የካቲት 18 ፣ 2013

የአጼ ፋሲል “ዶሮ ቤት”

City: Gonderታሪክዜናዎች

የአጼ ፋሲል “ዶሮ ቤት” ጉዳይ

Avatar: Tesfa Belayneh
ተስፋ በላይነህ

Tesfa Belayneh is a mobile journalist from the city of Gondar, working at Addis Zeybe

የአጼ ፋሲል “ዶሮ ቤት”

ከጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ በ500 ሜትር ርቀት ላይ በተለምዶ የ'ቀሃ ወንዝ' ድልድይ አጠገብ የሚገኘው የቤተመንግሥት ዶሮ ቤት “Royal Poultry” በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ተዳሳሽ ቅርሶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የቅርሱ ስያሜ ሕንጻው በታሪክ ውስጥ የነበረውን ትክክለኛ ግብር በግልጽ የሚያስቀምጥ ባለመሆኑ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የዶሮ ቤት የሚለውን አሻሚ ስያሜ ይዞ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ ለመሆኑ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ፋሲል ዘመነ መንግሥት የተገነባው፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የቤተመንግሥት ዶሮ ቤት ሥራው ምን ነበር? ዶሮ ማርቢያ ወይስ ከዶሮ የሚሰራ ምግብ ማዘጋጃ?

የጎንደር ከተማን የቅርስ መዳረሻዎች፣ ጥንታዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች በማጥናት ጊዜውን ያሳለፈው አቶ ኃይለኢሱስ ኤፍሬም ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ያቀረብንለትን ጥያቄ ሲመልስ ‹‹ቦታው እንደ ሌሎች የጎንደር ከተማ ቅርሶች በሐገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጎብኝዎች ትኩረት አልተሰጠውም›› ይላል፡፡ በነዋሪዎች እና ጎብኝዎች ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ታሪክ በሚዘክሩ መዛግብት ላይም መረጃዎች ሊገኙለት እንዳልቻሉና ‹‹ሕንጻው ምን ሲደረግበት ነበር?›› የሚለውን ጥያቄ አስመልክቶ የሚነሳው ውዝግብ ተጨባጭ ማስረጃ ካለመገኘቱ እንደሚመነጭ አብራርቷል፡፡ አቶ ኃይለኢየሱስ ማብራሪያውን ሲቀጥል ‹‹የሕንጻውን ቁመና እና የውስጥ አሰራር ስንመለከት ዶሮ ማርቢያ ነበር ለማለት የሚያስችል አይደለም፡፡ በይዘትም በቅርጽም የዶሮ እርባታ ይከናወንበት እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለውም፡፡ “ዶሮ ቤት” ከሚል ስያሜው ውጭ የዶሮ ማርቢያ ስፍራ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ በእንግሊዘኛው “ፖልትሪ” (የዶሮ ማርቢያ) የሚል ስያሜ ያገኘበት ምክንያት ለእኔ ግልጽ አይደለም››

የጎንደር ከተማ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ዐይቼው አዲሱ በበኩላቸው ቦታው የዶሮ ማርቢያ እንዳልነበረ አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አይቼው አክለውም
‹‹ከ1624 ዓ.ም. ጀምሮ የነገሡት አጼ ፋሲል በቤተመንግሥታቸው ውስጥ “ወሸባ” (ስቲም እና ሳውና) አገልግሎት መስጫ ቤት ነበራቸው፡፡ ይህንን ሕንጻ ያስገነቡት ከቤተመንግሥት ውጭ ያለው ማኅበረሰብ (ሕዝቡ) እንዲጠቀምበት ነው፡፡ በሕንጻው የላይኛው ክፍል የጭስ እና እንፋሎት መውጫዎቸ አሉ፡፡ ይህም የሕንጻውን ተግባር ያሳያል›› ብለዋል፡፡

የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ሕንጻው የ“ወሸባ” ቤት ሆኖ ሳለ ለምን “ዶሮ ቤት” ተባለ በሚል ያነሳውን ጥያቄ አቶ ዐይቼው ሲመልሱ ‹‹አንድ ሰው ወሸባ ሲገባ በእንፋሎት እና በፈላ ውሃ ይታጠባል፡፡ ልክ ለመብል የምትዘጋጅ ዶሮ በፈላ ውሃ እንደምትታጠበው ይሆናል፡፡ ዶሮ ቤት የሚለው ስያሜ ያንን ስሜት ለመግለጽ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕንጻው የቤተመንግሥት ዶሮ ቤት (ፖልትሪ) የሚለውን ስያሜ ያገኘው በ1928 በጣልያኖች እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአሁን ሰዓት የክልሉ ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ወጣቶችን አደራጅቶ ሕንጻውን የውበት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ከቡድን መሪው ሰምተናል፡፡

አስተያየት