እንደጤና ሚንስቴር መረጃ በኢትዮጵያ የኦክስጅን አገልግሎትን ማስፋፋት ከተቻለ በኦክስጅን እጥረት በየዓመቱ በእርግዝና ወቅት የሚሞቱ 11 ሺህ ሴቶችን፣ በተወለዱ የመጀመሪያው ወር ህይወታቸውን የሚያጡ 60ሺህ ጨቅላ ህጻናትንና በሳምባ ምች በሽታ የሚሞቱ 30ሺህ ህጻናትን መታደግ ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ በሠላሳ ሁለት የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ የህክምና ኦክስጅን እና ክሊኒካዊ ልምዱ አቅርቦት ላይ ተመርኩዞ በተካሄደ ጥናት በጥር ወር እ.አ.አ 2021 በታተመው ጥናታቸው ሃብታሙ ስዩም፣ ይገረም አበበ፣ አለበል ያረጋል፣ ድንቅነህ ብቂላ እንደገለፁት ኦክስጅን ብዙ ልጆችን በሃይፖዚሚያ የሚሞቱትን ከሳንባ ምች የሚታደግ ወሳኝ መድሃኒት ነው። ከ95% በላይ የሚሆኑት ሞት በታዳጊ አገሮች ውስጥ ይከሰታል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሳንባ ምች ስርጭት ከፍተኛ ነው።
ጥናቱን ለማካሄድ በየዓመቱ ከ32 የህዝብ ሆስፒታሎች መረጃ ተሰብስቧል፡፡ 15 (46.9%) አጠቃላይ ሆስፒታሎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 10 (31.2%) እና 7 (21.9%) ሪፈራል እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ነበሩ። የጤና እንክብካቤ ሠራተኞችን በቦታ እና ከቦታ ውጭ የአቅም ግንባታ፣ መደበኛ አማካሪ፣ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የመመሪያ/ማኑዋሎች ልማት፣ የኦክስጅን መሣሪያ ግዥ እና ጥገናን የመሳሰሉት ሁለገብ አቀራረቦች ለጤና እንክብካቤ ሠራተኞች እና ለጤና ተቋማት ተሰጥተዋል። ተግባራዊ የኦክስጅን ተደራሽነት በአጠቃላይ እና ሪፈራል ሆስፒታሎች የሕፃናት ውስጥ-የሕመምተኛ ክፍል ውስጥ ከ62% ወደ 100% በስታቲስቲክስ ጉልህ ጭማሪ ዐሳይቷል። ክሊኒካዊ ልምምድን በተመለከተ፣ በምርመራ እና መግቢያ ላይ የ SpO2 ልኬት በቅደም ተከተል ከ10.2% ወደ 75% እና 20.5% ወደ 83% አድጓል ብለዋል፡፡
ባህርዳር ከተማ ሁለተኛ የሆነው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ በቅርቡ ማስመረቁ ተሰምቷል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ በተገኙበት ለአግልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ ፋብሪካው በሰዓት 270 ሚሊ ሜትር ኪዩብ ኦክስጅን የማምረት አቅም እንዳለው እና ከ580 በላይ ለሚሆኑ የህሙማን አልጋዎች ኦክስጅኑ በቀጥታ እንዲደርስ ተደርጎ የማስተላለፊያ መስመሮች የተዘረጉለት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በሀገሪቱ እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ 20 የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት ለመገንባት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ባህርዳር ከተማ የተገነባው 6ኛ ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል መሆኑን ገልጸው ቀሪ 7 ማዕከላትም በመገንባት ላይ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን 20 በመቶ የኦክስጅን አቅርቦት ወደ 60 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው የጠቀሱት ሚኒስትሩ በቀጣይ 5 ዓመታት የኦክስጅን አገልግሎት በሀገሪቱ ሙሉ ለመሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ የተኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አድንቀው የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካው ለክልሉ ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በኦክስጅን እጥረት ለሚቸገሩ የጤና ተቋማት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የተገነባው የመጀመሪያው የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል ከሁለት ዓመታት በፊት በመጋቢት ወር መጨረሻ ተመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካዎች በኦክስጅን እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው በክልሉ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ1190 ሲሊንደር ኦክስጅን እንደሚመረት ተናግረው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያስገነባው ፋብሪካ ክልሉን በከፍተኛ ደረጃ የኦክስጅን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በባህርዳርና በደሴ ከተሞች የተገነቡ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት የክልሉን ነዋሪ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ያገለግላሉ፤ በቀጣይም በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ባህርዳር እና ደሴ ኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት የክልሉ መንግሥት ለሕንጻ ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር ወጭ ያደረገ ሲሆን ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ደግሞ ለማሽነሪ መግዣ 70 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ3 ቢሊየን ብር ወጪ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 411 ሆስፒታሎች ዘመናዊ የኦክስጅን፣ የቫኪዩም እና የሜዲካል ጋዝ ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከላት ለመገንባት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እቅድ ይዞ እንደነበር ከሦስት ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡
በሀገራችን የሚገኙ እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በትምህርቱና በጤናው ዘርፍ እየሰሯቸው ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎች ከክልሉም አልፎ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጣን ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ዶ/ር መልካሙ ጠቅሰው በታላቅ የአመራር ቁርጠኝነት እየሰሩ ያሉ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና ባለሙያዎችን አመስግነዋል፡፡ አክለውም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ የጤናውን ዘርፍ ማዘመን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ሆስፒታሉን በገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽ እያደረገ ያለውን Human Bridge’ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አመስግነው በፌደራል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እና በዩኒቨርሲቲው በጀት የተገነባው የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ የክልሉን የሕክምና ኦክስጅን እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ለመቅረፍ አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት በኦክስጅን እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ታማሚዎችን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
የክልሉን የሕክምና ኦክስጅን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ 500 አልጋዎችን በአንድ ጊዜ ሸፍኖ ከ200-300 ሲሊንደሮችን በ24 ስዓት ዉስጥ የመሙላት አቅም ያለው ነው።
በተመሳሳይም በሀገራችን የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የኦክስጅን ምርት ስራዎች ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ በ23 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ ተቋም በቀን እስከ 350 ስሊንደር ኦክስጅን የማምረት አቅም አለው። ከፌዴራል መንግሥት በተገኘ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግሥት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኦክስጅን ማምራቻ እያቋቋመ ነው፡፡