በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በተፈጠረው የቤንዚን እጥረት መቸገራቸውን ሾፌሮች ተናግረዋል። አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደሩ ሾፌሮች እንዳሉት ከሰኞ የካቲት8፣ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ የተፈጠረው የቤንዚን እጥረት ለእንግልት ዳርጓቸዋል። በከተማዋ ከሚገኙ 11 ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው አንዱ ብቻ ነው።
የባጃጅ አሽርካሪ የሆነው አቶ አብዱላሂ አብዲ ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ እንደተናገረው ‹‹ጎመጆ ቶታል በመባል ከሚታወቀው ማደያ በስተቀር የትኛውም ነዳጅ ማደያ ነዳጅ የለም። የተቀሩት ማደያዎች ነዳጅ እየሸጡ አይደለም። ለተጠቃሚው ሳይሆን አትርፈው ለሚሸጡ ቸርቻሪዎች በትርፍ እየሸጡ ነው። በማደያ በሊትር 21 ብር የሚሸጠውን ሕገ-ወጥ ቸርቻሪዎች 28 ብር ይሸጣሉ። ዋጋው በበርሜል ሲሆን ይጨምራል።››
አቶ አብዱላሂ ነዳጅ ለመቅዳት ብቻ ከሁለት ሰዓታት በላይ እንደሚሰለፍ ገልጾ አልፎ አልፎ ሰዓቱን ላለማባከን ከቸርቻሪዎች በሊትር እስከ 40 ብር ቀድቶ እንደሚሰራ ነግሮናል። በጅግጅጋ ከተማ የነዳጅ እጥረት አለ በሚል እጥረቱ እንዲፈጠር የሚሰሩ ማደያዎች አሉ። ከቸርቻሪዎች ጋር ተሻርከው በውድ ዋጋ ይሸጡታል። የከተማው የንግድ ቢሮም ይህንን ለመሰለው ድርጊት እርምጃ ሲወስድ ዐይታይም የሚለው አስተያየት ሰጪአችን ባለትዳርና እኔም የ6 ልጆች አባት ነው።
በአሁን ሰዓት በከተማው በብቸኝነት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ጎመጆ ነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ንጉሤ ክስተቱን አስመልክቶ ለአዲስ ዘይቤ በሰጡት ምላሽ
“ሁለት የነዳጅ ቦቴ ከጅቡቲ ተነስቶ አዳይቱ የሚባል ቦታ ስለተበላሸብን ተጠግኖ ጅግጅጋ ለመድረስ 10 ቀን ወስዶበታል። ነዳጁ ከደረሰ በኋላ ከሌሊቱ 12 ሰዓት ጀምረን አገልግሎት እይሰጠን እንገኛለን። በከተማው ያሉት አብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎች አንዳንዴ ነዳጅ እያላቸውም ለመሸጥ ፍቃደኛ አይሆኑም። ምክንያቱም ለቸርቻሪዎቹ እትርፎ መሸጥ ስለሚያዋጣቸው ብዙን ግዜ እጥረት ሳይኖር የለም ይላሉ። ለማሳያነት አሁን ተከሰተ የሚባለውን የቤንዚን እጥረት እንኳን ብንወስድ ከጀቡቲ ምንም አይነት እጥረት በሌለበት ሁኔታ ነው።” ብለዋል።
በጅግጅጋ ከተማ ንግድ ቢሮ መርማሪና ተቆጣጣሪ የሆኑት አቶ ዩሱፍ መሃመድ በበኩላቸው “የቤንዚን እጥረቱ የተፈጠረው በጅግጅጋ ከተማ ብቻ ሳይሆን በጅግጅጋ ዙሪያ ባሉ 12 ወረዳዎችም ጭምር ነው። የእጥረቱ ምክንያት ደግሞ በጅቡቲ ካለው የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ ነው። ችግሩ ከተከሰተ ግዜ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በመደወል ነዳጅ ማደያዎቹ በቶሎ ቤንዚን እንዲያስገቡ እያደረገን ነው። በከተማው ያሉ የነዳጅ ማደያዎች በሕገ-ወጥ መንግድ እንዳይሰማሩ ከፖሊስ ጋር ሆነን ቁጥጥር እያደረገን እንገኛልን።›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ችግሩ በነገው ዕለት ይፈታል።