የካቲት 11 ፣ 2013

ለሌሎች አገራት ገበሬዎች የእንጀራ ገመድ የቀጠለው ፊቤላ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ስማቸው ተደጋግሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ይጠራል። በአንደኛው የሕይወታቸው ገፅ ወታደር ነበሩ በሌላኛው ደግሞ የቀን ሰራተኛ። እነሆ አሁን ደግሞ “ቢጠሯቸው የማይሰሙ” ባለፀጋ ሆነዋል

Avatar: Endale Mekonnen
እንዳለ መኮንን

በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር

ለሌሎች አገራት ገበሬዎች የእንጀራ ገመድ የቀጠለው ፊቤላ

ስማቸው ተደጋግሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ይጠራል። በአንደኛው የሕይወታቸው ገፅ ወታደር ነበሩ በሌላኛው ደግሞ የቀን ሰራተኛ። እነሆ አሁን ደግሞ “ቢጠሯቸው የማይሰሙ” ባለፀጋ ሆነዋል፤ አቶ በላይነህ ክንዴ።
በቀን አራት ብር እየተከፈለኝ የቀን ስራ ሰርቼ አውቃለሁ የሚሉት አቶ በላይነህ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን ሲቆናጠጥ እርሳቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር አባል ነበሩ፡፡ ያ ጦር “የደርግ ጦር” ተብሎ እንዲበተን ሲደረግ እርሳቸውም የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል።


በውጣ ውረድ እዚህ እንደደረሱ የሚነገርላቸው አቶ በላይነህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሳይቀሩ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኖበታል የተባለውንና የእርሳቸው ንብረት የሆነው ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በተመረቀበት ወቅት “እርስዎ ባለሃብት ሳይሆኑ ባለፀጋ ነዎት፤ በባለሃብትና ባለፀጋ መካከል ልዩነት አለ” ሲሉ ሙገሳ እንደቸሯቸው ይታወሳል።


ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋሙ ፋብሪካዎች ለምርት ግብዓት የሚሆናቸውን ጥሬ ዕቃ በአብዛኛው ከተለያዩ የውጪ አገራት በሚያስገቡባትና የውጪ ምንዛሪ እጥረቱ አላላውስ ባለበት አገር አማራ ክልል ቡሬ ከተማ የተቋቋመውና በቀን 1500 ቶን የምግብ ዘይት እንደሚያመርት የተነገረለት ፊቤላ ይህንን ከመሰለ ችግር ምን ያህል የራቀ ነው የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የፋብሪካውን ኃላፊ አዲስ ዘይቤ አነጋግራለች።


“አሁን ላይ ከኢትዮጵያ የምንጠቀመዉ ምንም ምርት የለም፤ ድፍድፉን ነዉ እያስመጣን የማጣራት ስራ የምንሰራዉ” ያሉን የፊቤላ ዘይት ፋብሪካ ኃላፊ አቶ እንየዉ ዋሴ ለግብዓት የሚያገለግለው ድፍድፍ ዘይት የሚመጣው ከኢንዶኔዢያ እና ከሌሎች የእስያ አገራት እነደሆነ ይናገራሉ። ይህ ማለት አማራ ክልል የተቋቋመ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ኢንዶኔዢያ እና ሌሎች የእስያ አገራት ውስጥ ለሚገኙ ገበሬዎች የእንጀራ ገመድ መቀጠሉን ያሳያል።


አማራ ክልል ውስጥ የተቋቋመ ፋብሪካ ስለምን በኢንዶኔዢያ እና ሌሎች የእስያ አገራት ገበሬዎች ምርት ላይ ይመሰረታል፤ ለግብዓት የምትጠቀሙበትን ምርት ለምን ከአገር ውስጥ አትገዙም የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኃላፊው “ምርቱ ኖሮ ብንገዛ በምን እድላችን ግን ለኛ ፋብሪካ ምርት የሚሆን ብዛት ያለው ግብዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት አልሆንላችሁ ስላለን ነው ወደ ውጪ ያማተርነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

  
ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገበሬ ነው እየተባለ በሚነገርበት አገር ውስጥ የሚገኝን አንድ የምግብ ዘይት ፋብሪካ የግብዓት ፍላጎት ማሟላት ያልቻልንበት ምክንያት ምን እንደሆነ የሚጠይቅ ዜጋ ለጥያቄው ምላሽ የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶችን ሊያገኝ ይችላል።


እስካሁን በበሬ በተበጣጠሰ መሬት በሚታረስበት አገር አሁንም ድረስ ለዳቦ የሚሆን ስንዴ በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ እያደረገች ለምትገዛው ኢትዮጵያ ለአንድ ፋብሪካ የምግብ ዘይት ምርት የሚሆን ግብዓት ለማምረት ወገቤን ማለቷ ብዙም ላይገርም ይችል ይሆናል። በራስ አቅም ያመረቱትን በግብዓትነት ተጠቅሞ የተጠናቀቀ ምርት ማምረት አለመቻል ግን ብዙ ጣጣዎች እንደሚኖሩት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።


የተለያዩ የተጠናቀቁ ምርቶችን በብዛት ወደ ዓለም አገራት መላክ ያልቻለና መላክ ባይችል እንኳን በአገር ውስጥ ምርት አብዛኛውን የአገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ያልቻለ አገር በንፅፅር ሉዓላዊ ነፃነቱን አስከብሮ ለመኖር እንደሚያዳግተው ብዙ ምሳሌዎች አሉ።


በአመት 20 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል እንደሚያስፈልገው የተነገረለት ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ፍላጎቱን ለማሟላትና ምርቱን በአገር ውስጥ ግብዓት ለመሸፈን አስር ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ ለማልማት በምንጣሮ ላይ እንደሆነና ይህም ከሁለት አመት በኋላ ሊሳካ እንደሚችል የፋብሪካው ኃላፊ ነግረውናል።


ይህ ዕቅድ እስኪሳካ ድረስ ግን በፋብሪካው ውስጥ የስራ ዕድል ካገኙት ኢትዮጵያውያን ውጪ ግብዓቱን ለሚገኝባቸው አገራት ገበሬዎች የስራ እና ገቢ ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው።


በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና በ2006 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ 2013 ዓ.ም ላይ የተገባደደው ይህ ፋብሪካ የኢትዮጵያን የምግብ ዘይት ፍላጎት 60 በመቶ እንደሚሸፍን መነገሩ የሚታወስ ነው። እንደተባለው አሁን ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር ይፈታል ወይስ ችግሩ ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ ግን በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።

አስተያየት