ነሐሴ 12 ፣ 2013

የዋጋ መናር እና የአቅርቦት እጥረት

City: Gonderጤና

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ግሽበት አማካኝነት ከተጋፈጠቻቸው ትልልቅ ተግዳሮቶች መካከል የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እጥረት አንዱ መሆኑን በተለያየ ጊዜ የሚወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

Avatar: Ghion Fentahun
ግዮን ፈንታሁን

የዋጋ መናር እና የአቅርቦት እጥረት

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ግሽበት አማካኝነት ከተጋፈጠቻቸው ተግዳሮቶች መካከል የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እጥረት አንዱ መሆኑን በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በማኅበረሰቡ በኩልም ተደጋጋሚ ምሬቶች ይታያሉ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከሚያስፈልጋት የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ዓመታዊ ፍላጎት መካከል ከ85% የበለጠውን ከውጭ እንደምታስገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።

ከነሃሴ 1 እስከ 3 በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው 4ኛው ዓመታዊ የመድኃኒት የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ «በ2013 ዓ.ም. የመድኃኒት አቅርቦት በኮቪድና የተለያዩ ምክንያቶች ፈተና ላይ የወደቀበት ወቅት ነበር» በማለት የችግሩን እውነትነት አረጋግጠዋል። የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታትና አቅርቦቱን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። የሚመሩት ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ ከ27 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያ፣ የኬሚካልና ሬጄንት ማሰራጨቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። መንግሥት በአዋጅ ያቋቋመውና በኢትዮጵያ ግዙፉ መድኃኒት አቅራቢ ተቋሙ ለማኅበረሰቡ በበቂ ሁኔታ መድኃኒት ማቅረብ አለመቻሉንም የመንግሥት የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በምሬት ይናገራሉ።

ይህንን መነሻ በማድረግ በጎንደር ከተማ ዕየታዩ ያሉ የመድኃኒት መጥፋትና የዋጋ ንረቱን በተመለከተ አዲስ ዘይቤ መጠነኛ ዳሰሳ አድርጋለች። አቶ መንግሥቱ ዓይቸው በጎንደር ከተማ የሚኖሩ ጡሮተኛ አባት ናቸው። ከረጅም ዓመታት የሚያሰቃያቸው የስኳርና ደም ግፊት ህመም አለባቸው። አቶ መንግሥቱ በሀኪም ትዕዛዝ የስኳርና የግፊት መድኃኒት ይወስዳሉ። «አመጋገቤን በማስተካከልና እንቅስቃሴ በማድረግ የስኳር መጠኔና የደም ግፊቴ በሚፈለገው ልክ ሊወርድ ባለመቻሉ መድኃኒት እንድጀምር ሀኪም አዞልኝ መድኃኒቱን እየተከታተልሁ እገኛለሁ» ይላሉ አቶ መንግሥቱ። አስከትለውም «መድኃኒት በጀመርሁበት ሰሞን መድኃኒቱም እንደ ልብ ይገኛል። ዋጋውም አያማርርም። አሁን ግን መድኃኒቱም ዛሬ ሲገኝ ነገ ይጠፋል። መድኃኒቱ ቢገኝ እንኳ ዋጋው ከአቅሜ በላይ እየሆነ ተቸግሬያለሁ። እንግዲህ አቅሜ እስከፈቀደ እየታገልሁ ነው።» በማለት የሚወስዱት መድኃኒት በሚፈልጉት ወቅት አለማግኘትና የዋጋ ጭማሪው ሌላ ህመም እንደሆነባቸው ይናገራሉ። 

የወ/ሮ ሽታዬ መልካሙ ልጅ የሚጥል በሽታ (Epilepsy) ህመምተኛ ነው። ዕድሜው  የ17 ነው፡፡ በሀኪም የታዘዘለትን መድኃኒት እየወሰደ ይገኛል። መድኃኒቱን ካልወሰደ ይጥለዋል። ወ/ሮ ሽታዬ የልጃቸውን መድኃኒት ለማግኘት ፈተና ሆኖብኛል ይላሉ። «የልጄ መድኃኒት ሲገኝ የአንድ ወርም፣ የሁለት ወርም እገዛለታለሁ። ከጤና ጣቢያ ብዙ ጊዜ አልቋል እንባላለን። ከግል መድኃኒት ቤቶች ከተገኘ ዋጋው ውድ ቢሆንም እንገዛለን። ብዙ ጊዜ ግን መድኃኒቱ አይገኝም። መንግሥት እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶችን በበቂ ሁኔታ ለምን እንደማያቀርብ አይገባኝም» ይላሉ፡፡

የመድኃኒት አቅርቦት ችግር በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ እንደሚንፀባረቅ በተዟዟርንባቸው የመንግሥት ጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያገኘናቸው አገልግሎት ፈላጊ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በግል የመድኃኒት መሸጫ ፋርማሲዎች ላይም መሰል የመድኃኒት እጥረት እንዳለ ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ።

ሰለሞን ጌታነህ በግል ፋርማሲ ውስጥ ተቀጣሪ ባለሙያ ነው። የዋጋውን ንረት እና እንደልብ አለመገኘት አስመልክቶ ሲናገር በአጭሩ «ቅሬታው እውነተኛ ነው» በማለት ይመልሳል። አስከትሎም «እኛ በትዕዛዝ ወረቀት ለመሸጥ የምንፈልጋቸው መድኃኒት እንደበፊቱ በምንፈልገው መጠንና በምንፈልገው ጊዜ ከአከፋፋዮች አናገኝም። ዋጋውም እየተወደደ ነው። እኛ ከአከፋፋዮች ነው መድኃኒት የምናመጣው። አከፋፋዮቹ ደግሞ ከአስመጭዎች። አከፋፋዮቹ ዋጋ ሲጨምሩ እኛም እንጨምራለን። አስመጭዎቹ የውጭ ምንዛሬ በብር የሚገዙበት መጠን ጨምሯል። ድሮ አንድ ዶላር ለመግዛት 35 ብር የሚያወጡ ከሆነ አሁን እስከ 60 ብር ያወጣሉ። ስለዚህ እንደ ቀድሞው 40 ብር ሳይሆን 70 ወይ 80 ብር ይሸጡታል። ይህ ሁኔታ ሰንሰለቱን ጠብቆ እስከተጠቃሚው ይወርዳል። ይህም ሊሆን የሚችለው ዶላሩ ከተገኘ ነው» በማለት መድኃኒት ላይ እጥረቱም የዋጋ ንረቱም እንዳለ ያስረዳል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሙያዊ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጎንድ ቅርንጫፍ በመስራት ላይ ያሉትን ሲኒየር ፋርማሲስቱን አቶ ሀብታሙ ቀለሙን ጠይቀናቸዋል። አቶ ሀብታሙ ቀለሙ የሚከተለውን ሀሳብ አንስተንላቸው ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሰጠውናል።

«መድኃኒት በሕብረተሰቡ ፍላጎት ልክ እየቀረበ አይደለም። ይህ የጎንደር ከተማ ችግር ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ችግር ነው። የኛ ተቋምም ይሄንን ችግር በሚፈለገው ደረጃ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በተቋማችን ለስኳር፣ ለግፊትና ለሚጥል ህመም ህክምና የሚያገለግሉ መድኃኒቶች ክምችታችን ላይ በበቂ መጠን ይገኛሉ። የግል ተቋማትን ሁኔታ አላውቅም። በተለያየ ወቅት የእነዚህ መድኃኒቶች የአቅርቦት መቆራረጥ የለም ማለት ግን አይቻልም። በአጠቃላይ ለችግሩ መከሰት አንድ ነጠላ ምክንያት ብቻ መጥቀስ አይቻልም። ጥቂቱን ለመጥቀስ ያክል ከኮቪድ መከሰት ማግስት በዓለምአቀፉ ንግድ ላይ የተፈጠረው ጫና ያስከተለው የአቅርቦት እጥረትና የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለበት መሆኑ፣ ለሀገራችን ፍጆታ የሚውል መድኃኒት ሀገር ውስጥ አለመመረቱ ይገኙበታል፡፡ እንደሚታወቀው ከ85% በላይ መድኃኒት ከውጭ የምናስገባው ነው። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መፈለጉ ሀገራችን ከገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተዳምሮ ለአንድ መቶ ሚሊየን ህዝብ ፍጆታ የሚውል መድኃኒት ወደ ሀገር ማስገባት ቀላል አይደለም። የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ የሚከሰቱ መሰናክሎች፣ የሀገራችን የጤና ስርዓት በራሱ ለመድኃኒት አስተዳደር የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት ከብዙ በጥቂቱ ለመድኃኒት አቅርቦት መሳሳትና ለዋጋ ንረቱ ምክንያት ናቸው።» በማለት ጥቅል ሙያዊ አስተያየት በመስጠት በጎንደር ያለውን ሁኔታ ሲያብራሩ

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ጎንደር ቅርንጫፍ የሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት ነፀብራቅ መሆኑን ያነሳሉ። የጥቅል ሀገራዊ እጥረቱን የሚጋራ ቢሆንም ችግሩ በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመፍታት የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል። ‹ቫይታል› የሚባሉ በጣም ወሳኝ መድኃኒቶች አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም ከዋናው መስሪያ ቤትና ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር በመተጋገዝ እየሰሩ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

‹‹የሚፈልጉትን መድኃኒት በሙሉ ማግኘት ባይችሉም በኛ ቅርንጫፍ እየተገለገሉ የሚገኙ ተቋማት በምንችለው አቅም የጠየቁትን መድኃኒት እንዲያገኙ ለማድረግ እየሞከርን እንገኛለን። በዚህ ጥረታችንም በቅርቡ በአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ በተካሄደው ሀገርአቀፍ የመድኃኒት የምክክር መድረክ ላይ ጥሩ አፈፃፀም በማሳየታችን የአንድ ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆነናል።» ብለዋል በመጨረሻም አቶ ሀብታሙ።

የፋርማሲዩቲካል ኢንደስትሪው በርካታ ባለድርሻ አካላት ያሉበት በመሆኑ የሁሉንም የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል። የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማዘመን፣ ለሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ የመድኃኒት አምራች ተቋማትን ሀገር ውስጥ በማስፋፋት ችግሩን ማቃለል ይቻላል። የግል ዘርፉን በመደገፍም ለፋርማሲውቲካል ኢንደስትሪው የራሱን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አስተያየት