ዓላማዬ ዕድለኞችን መሸለም ነው የሚለው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከሰሞኑ ባስነገረው ማስታወቂያ የእንቁጣጣሽ ሎተሪ 1ኛ ዕጣ ዕድለኛ እስካሁን ወደ አስተዳደሩ እንዳልቀረበ/ች አስታውቆ የዚህ ዕጣ ቁጥር ስርጭት ደቡብ ማስተባበሪያ እንደነበር ማስታወቁ አይዘነጋም።
20 ሚሊዮን ብር የሚያስገኘው የዚህ ዕጣ አሸናፊ ወደ አስተዳደሩ መጥቶ/ታ ገንዘቡን የማይረከብ/የማትረከብ ከሆነ የገንዘቡ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ስንል ወደ አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ስልክ ደውለናል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ አሸናፊው/ዋ ካልቀረበ/ች የ20 ሚሊዮን ብሩ የመጨረሻ ማረፊያ የት ሊሆን እንደሚችል ሲናገሩ “የዕጣው አሸናፊ ወደ አስተዳደሩ መጥቶ/ታ ገንዘቡን የማይረከብ/የማትረከብ ከሆነ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ገንዘቡን ለራሱ ገቢ ያደርገዋል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የዕጣ አሸናፊ ሳይቀርብበት ወደ አስተዳደሩ ገቢ የተደረገ የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የጠየቅናቸው ዳይሬክተሩ ይህንን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ጠቅሰው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ብሔራዊ ሎተሪ አቅርቧቸው ከነበሩት ሽልማቶች መካከል የሚገኙት የፀሐይ እና የዘነበ ፍሬው ሪል እስቴት ቤቶች የዕጣ አሸናፊዎች ሳይመጡ በመቅረታቸው ምክንያት ሽልማቱ ሳይበረከት እንደቀረ ነግረውናል።
ይህ ዘገባ ከተጠናከረበት ግዜ ጀምሮ የዕጣው ማብቂያ ቀን ሊጠናቀቅ 14 ቀን የቀረው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ 1ኛ ዕጣ አሸናፊ ቁጥር 0216884 ሲሆን አስተዳደሩ ዕድለኛው/ይቷን እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ እጠብቃለሁ ብሏል።
በተያያዘም አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 42 የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ባለፉት 7 ወራት 50 ሚሊዮን ብር እንዳገኘ ገልጿል።