በኢትዮጵያ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች ክምችት ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዘርፉ ችግሮች መካከል በቀላሉ ለመለየት የሚያዳግቱ ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶች በገበያው በብዛት መኖር እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች ስርጭት መጨመር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእጥረት፣ ጥራትና ስርጭት ጎን ለጎን በአወጋገድ በኩል ያለው ተግዳሮትም እንደገዘፈ ይገኛል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የ2020 ሪፖርት እንደሚያመለክተው በጤና ማዕከላትና በሆስፒታሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ከፍተኛ መጠን ያላቸው መድኃኒቶች ይገኛሉ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እንደ ሐገር ከፍተኛ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ስርጭት እንደሚያሰጋው በኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ትብብር እአአ በ2017 የተካሄደው ጥናት ያሳያል፡፡
የመድኃኒት ጥራት ጉዳይን መሠረት በማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት የ100 ግለሰቦችን ጉዳይ መርምሮ እንዳገኘው ውጤት ከሆነ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በአማካይ 10.5 በመቶ የሚሆኑት በስርጭት ላይ የሚገኙ መድኃኒቶ የጥራት ደረጃቸው የወረደ ወይም የሀሰት መሆናቸውን አመላክቷል።
የፋርማሲ ባለሙያው አቶ ደረጀ ሰጠኝ የጥናቱን ግኝት ሲያብራሩ “ደረጃቸው የወረደ እና የሀሰት መድኃኒቶች ስርጭት የመስፋፋታቸው ሰበብ ለሰው ሕይወት ደንታ የሌላቸው ወገኖች በመበራከታቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የገንዘብ ትርፍን ብቻ የሚመለከቱት የተቋማት መሪዎችና አስመጪዎች መድኃኒትን እንደ ተራ ሸቀጥ መመልከታቸው፣ በዘርፉ ያለው ዕውቀት አናሳ መሆኑ፣ የሕግ አፈፃሚዎች ድክመት፣ መድኃኒት የማግኘት ዕድል መጥበብ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የመሳሰሉት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች መስፋፋት መንስኤ መሆናቸውን ይጠቀሳሉ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ኮሌጅ በተካሄደው እና በ2020 በምርምር መጽሔት ለህትመት በበቃው “Assessment of Prescription Completeness and Drug Use Pattern in Tibebe-Ghion Comprehensive Specialized Hospital, Bahir Dar, Ethiopia” ጥናት መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በአፍሪካ ሐገራት የሚገኙ ዜጎች ጤናቸውን ለመጠበቅ ርካሽ መድኃኒቶችን የመምረጥ አዝማሚያቸው ከፍተኛ መሆኑን ያስቀምጣል።
እንደ ጥናቱ ድምዳሜ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ስህተት የሚያጋጥመው በወባ እና ‘አንቲባዮቲክ’ መድኃኒቶች ሲሆን የሚያስከትሉት ጠንቅም የከፋ ነው። ለዚህም ይሆናል ትክክለኛውን መድኃኒት በማግኘት ሊፈወሱ የሚችሉት ወባ እና ባክቴሪያ አመጣሹ ሳምባ ምች እስከ ሞት የሚያደርስ ጥፋት እያደረሱ የሚገኙት፡፡ የጥራት ደረጃቸው በወረደና በሀሰት መድኃኒቶች ምክንያት በየዓመቱ በወባ በሽታ 267 ሺህ፣ እንደ ሳምባ ምች ባሉ ሕጻናት እና ታዳጊዎችን የሚያጠቁ ህመሞች 20,225 ሕፃናት ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሃገራት እንደዋዛ ህይወታቸው እንደሚቀጠፍ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት ጥራታቸው ዝቅተኛ የሆነና የሀሰት መድኃኒቶች መነሻ አብዛኛውን ጊዜ ቻይና እና ከህንድ ናቸው።
አቶ ሰለሞን ጣዕምአለው በባህርዳር የግል መድኃኒት ቤት ባለቤት ናቸው፡፡ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ሲገልጹ “በእኛ አካበቢ መንግሥት ለገበያ የምናቀርባቸውን መድኃኒቶች ጥራት የሚከታተለበት አሰራር አልተዘረጋም፡፡ በየመድኃኒት መሸጫው ድንገተኛ እና ተከታታይ የመድኃኒት አቀማመጥ፣ አያያዝ፣ አቀራረብ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ቁጥጥር አይደረግም” ብለዋል፡፡
የፋርማሲ ባለሙያዋ ሰናይት አልታሰብ በበኩሏ “የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው” ስትል አሰተያየቷን ሰጥታለች፡፡ የመድኃኒቶቹን መሸፈኛ ካርቶን መቀየር እና ላዩ ላይ የተለጠፈውን ወረቀት የመቀየር ያህል ቀላል በመሆኑ የፈውስ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ለሽያጭ ሊቀርቡ እንደሚችሉ እና ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶች ውስጥ ለውስጥ እንደሚከፋፈሉም ትናገራለች፡፡
ያብባል ጥላሁን የተባለ ባለሙያ በበኩሉ “እኛ ሀገር ጥራት የሌለው መድኃኒት ለመሸጥ በጣም ቀላል ነው። ምክንያቱም ቁጥጥሩ የለም የሚባል ስለሆነ፤ ከሌላ ቦታ አምጥቶ ዝም ብሎ መሸጥ ይቻላል። ማንም የመጣለትን መድኃኒት ይሰጣል እንጅ የመድኃኒቱን ጥራት አይመረምርም፡፡ የጅምላ መድኃኒት ሻጩም ተመሳሳይ ነው። ጥርጣሬ ኖሮህ ‘ሴንትራል ላቦራቶሪ ወስጀ አስመረመራለሁ’ ብትል መመርመሪያውም የለንም።” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡
እንደ አቶ ጌትነት ተሻለ ገለጻ መድኃኒቶች በተጠቃሚዎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከከፋ የአካልና የአዕምሮ ጤና ችግር እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ አቶ ጌትነት የፋርማሲ ባለሙያ ነው፡፡ “መድኃኒቶች በተመረቱበት ሐገር ወይም በ‹ብራንዳቸው› ስያሜ ብቻ በገበያው ላይ የተጋነነ የዋጋ ልዩነት መኖሩ ለታካሚው ራስ ምታት ነው” ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ
የተለያዩ ዓይነት መድኃኒቶች ወደ ሀገራችን ሲገቡ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ዝቅተኛ እንደሆነ ያሳያል፤ ይህ መሆኑ የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ ተመሳስለው የተሰሩ ምርቶች ገበያውን እንዲያጥለቀልቁት አድርጓል ባይ ነው፡፡
የድርጊቱን ውጤት መገመት ቀላል ነው፡፡ ለፈውስ የወሰዱት መድኃኒት ተጨማሪ ከባድና ውስብስብ የጤና ችግር ሊያስከትል ወይም ሕይወትን ሊያሳጣ የሚችልበትን አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡
እንደ አሜሪካው የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥር ቢሮ ሪፖርት በአሜሪካ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥር 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ መድኃኒቶች ተገኝተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በእንግሊዝ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻ በአገሪቱ ተመርተው ገበያ ውስጥ ከተሠራጩ መድኃኒቶች መካከል ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተመሳስለው የተሠሩ መድኃኒቶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሀገራቱ እነዚህን ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በመሰብሰብ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች ውስጥ ስምንት በመቶ ያህሉ የሚገኙት በጤና ተቋማት ሲሆን፤ ሦስት በመቶው በግል የመድኃኒት መሸጫ ጣቢያዎች፣ ሁለት በመቶ በክልል የመድኃኒት መደብሮች ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ መድኃኒት ዘርፍ ግምገማ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ የተከናወነ ሲሆን ግምገማውን በማዕከላዊ አስተባባሪነት አቶ ዓለማየሁ ለማ፣ የፋርማሲ አስተዳደር ኃላፊ እና የMOH የአቅርቦት አገልግሎት (PASS) አሰተባባሪ አቶ በቀለ ተፈራ፣ የብሔራዊ ፕሮፌሽናል ኦፊሰር (NPO) የዓለም ጤና ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅ እና የመድኃኒት ፖሊሲ (EDM) ፕሮግራም ባለሙያ ወ/ሮ ሀዳስ አዱኛ አጥንተውታል፡፡
በዚህ የዓለም የጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ሪፖርት መሰረት ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች በቅደም ተከተል ሲቀመጡ በጤና ተቋማት 8%፣ በክልል የመድኃኒት መደብሮች 2%፣ በግል የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች 3% ናቸው። አጥኝዎቹ በውጤቱ በጤና ተቋማት እና በክልሎች መካከል የታየው ከፍተኛ ልዩነት ጉዳዩ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች በኢትዮጵያ በተለይም በስድስት የተመረጡ ክልሎች ላይ በተካሄደው ፍተሻ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈበት መድኃኒት የሚገኝበት ቦታ በ38% የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡ በተሻለ የመድኃኒት አቅርቦት እና ጥራት የሚገኝው ክልል በ3% አነሰተኛ ክምችት የትግራይ ክልል መሆኑን ጥናቱ ዐሳይቷል፡፡ ይህ ማለት በአንጻራዊ ሁኔታ የመድኃኒት ጥራት በትግራይ ክልል የተሻለ ሲሆን በቤኒሻንጉል−ጉሙዝ ክልል ግን በከፍተኛ ሁኔታ ማኅበረሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜ ላለፈባቸው መድኃኒቶች እንደተጋለጠ አመላካች ነው፡፡
ምንጭ፡- በኢትዮጵያ የመድኃኒት ዘርፍ ግምገማ በPASS ከዓለም ጤና ድርጅት በአምስት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት (ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) እና አዲስ አበባ 7 ሆስፒታሎችን፣ 19 ጤና ጣቢያዎችን፣ 85 ጤናን ማዕከላትን፣ 5 የክልል የPHARMID የመድኃኒት መደብሮችን፣ 24 የግል ፋርማሲዎችን እና 490 አባወራዎችን ያካተተ ጥናት አካሂዶ ያወጣው የማጠቃለያ ውጤት መግለጫ።
በአጠቃላይ የጥናቱ ግኝት ዕደሚያሳየው በጤና ተቋማት ደረጃ ሲወዳደሩ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች በሆስፒታሎች ውስጥ 13.1 በመቶ፣ በጤና ማዕከላት 9.7 በመቶ እና 7.5 በጤና ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ፡፡ ይህም በአመዛኙ የጥናቱ ቁጥሮች የሚናገሩት የመድኃኒት ጥራት በአንጻራዊነት በጤና ጣቢያዎች ውስጥ የተሻለ ሲሆን በሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኘው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ስብጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው።
በስድስቱ ክልሎች ውስጥ በሐገሪቱ በአስፈላጊነታቸው ተለይተው ለጤናው ዘርፍ ምላሽ እንዲሆኑ መገኝት ከሚገባቸው ቁልፍ አስፈላጊ መድኃኒቶች ውስጥ በአማካይ 90 በመቶ በትግራይ ክልል ይገኛሉ፡፡ በዝቅተኛ ሁኔታ አስፈላጊ መድኃኒቶች የማይገኙበት ክልል በ65 በመቶ ድርሻ የአማራ ክልል ነው፡፡
የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለማሳየትና መፍትሔውን ለማመላከት በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በመድኃኒትና ሕክምና መገልገያዎች ክምችትና ስርጭት አፈጻፀም ላይ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ዕንደሚያሳየው፤ ኤጀንሲው የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ከአገር ውስጥም ሆነ ከዉጪ ሐገራት ገዝቶ የሚያቀርባቸው መድኃኒቶች ከዓመታት በፊት ከ700 ሚሊዮን ብር በታች የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 40 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ኤጀንሲው በመላ ሀገሪቱ መድኃኒትና የህክምና መገልገያዎችን ለማሰራጨት እንዲረዳው አስራ አንድ ቅርንጫፎችን በተለያዩ አካባቢዎች (አዲስአበባ፣ ሐዋሳ፣ ደሴ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ ደምቢዶሎ፣ ድሬዳዋ፣ መቐለ) በመክፈት ለመንግሥትና ለግል ጤና ተቋማት መድኃኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
በተለያዩ የመንግሥት ሕክምና መስጫ ተቋማት ዕንደታየው፤ የመድኃኒት አቅርቦት ከጊዜ ወደ መሻሻል ቢያሳይም፤ የአቅርቦት መቆራረጥ ችግር አሁንም አለ፡፡ በተለይ በኬሚካሎችና ላብራቶሪ ሪኤጀንቶች (Chemicals and lab-reagents) አቅርቦት ረገድ ያለው እጥረት ከፍ ያለ ነው፡፡ በተጨማሪም በጤና ተቋማት ኤጀንሲው የተጠየቁትን መድኃኒቶች ሙሉ ለሙሉ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በባህርዳር በፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል በተደረገ ጉብኝት በሆስፒታሉ መድኃኒት ማከማቻ መጋዘን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ተብለው ከተለዩት ውስጥ 42 ዓይነት መድኃኒቶች በክምችት ክፍሉ ውስጥ አልነበሩም፡፡
ሀገራዊውን ከፍተኛ የመድኃኒት እጥረት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ተግዳሮት ናቸው ተብለው ከተዘረዘሩት ነጥቦች ውስጥ ከዋና መ/ቤት ለቅርንጫፎች የሚመደበው በጀት ከረጂ ድርጅቶች የሚገኝ በመሆኑ በጀቱ በተፈለገው ጊዜ አለመለቀቁ፣ የመድኃኒቶች፣ ኬሚካሎች እና የላቦራቶሪ ሪኤጀንቶች አቅርቦት ላይ መቆራረጥ መኖሩ፣ ጤና ተቋማት መድኃኒቶችን ከግል አቅራቢዎች እንዲገዙና በመድኃኒት ግዥ ሥራ እንዲጠመዱ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በመንግሥት ጤና ተቋማት የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ክምችትን በተመለከተ በኤጀንሲው በኩል የሚካሔደው ክትትልና ቁጥጥር የተጠናከረና ወጥ የጊዜ ሰሌዳ ያልተዘጋጀለት መሆኑ ኤጀንሲው በተቋማቱ ውስጥ የሚዘወተሩትን ችግሮች ለይቶ የማሻሻያ ሃሳቦች እንዳይሰጥና በጤና ተቋማት ያልተገባ የመድኃኒት ክምችት እንዲኖራቸው ምክንያት ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በተለይም ከመድኃኒት ስርጭት ጋር በተያያዘ በመላ ሃገሪቱ ያሉት መረከቢያ፣ ማከማቻና ማስረከቢያ መጋዘኖች ለአገልግሎት የሚውሉ አስፈላጊ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች (የሙቀት መለኪያዎች፣ ፎርክሊፍት፣ ጋሪ፣ ፓሌት፣ የማሸጊያ ቁሳቁሶች ወዘተ) አልተሟሉም፡፡
የኤጀንሲው ኃላፊዎች ስለጉዳዩ እንዳብራሩት፣ ከመንግሥታዊ የህክምና መስጫ ተቋማት መካከል ከ15 በላይ በሚሆኑ ተቋማት የመድኃኒት መጋዘኖች ውስጥ ለ‘ናርኮቲክ’ና ‘ሳይኮትሮፒክ’ መድኃኒቶች የተለየ ማስቀመጫም ሆነ የተለየ ባለሙያ የላቸውም፡፡ አንዳንዶችም የበር ቁልፋቸው የተበላሸ ነው፡፡ በተለይም ተለይተው በጥንቃቄ መቀመጥ ያለባቸው መድኃኒቶች ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ተቀላቅለው ያለጥንቃቄ መከማቸታቸው ተገቢና ጥንቃቄ የተሞላበት የመድኃኒት ክምችት ስርዓት እንዳይኖር አድርጓል፡፡
ኤጀንሲው ባካሄደው ፍተሻ የነቀምት፣ የጅማ፣ የባህርዳር፣ የደሴ እና የአዲስ አበባ የኤጀንሲው ቅርንጫፎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶችን ለማስወገድ ቋሚ የሆነ የማስወገጃ የጊዜ ሰሌዳ ካለመኖሩም በተጨማሪ በጋምቤላ፣ በደሴ፣ በፈለገ ህይወት ሆስፒታሎች እንዲሁም በኤጀንሲው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በዓይነት የተለያዩ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ጥቅም ሳይሰጡ እና በኮሚቴ ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ሳይወገዱ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በሌላ የመድኃኒት ዓይነት ተተክተው ግልጋሎት እንዳይሰጡ የታገዱ ነገር ግን የአገልግሎት ገደባቸው ያልተጠናቀቀ የፀረ-ኤችአይቪ እና የቲቪ መድኃኒቶች ከኤጀንሲው የመፍትሄ አቅጣጫ ስላልተቀመጠላቸው ጥቅም ሳይሰጡ በመራዊ ጤና ጣቢያ በስፋት ተከማችተው ተገኝተዋል፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች በመመሪያው ላይ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አለመወገዳቸው እንደ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል እና የኤጀንሲው አዲስአበባ ቅርንጫፍ ባሉ ተቋማት የማያገለግሉ መድኃኒቶች ክምችት እንዲፈጠርና ለማስወገድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም በቅርንጫፎችና በጤና ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ጥቅም የማይሰጡ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ለጉዳዩ ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ አለመወሰዱ መሳሪያዎቹ ወደ ሌላ ተቋም ተዛውረው ጥቅም ሊሰጡ የሚቻልበትን ዕድል ዘግቷል፡፡ በተጨማሪም አግልግሎት ላይ መዋል የማይችሉት መድኃኒቶች በአግባቡ እንዳይወገዱና የማከማቻ ቦታ ጥበት እንዲፈጠር አስገድዷል፡፡
ለጤና ተቋማት የሚመደቡት መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ወደ ተቋማቱ ስለመድረሳቸው የሚረጋገጥበት ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ይህ መሆኑ ሆስፒታሎችን ኪሳራ ላይ ጥሏል፡፡ ለምሳሌ እንደ በአዲስ ህይወት ሆስፒታል በብር 110,000፣ በአሶሳ ዞን ጤና ጽ/ቤት በብር 197,575፣ በዓባይ ጤና ጣቢያ በብር 38,429፣ በባህርዳር አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት በብር 23,436፣ በማሻ ጤና ጣቢያ በብር 46,000 እና በገንጂ ጤና ጣቢያ በብር 113,702 የሚያወጡ መድኃኒቶች ወደ ጤና ተቋማቱ ሳይደርሱ ሊጭበረበሩ ሲሉ ተይዘው ጉዳዩ በሕግ ዕንደታየ ባለፉት ዓመታት የወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡
ለናሙና ከተመረጡት የመንግሥት የህክምና መስጫ ተቋማት መካከል በነቀምት ቅርንጫፍ ስር ለጉቴ ጤና ጣቢያ፣ ለኡኬ ጤና ጣቢያ አና ለነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲሁም በጅማ ቅርንጫፍ ስር ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለአጋሮ ጤና ጣቢያ፣ ለሰርቦ ጤና ጣቢያ፣ ለቦንጋ ጤና ጣቢያ፣ ለጋምቤላ ጤና ጣቢያ እና ለጋምቤላ ሆስፒታሎች የሚላኩት መድኃኒቶች ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ በደሴና ባህርዳር ቅርንጫፍ ግልጋሎት ላይ የሚያገኙ ጤና ተቋማትም መድኃኒቶችን በግዴታ እንዲወስዱ ሆኗል፡፡