የካቲት 16 ፣ 2013

"የሞተር አደጋ የደረሰበት አይነት አውሮፕላን የለኝም” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ዜናዎች

አሜሪካ ውስጥ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ሆኖሉሉ በረራ ላይ የነበረው ቦይንግ 777 አውሮፕላን በቀኝ ክንፉ በሚገኘው ሞተሩ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ተከትሎ ሊደርስበት ከሚችለው አደጋ ማምለጡ የሚታወስ ነው።

"የሞተር አደጋ የደረሰበት አይነት አውሮፕላን የለኝም” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

አሜሪካ ውስጥ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ሆኖሉሉ በረራ ላይ የነበረው ቦይንግ 777 አውሮፕላን በቀኝ ክንፉ በሚገኘው ሞተሩ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ተከትሎ ሊደርስበት ከሚችለው አደጋ ማምለጡ የሚታወስ ነው።


በበረራ ቁጥር 328 የተመዘገበውና ንብረትነቱ የዩናይትድ ኤርላየንስ የሆነው ይህ አውሮፕላን 231 ተሳፋሪዎችን ከ10 የበረራ ሰራተኞች ጋር አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ ሲሆን ያጋጠመውን የሞተር ብልሽት ተከትሎ ዴንቨር አየርማረፊያ እንዲያርፍ ተደርጓል።


በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰውን የሞተር ብልሽት አደጋ ተከትሎ የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ ኩባንያ በደረሰው አደጋ ዙሪያ ምርመራ ተደርጎ አንዳች ግኝት ላይ እስኪደረስ ድረስ በአለም ላይ የሚገኙ 128 “ፕራት እና ዊትኒ 4000” የተሰኘ ሞተር የተገጠመላቸው  አውሮፕላኖች ከበረራ መውረድ እንዳለባቸው ገልጿል።


ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሰል አውሮፕላን ይኖረው እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ለአየር መንገዱ ጥያቄ አቅርቧል።


የኢትዮጵያ አየርመንገድ በምላሹ “ፕራት እና ዊትኒ የተሰኘ የሞተር አይነት የተገጠመለት ቦይንግ 777 አውሮፕላን እንደሌለው” ነግሮናል።


ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲጠቀምበት የነበረው ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን 737 ማክስ 8 ተከስክሶ ለ157 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።


“ከጥልቅ ትንተና በኋላ” ይህንን አውሮፕላን በድጋሚ ሥራ ላይ ለማዋል ከውሳኔ ላይ መደረሱን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የተናገሩ ሲሆን አገልግሎቱ በሐምሌ ወር ውስጥ ሊጀመር እንደሚችል መጠቆማቸው የሚታወስ ነው።


አውሮፕላኑ የተደረገለትን ማሻሻያ ተከትሎ አገልግሎት ለመስጠት አስተማማኝ ሆኗል ያሉት ሥራ ዋና አስፈፃሚው ነገር ግን ሠራተኞቻችንና ተሳፋሪዎቻችን በዚህ አውሮፕላን እንዲጠቀሙ ለማድረግና ዕምነት ለመፍጠር ግዜ መውሰዱ አይቀርም ብለዋል።


ከዚህ ቀደም የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከአገልግሎት ውጪ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በያዝነው የካቲት ወር ከቦይንግ ጋር የካሳ ስምምነቱን እንደሚያጠናቅ ይጠበቃል ሲሉ አቶ ተወልደ መናገራቸው ተዘግቧል።


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

አስተያየት