የግብርና ሚኒስቴር ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ እየተከተሰ ያለውን አንበጣ አስመልክቶ ሲናገር “ከኬንያ በየቀኑ በአማካኝ ሁለት መንጋ አንበጣ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ነው” ማለቱ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ያስቸገረው የአንበጣ መንጋ ኬንያ ውስጥ ለእንስሳት ምግብ ከመሆኑ ባሻገር አንበጣውን ሰብስበው ለሚሸጡ ግለሰቦች የገቢ ምንጭ እንደሆነ ተሰምቷል።
በቀን አንበጦቹን ለመያዝ አዳጋች ስለሚሆን በምሽት እንደሚዘምቱባቸው የሚናገሩት አልበርት ሊማሱላኒ የአንበጣው መንጋ በምሽት እንቅስቃሴ ስለማያደርግ ያኔ ለመያዝ ቀላል ነው ይላሉ።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን አንበጣዎቹን ለመያዝ ከልጅ እስከ አዋቂ ለመሰብስቢያ የሚሆን ከረጢት ይዘው ይወጣሉ።
የአንበጣው መንጋ አገር አማን ብሎ በተቀመጠበት የሚካሄደው ይህ የመሰብሰብ ዘመቻ በእጅ በመልቀም ወይም ያረፈበትን ተክል በመነቅነቅና ወደ መሬት እንዲወድቅ በማድረግ ይካሄዳል።
የተሰበሰበውን አንበጣ የሚረከበው አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ለ1 ኪሎ አንበጣ 50 የኬንያ ሽልንግ ይከፍላል። የተሰበሰቡት አንበጦች በከረጢት ውስጥ እንዳሉ በመዳመጫ ተዳምጠው እንዲሞቱ ከተደረገ በኋላ በፀሀይ ብርሃን እንዲደርቁ ይደረጋል።
በፀሀይ ብርሃን እንዲደርቁ የተደረጉት አንበጦች ለአሳ፣ ላም፣ አሳማ እና ለአዳንድ የወፍ ዝርያዎች ለምግብነት ይውላል።
አንበጣ በውስጡ 70 በመቶ ፕሮቲን ስለያዘ የእንስሳት የፕሮቲን ምግብ እጥረት እንደሚቀርፍም ተነግሯል። ይህ ዘዴ የመንጋውን ጥቃት መሉ በሙሉ መቅረፍ ባይችልም እንኳ በአንድ ድንጋይ 2 ወፍ እንዲሉ የሚበላውን እንዲበላ በማድረግ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ ጉጂና በቦረና ዞን፤ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ እንዲሁም በደቡብ ሶማሌ ክልል እንደተከሰተ ያስታወቀው የግብርና ሚኒስቴር መንጋውን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተደረገ እንደሆነና በመንጋው ምክንያት በአገሪቷ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንን ተናግሮ በጥናቱ ውጤት መሰረት ጉዳት ለደሰረባቸው አካባቢዎች ድጋፍ እንደሚደረግ ማስታወቁ አይዘነጋም።
በምስራቅ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ2020 የታየው የአንበጣ መንጋ በ70 አመት ውስጥ ከታየው የከፋ እንደሆነ ይነገራል።