዎቹ የቅርስ ባለሙያዎች እንደዘገቡት የሆያ ሆዬን ግጥሞች የአሰነኛኘት ሁናቴ በ4 ይከፍሉታል፤ የጉዞ (የመንገድ)፣ የምስጋና፣ የምርቃት፣ የቅሬታ፡ በሚል…
የጉዞ/የመንገድ
የመጀመርያው የጉዞ/የመንገድ ግጥም የሚባለው ወጣቶች ገና አባወራው ቤት ከመሄዳቸውና “ሆያ ሆዬ” ከማለታቸው በፊት የሚጠራሩበትንና የሚገጥሙትን በየመንገዱም “እሆይ ሲራራ፣ እሆይ ሲራራ” (እንደየ አካባቢው ይለያያል) የሚሉትን የዜማ/ግጥም ዓይነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “እንኳን አደረሳችሁ” ወደሚሉበት ቤት ገና ሳይገቡ ከአጥሩ/ግቢው ትንሽ ራቅ ብለው የቤቱ ጌታ ወይም ጠባቂ በሩን ከፍቶ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቃቸው የሚያባብሉበት ዜማና ግጥም በዚሁ ይካተታል፡፡
ቡሄ በሉ፣
ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ፤
ያ መላጣ
ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ
ይህ በየመንገዱ የሚባል ነው፡፡ ወደ ሚጨፈርበት ቤት ሲደርሱ ደግሞ…
ክፈት በለው በሩን
የዚያን ወንዱን፣
ክፈት በለው ተነሳ
የወንዱን ጎረምሳ
ክፈት በለው በሩን
የጌታዬን
መጣና መጣና
ደጅ ልንጥና
እያለ ከነ አጀቡ ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሆያ ሆዬ ተጨዋቾች ዓመቱን ጠብቀው እንኳን አደረሳችሁ ለማለትና የደንቡን ለመጠየቅ መምጣታቸውን የሰማ አባወራም ቤቱን በመክፈት ጭፈራውንና ሁኔታውን በሚገባ ይከታተላል፡፡ የሚገባውንም ስጦታ ያዘጋጃል፡፡ ስጦታውም የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ በገጠሩ እርጎ፣ ጋን ጠላ ከነመክደኛው /ዳቦ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ሙክትም የሚሰጥ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ገንዘብ ይሰጣል፡፡
ሁለተኛው የምስጋና ነው፡፡
ማር ይዘንባል ጠጅ
ከጌታዬ ደጅ
ከመቤቴ ደጅ
አሆሆ በል እረኛ
በጊዜ እንተኛ፤
ይኸ የማነው እንዝርት እመከታው ላይ
ይቺ የኔ እመቤት የቀጭን ፈታይ
እሷ ፈትላ ባሏ መልበስ ያውቃል
ይኼ የኔ ጌታ በሩቅ ያስታውቃል፡፡
ይሔ የማነው ቤት - የኮራ የደራ
የማምዬ ነው ወይ የዛች የቀብራራ
የአባብዬ ነው ወይ የዚያ የቀበራራ
ይህ የግጥሙ ክፍል ከሌሎቹ ረዘም የሚለው ነው፡፡ በሙያ፣ በችሎታ፣ በመልክ፣ በጸባይ የቤቱ ባለቤት ይመሰገንበታል፡፡ ሻል ያለውን ስጦታ እንዲሰጥም ግፊት ይደረግበታል፡፡
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
ባለ ቦቃ ነው ባለ ምክልት
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ።
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታዉ ይጣራል ገመገም ዞሮ
የኔማ እመቤት የጋገረችው
የንብ እንጀራ አስመሰለችው።
ግጥሙ መስከረም ከመጥባቱ በፊት ቡሔን በሚያከብሩት ዘንድ እንደሚዘወተር ያሳያል፡፡
የወንዜው ነብር የወንዜው ነብር
የኛማ ጌታ ሊሰጡን ነበር።
ለብሩ ነወይ ነወይ ሽርጉዱ
በአባትህ ጊዜ ሰንጋ ነው ልምዱ
ሦስተኛው ምርቃት ነው፡፡
ስጦታው ከተከናወነ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ስጦታው የማይሰጥ ከሆነ አይኖርም፡፡
ዓመት አውደ ዓመት
ያባብዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት
እዚህ ቤት
ይግባ በረከት
በሆያ ሆዬው ላይ የሚንፀባረቁት የቅሬታ ግጥሞች በአራተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡት ናቸው፡፡ እነዚህ የቅሬታ ግጥሞች አጠርና ደመቅ ባለ የዜማ ሥልት የምስጋናውን መልዕክት ካጠናቀቁና ከጨፈሩ በኋላ ስጦታው የሚዘገይ ወይም የሚያንስ ከሆነ ቅሬታቸውን በግጥም ማሰማት የተለመደ ነው፡፡ ቡሄውን ጨፍረው በጎ ምላሽ ካላገኙ፣ ካልተሸለሙ፣ በግጥማቸው በመጎሸም ብቻ አይወሰኑም፡፡ “ቀበራ” የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ (ላሊበላ እና ትግራይ አካባቢ በብዛት አለ) ማዶ ለማዶ እየተጯጯሁ ባልሰጧቸው ሰዎች ላይ አደጋ እንደደረሰ አድርገው በቅብብሎሽ ያስተጋባሉ፡፡
“እከሌ ተጎድቷል - ድረሱ” እያሉ መርዶ ይናገራሉ (ተጎዳ ማለት ሞተ ማለት ነው)፡፡ ይኼን መርዶ የሰማ በቅርብም በሩቅ ያለ ዘመድ ፀጉርን እየነጨ እያለቀሰ ሲመጣ ጉዳዩ ሌላ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ቡሄ፡፡ ሞተ ለተባለው ዘመዳቸውም “ምነው አንድ ብር አትሰጥም አፈር በበላህ” ይሉታል፡፡ ይህም ሆኖ በቅሬታቸው ዜማውን ለውጠውና ከግጥሙ ጋር አዋህደው ሲያቀርቡ ቅሬታ ተሰማኝ ብሎ የሚያኮርፋቸው አይኖርም፡፡
ማኅበራዊ ፋይዳ
የሆያ ሆዬ ጨዋታ በየዓመቱ በደስታ ተከብሮ ብቻ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለጨዋታው የሚሰባሰቡ ወጣቶች የማኅበራዊ ሕይወት ትስስር መሠረት ይጥሉበታል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ የስብስብ ሒደቱ ወደ ሚዜነት የሚያድግብት፣ የሚዜነት ተግባሩም ለጊዜው ሳይሆን ሁሉም እስኪያገቡ ድረስ በዘላቂነት የሚቀጥሉበት፤ አግብተው ሲጨርሱም ማኅበራዊ ቁርኝቱ የሚዳብርበት፣ የጽዋ ማኅበር የሚጠጡበት/የሚዘክሩበት፣ አብረው የሚበሉበት/ የሚጠጡበት፣ በደቦና በወንፈል እየተረዳዱ የሚሠሩበት፣ ይህም በእነሱ ሕይወት ብቻ ሳይወሰን በልጆቻቸው የሚቀጥልበት እንደሆነ የአካባቢው የባህል አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
“ሆያ ሆዬ የማኅበራዊ ትስስር መፍጠሪያነት ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ አገልግሎት ሚና በልጅነት ሙከራ የሚደረግበት ማለትም መሪ ለመሆን የሚችለው- አለቃ፣ ታማኝ የሆነው- ገንዘብ ያዥ፣ ልሳነ ወርቁ- አቀንቃኝ (አውራጅ)፣… ሆኖ ወጣቶች ለቁም ነገር የሚታጩበትም ጭምር ነው፤” የሚለው ሰነዱ፣ ከዚህ በተጨማሪ በጨዋታው ግለሰቦች በመልካም ሥራቸውና ሙያቸው በግጥም የሚወደሱበት በተቃራኒው- ፍርኃት፣ ስንፍና፣ ሙያ ቢስነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ጊዜን አልባሌ ሥፍራና ቦታ ማሳለፍ የሚነቀፍበት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
የሆያ ሆዬ ጨዋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት የሚጀምረው ዕለተ በዓሉ ከመከበሩ አስቀድሞ ነው፡፡ ጊዜው እንደየ አካባቢው ይለያያል፡፡ ለዝግጅቱ ወጣት ወንዶች ወንዝ እየወረዱ ገላቸውን ይታጠባሉ፣ ልብሳቸውን ያፀዳሉ፣ ለጭፈራው ዋና መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን ዱላ ያዘጋጃሉ፡፡ ለጨዋታ የሚያስፈልጋቸውን ግጥምም ያጠናሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አለቃና ገንዘብ ያዥም ይመርጣሉ፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች ከመስክ ጥናታቸው በመነሳት እንደሚገልጹት፣ የሆያ ሆዬ ባህላዊ ጨዋታ በአንዳንድ አካባቢ እየተረሳና እየቀዘቀዘ አንዳንድ ጊዜ በዜማውና ግጥሙ እየተዛባ ይምጣ እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በዘመናዊ መልክ የተሰሩትን የሆያ ሆዬ ዘፈኖች ስንመከለት ደግሞ ተከታዮቹን መልኮች እናገኛለን፡፡ መጀመሪያዎቹ ራሱን ቱባውን የቀድሞ ባህል የዘፈኑ ናቸው፡፡ ታሪክን ከማቆየት እና ነባሩን እንደነበረ ከማስተላለፍ አንጻር ሰፊ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የሰለሞን ደነቀ (ነፍስ ይማር) ዘፈን ለዚህ ብርቱ ምሳሌ ነው። በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚካተቱት በርከት ያለ ቁጥር አላቸው፡፡ እነዚህኞቹ የልጅነት ፍቅራቸውን በሆያ ሆዬ በኩል ያስታውሳሉ፡፡ መዝሙር ዮሐንስ፣ ነዋይ ደበበ፣ ተስፋዬ ታዬ ይገኙበታል።