ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቁ በሚባልበት አገር ውስጥ ወደ ፖለቲካ ከገቡ ሶስት አስርት አመታትን ሊደፍኑ ጥቂት ቀርቷቸዋል፤ አቶ ልደቱ አያሌው። በቅርቡ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ አድርገውት በነበረው አንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ከአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ “አሁን እኮ እኔ የከሰርኩ ፖለቲከኛ ነኝ” ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ልደቱን በበጎ የሚመለከቷቸው የመኖራቸውን ያህል ምርጫ 97ን ተከትሎ የመንግስት ተለጣፊ ናቸው በሚል ጥርስ የነከሱባቸው አሉ።
ሰውየው ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተፈጠረውን ሁከት በማነሳሳት፣ በመምራትና በገንዘብ በመደገፍ እንዲሁም ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ተጠርጥረው እስር ቤት ከርመዋል።ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ በሚል የተከሰሱበት ወንጀል ውድቅ ሆኖ በሌላኛው ክስ በዋስትና እንዲወጡ የተደረጉት አቶ ልደቱ ፍርድ ቤት የተጠየቀባቸውን ዋስትና አሲዘው ይለቀቁ የሚል ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ፓሊስ አሻፈረኝ ሲል ከርሞ ነው በመጨረሻ የተፈቱት።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ “ለህክምና” በሚል ወደ አሜሪካን አገር ለመጓዝ ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም “ከበላይ አካል” የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል ምክንያት የአውሮፕላን ጣቢያውን የመውጫ በር ሳያልፉ ቀርተዋል።ይህ ፅሁፍ የአቶ ልደቱ አያሌውን የጉዞ ክልከላ እና የፍርድ ቤትን ውሳኔ ያለመፈፀምን ጉዳይ እንደ አንድ መነሻ በማድረግ በርዕሱ ላይ ለመግለፅ የተሞከረውን ጉዳይ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ፅሁፉ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ጥያቄ ውስጥ የሚገባው በምን አይነት መንገድ እንደሆነ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎችን በማናገር ለማካተት ጥረት አድርጓል።በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፕሬስ ሴክራታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን “የአንድ ሰው ከአገር የመንቀሳቀስ መብት የሚታገደው የኢሚግሬሽን አዋጅ ወይም ደንብ ሲጣስ እና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ” መሆኑን ይገልፃሉ።በሌላ በኩል በኢትዮጽያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑት ደጀኔ ግርማ (ዶ/ር) አንድ ሰው የጉዞ እገዳ ሊጣልበት የሚችለው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ እምደሆነ ይገልፃሉ።ከአገር የመውጣት ፈቃድ በፍርድ ቤት ምልከታ የሚወሰን ቢሆንም በመርህ ደረጃ ሊያሳግዱ ከሚችሉት ወንጀሎች ውስጥ "ህገ-መንግስቱን በኃይል መናድ እና የብሔር ወይም ልዩነትን መሠረት ተደርጎ የሚፈጠር ግጭት" እንደሚገኝበት ደጀኔ ግርማ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
ፍርድ ቤት ከአገር እንዳልወጣ የጣለብኝ ክልከላ የለም የሚሉት አቶ ልደቱ አሁን የመከልከሌ ነገር ትክክል አይደለም ከማለት አልቦዘኑም። ከዚህ ቀደም አቶ ልደቱ ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከራከሩና፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር የምስራቅ ሸዋ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ሲሆን የቢሾፍቱ ፖሊስ በበኩሉ አቶ ልደቱ "በአደራ ነው" ያሉት በማለት አልለቅም ማለቱ ይታወሳል።አቶ ልደቱ ፖለቲከኛ በመሆናቸውና በብዙዎች በበጎም ይሁን በአሉታዊ መንገድ እውቅና በማግኘታቸው የእርሳቸውን ጉዳይ አነሳነው እንጂ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጉዳዩ ሌላውንም ዜጋ የሚመለከት ሊሆን ይችላል።
ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ሆኖ ሳለ በየቦታው ያሉ የተለያዩ ባለሥልጣናት በመሰላቸውና እነርሱ በፈቀዱት መንገድ የሚሰጡት ያልተገባ ውሳኔ የዜጎችን መብት ከመጋፋቱም በላይ የፍርድ ቤቶቹን ሥልጣን በእጅጉ የሚቃረን እንደሆነ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚነያነሱት ሃሳብ ነው።
የፍርድ ቤት ውሳኔን ወደ ጎን የሚገፋ አስፈፃሚ ስርዓት አልበኝነት ላለመንገሱ ሊሰጠው የሚችለው መተማመኛ እንደሌለም ይነገራል።
"ዲሞክራሲ፣ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከተፈለገ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበር አለበት" ደጀኔ ግርማ (ዶ/ር) አፅዕኖት ሰጥተው የተናገሩት ሃሳብ ነው።