የካቲት 18 ፣ 2013

ሥልጣን እስከመቼ? የስልጣን ጊዜ ገደብ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ሕግወቅታዊ ጉዳዮች

የስልጣን ጊዜ ገደብ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

Avatar: Endale Mekonnen
እንዳለ መኮንን

በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር

ሥልጣን እስከመቼ? የስልጣን ጊዜ ገደብ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

በአንድ ወቅት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ሁሴን ኦባማ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔን አዲስ አበባ በሚገኘው የሕብረቱ ጽ/ቤት በታደሙበት ወቅት የአህጉሪቱን መሪዎች ሸንቆጥ ያደረገ ንግግር አሰምተው ነበር። የቀድሞው ፕሬዝደንት “እናተ የአፍሪካ መሪዎች ስለምን ስልጣን ላይ ሙጭጭ ትላላችሁ?” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ተከታዩን ንግግር አደረጉ። “ስራዬን በጣም እወደዋለሁ፤ ፕሬዝደንት በመሆኔም ትልቅ ክብር ይሰማኛል። ለሶስተኛ ግዜ ለፕሬዝደንትነት ብወዳደር ላሸንፍ እንደምችልም እገምታለሁ፤ ግን በአገሬ ሕገ-መንግስት ላይ ከሁለት ግዜ በላይ መወዳደር እንደማልችል ተደንግጓል። ሕግ ደግሞ ሕግ ነው። ማንም ሰው ከሕግ በታች ነው፤ ፕሬዝደንቱን ጨምሮ።” እኔን የማይገባኝ አሉ ፕሬዝደንቱ “በተለይ ብዙ ገንዘብ እያላቸው ስልጣን ላይ ለረጅም ግዜ የሚቆዩት ለምንድን ነው?” በማለት ከጠየቁ በኋላ “ማንም ሰው የሕይወት ዘመን መሪ ሊሆን አይገባውም” ሲሉ ንግግራቸውን ቋጩት።

የሥልጣን ጊዜ ገደብን በሕገ-መንግስቷ ያልደነገገችው ኢትዮጵያ አንድ መሪ ሕዝብ ከመረጠኝ እስካሻኝ ግዜ ድረስ በሥልጣን ላይ ብቆይ ምን ሃጥያት አለበት ለሚሉ መሪዎች የተራዘመ የሥልጣን ጊዜ የተመቸች እንደሆነች የሚናገሩ ብዙ የፖለቲከኞች አሉ። በ1987 ዓ.ም “በህዝብ ይሁንታ” እንደወጣ የሚነገርለት የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 70 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ “የፕሬዝደንቱ የሥልጣን ጊዜ 6 ዓመት ይሆናል፤ አንድ ሰዉ ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዝደንትነት መመረጥ አይችልም” ሲል ይደነግጋል። ነገር ግን ከአንቀፅ 72-77 ድረስ የስራ አስፈፃሚዉን የስልጣን አካል የሚዘረዝር ሲሆን በተለይም ደግሞ አንቀጽ 72 የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ጊዜ ሳይገድብ ወይም ሳያነሳ ያልፋል።

በሌላ በኩል እንደ አንዳንድ በፖለቲካ ውስጥ እንዳሉ ሰዎች አገላለፅ “በሕዝብ ተመርጠው ሥልጣን ላይ ከሚቀመጡ መሪዎች ባሻገር የተወሰኑ በፖለቲካ ሜዳ ውስጥ የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ቢሆኑ በፓርቲ መሪነት ለረጅም ግዜ የቆዩ ከመሆናቸው በላይ ከመሪነታቸው ከወረዱ ሌላ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው መሪ የሚሆኑ ናቸው” ይላሉ።

ከላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች መሰረት አድርገን ኢትዮጵያ እና የሥልጣን ጊዜ ገደብ እስካሁን ለምን አልተገናኙም ስንል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አነጋግረናል፡፡

የባልደረስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ ጫኔ (ዶ/ር) “ሥልጣን ገደብ ከሌለው እና በጊዜ ካልተወሰነ ለሙስና በር የሚከፍት ብሎም መሪዎች በስልጣን እንዲባልጉ የሚያደርግ ትልቅ ክፍተት ነው” ይላሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ ይህንን ችግር ለመፍታት “የስልጣን ገደብ ወሳኝ እና መሰረታዊ ነዉ።” ከዚህም በላይ ይላሉ በቃሉ ጫኔ (ዶ/ር) “ሁሉም ሰዉ የየራሱ ብቃትና ችሎታ ያለዉ በመሆኑ የግለሰቦቹ በሥልጣን ላይ መቆየት ሌሎች በችሎታቸው አስተዋዕፆ እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆናል።” እንደ እርሳቸው ሃሳብ “በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ግን ትግል ስለሆነ የጊዜ ገደብ አያስፈልገዉም” የሚል ዕይታ እንዳላቸው ገልፀውልናል።

የኦፌኮ እና የመድረክ ሊቀ-መንበር የሆኑት መራራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ግን የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ቢሆኑ በፓርቲያቸው ውስጥ የሥልጣን ገደብ ሊያበጁ ይገባል ከሚሉት ጎራ ናቸው፤ “ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የመሪያቸዉን የሥልጣን ጊዜ መገደብ አለባቸዉ። ምክንያቱም የፓርቲ መሪዎች ፓርቲዉን እንደ ግል ንብረት የመያዝ አዝማሚያ ስላለ ለነሱም ቢሆን አስፈላጊ ነዉ” ይላሉ። “ኦፌኮ እንደ አቋም እስከ አሁን የሥልጣን ገደብ አላስቀመጠም” የሚሉት መራራ “አገራችን የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ተከታይ ብትሆንም የመሪዉ የስልጣን ጊዜ ተገድቦ ነገር ግን ፓርቲው እስከተመረጠ ድረስ ቢቀጥል ይህም አንዴ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ መሪዎች አላግባብ ብዙ ነገር ስለሚያደርጉ ይህንን ለመገደብ ወሳኝ ነዉ” የሚል አቋም አራምደዋል።

“የስልጣን ገደብ በሕገ-መንግስት ሊካተት ይገባል” የሚሉት ሌላኛው ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ዋና ፀሃፊ አቶ አለሙ ኩ’ራይ “እንደ ኢሶዴፓ የስልጣን ጊዜ ለሁለት የምርጫ ወቅት ቢወስንም ነገር ግን ያሉን ትልልቅ ሰዎች ተሰሚነታቸዉ እና ተዓማኒነታቸዉ ትልቅ ስለሆነ ለፓርቲዉ ድጋፍ ሲባል በጠቅላላ ጉባዔ እንዲቀጥሉ ይደረጋል” ሲሉ ነግረውናል።

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ከተለያዩ የማህበረሰብ አባላት ጋር ሲወያዩ “የጡረታ ጊዜያቸዉ አልፎ ከወንበራቸዉ መነቃነቅ የማይፈልጉ በጣም በርካቶች በእኛ ዉስጥ አሉ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አገራችን እያደገች በመሆኑ ጥቂት ሰዎችን ለረጅም ጊዜ በወንበር ላይ ማቆየት አግባብ አይደለም። ይህንንም የስልጣን ላይ የቆይታ ጊዜ መገደብ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር፣ ሙስናን ለማጥፋት እና ለመቀነስ እንደሚያስችል፤ ለዚህም የሥልጣን ላይ ቆይታ ጊዜ ከሁለት የምርጫ ዘመን እንዳይበልጥ የሚገድብ ሕግ በህገ-መንግስቱ ይደነገጋል” ማለታቸዉ አይዘነጋም። ይህ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቋም ከ3 ዓመት ገደማ በኋላ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አስተያየት