አውሮፓውያን አፍሪካን ተቀራምተው እንደልባቸው ያሻቸውን በሚያደርጉበት ዘመን ጣሊያንም የልብ መሻቷን ለመፈፀም ኢትዮጵያ ላይ ጦር አዘመተች።
የዘመተው ጦር አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ የሃፍረት ሸማን ከተከናነበ 40 ዓመታት በኋላ የአድዋን ድል ለመበቀል በድጋሚ በኢትዮጵያን ላይ ወረራ ተፈፀመ።
የፋሺሽቱ ጦር ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ በድጋሚ በፈፀመው ወረራ ለአምስት ዓመት ያህክል ኢትዮጵያ ውስጥ ቢቆይም በቆይታው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና አርበኛውን አንገት አስደፍቶ በሰላም ሊገዛ አልቻለም። ለዚህ አባባል ተምሳሌት የሚሆነው በሁለት የኢትዮጵያ ልጆች የተፈፀመው የጀግንነት ተግባር አንዱ ነው፡፡
ኤርትራ ውስጥ የተወለዱት አብራሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ የኔፕልስ ልዑል ልጅ የልደት በዓል ለማክበርና በዕለቱም ቸርነቱን ለማሳየት በአዲስ አበባ ለሚገኙ ደሃዎችንና አካል ጉዳተኞች ምጽዋት ለመስጠት በተዘጋጀበት ሰዓት አርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ የእጅ ቦምባቸውን ወረወሩበት።
በዚህም ሮዶልፍ ግራዚያኒ ከ250 ያላነሱ ቁርጥራጭ ብረቶች በሰዉነቶ ቢገቡም ሆሰፒታል ገብቶ ህይወቱ የተረፈ ሲሆን ጀነራል ሊኦታ የተባለዉ ደግሞ እግሩን አጥቶ እርሱም በሕይወት ተርፏል።
ጣሊያን ወትሮም ፋሺስት ወራሪ ሃይል ነው እና የቦምብ አደጋውን ለመበቀል የተሰማሩ የፋሺስት ወታደሮች በዕለቱ በእንግድነት የተሰበሰቡት ኢትዮጵያዊያንን፣ ደሃዎችንና አካል ጉዳኞችን ጨምሮ የአዲስ አበባን ህዝብ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ጨፍጭፈዋል።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት በዚህ ጭፍጨፋ ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ተገድለዋል። የፋሺሽት ወታደሮች የኢትዮጵያዊያንን ጎጆዎች በማቃጠል ከእሳት ለማምለጥ የሚሞክሩትን እንደ አዳኝ ግዳይ ጥለዋል።
በየዓመቱ የካቲት 12 ቀን የሚከበረው ይህ የመታሰቢያ በዓል ዘንድሮም ለ84ኛ ግዜ 6 ኪሎ በሚገኘው የካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልት ተከብሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ቀኑን አስመልክተው ከስፍራው ባስተላለፉት መልዕክት ደማቸውን ለሃገር ክብር ላፈሰሱ፣ አጥንታቸውንም ለህዝብ ነጻነት ለከሰከሱት ጀግና ሰማዕታት ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።