የካቲት 11 ፣ 2013

የጌዴኦ የምስጋና ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

City: Hawassaታሪክ

የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሣውን ጨምሮ የክልል አመራሮችና ጥሪ የተረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የጌዴኦ የምስጋና ቀን “ደራሮ” በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

የጌዴኦ የምስጋና ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሣውን ጨምሮ የክልል አመራሮችና ጥሪ የተረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የጌዴኦ የምስጋና ቀን “ደራሮ” በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በየ8 ዓመቱ በሚመረጥ ባህላዊ አስተዳዳሪ የሚመራው የጌዴኦ ብሔረሰብ በአደባባይ ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ “ደራሮ” ነው።
“አምናን አልፈን፣ ዘንድሮ ላይ ደርሰን የዘራነው አፍርቶ፣ የተከልነው ለምልሞ፣ ለመብላት ላበቃን አምላክ ምስጋና ለማድረስ እዚህ ተሰባሰብን” በማለት የሶንጐው አባት ምስጋና አቅርበው የገብስ ቆሎ ከተቆላ ቡና ጋር በማር ወይም በቅቤ ተለውሶ ለአባ ገዳው የሚቀርብበት የምስጋና በዓል ነው። ከጥር 18/2013 ዓ.ም. በታላቁ ‘ሶንጎ አጋምሳ ኦዳ ያአ’ የተጀመረው በዓል በ‹‹ፋጎ›› ባህላዊ ዝማሬ በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከስፍራው እንደዘገበው “ደራሮ” አባ ገዳው በባህላዊው ሥርዓት ፀሎት አድርጎ፣ እግዚአብሔርን አመስግኖ፣… ሕዝቡን የሚመግብበትና የህዝቡን ቅሬታና ችግሮች ከተከታዮቹ ጋር አድምጦ መፍትሔ የሚሠጥበት ነው። ጠለፋ፣ ጥንቆላ፣ መተት፣ አስገድዶ መድፈርንና የሴት ልጅ ግርዛት በአጠቃላይ በኀብረተሰቡ ዘንድ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳይስፋፉ የሚያወግዝበትና ምክርና ተግሳፅ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ አዋጆችን /ላላባ/ በማውጣት ሕዝቡ ለሰላም፣ ለስራ እንዲተጋ ጥብቅ መመሪያ የሚተላለፍበት የጌዴኦዎችና በውስጡ ለሚኖሩ ሕዝቦች ሠፊ ባህላዊ አውድ መሆኑን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።
በዛሬው ዕለት በዲላ ሁለገብ ስታዲየም የተከበረው የ“ደራሮ” በዓል የብሄሩን አጠቃላይ ገፅታ የሚያንፀባርቅ ባህል ሆኖ ለዘመናት ወዙን፣ ታሪኩንና ባህላዊ ገፅታውን ሸክፎ በደመቀ ሁኔታ ለዘመናት እየተከበረ የመጣ፤ ሲሆን በዲላ ከተማ መከበር የጀመረው ከኢትዮጵያ ሚሊንየም ወዲህ መሆኑ ታውቋል።

አስተያየት