የካቲት 12 ፣ 2013

ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ከወረረች 100 ቀናት አለፉ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ድንገት የተከሰቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ “የእናት ጡት ነካሾች በብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሰነዘሩበት” ሲሉ ተደመጡ።

ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ከወረረች 100 ቀናት አለፉ

ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ድንገት የተከሰቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ “የእናት ጡት ነካሾች በብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሰነዘሩበት” ሲሉ ተደመጡ። ይህንን ጥቃት ለመመከትና አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም ተናገሩ። ጦርነቱ ተጀመረ። ብሔራዊው የመከላከያ ሠራዊት ተጋርጧል የተባለውን አደጋ ለመቀልበስ በትግራይ የጦር ግጃጅ እየተወጣ በነበረበት ወቅት መልካም አጋጣሚ ያገኘች የመሰላት ሱዳን ድንበር ጥሳ መሬት መውረራን በይፋ ጀመረች።
ለሶስት አስርት ዓመታት ሱዳንን የገዙት የአገሪቱ የቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ምዕራብያውያን ከስልጣኔ ሊነቀንቁኝ እያሴሩ ነው በሚል የሩሲያን እርዳታ ለማግኘት ሞስኮ ሲመላለሱ ቢከርሙም የፈሩት ደርሶ “በዳቦ ዋጋ” ጭማሪ የተነሳባቸው አመፅ በመጨረሻ የስልጣናቸውን ገመድ አሳጥሮ ዘብጥያ እንዳወረዳቸው ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።
ይህንን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣውና ከሲቪሉ እንዲሁም ከወታደራዊ አመራሮች የተውጣጣው ጥምር መንግስት አገሪቱን ለመምራት ስልጣን ተቆናጠጠ። በሂደቱ ማንም የጎረቤት አገር መሪ ሳይቀድማቸው ካርቱም የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥምር መንግስቱ መሪዎች ጋር ወንድሜ ሲባባሉና አዲሱ አስተዳደር መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመው በመመኘት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጎን እንደሆነች ሲናገሩ ከርመዋል።
የሆዳቸውን በሆዳቸው የያዙት የጥምር መንግስቱ አመራሮች በተለይም ወታደራዊን ክንፍ የሚመሩት ጀነራሎች ግን የልብ ሃሳባቸው ምን እንደሆነ በአደባባይ በግልፅ መናገር የጀመሩት ወረራ መፈፀም ከጀመሩ በኋላ ነው። እንደ ወታደራዊ አመራሮቹ ገለፃ ከሆነ የቀድሞው የአሪቱ ፕሬዝደንት ኦማር ሃሰን አልበሽር የአገራችንን ጥቅም አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ይከሷቸዋል። የቀድሞው ፕሬዝደንት የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ የተለሳለሰ አቋም ከማሳየታቸው በተጨማሪ ግዴለሽ ነበሩ የሚል ክስ የሚያቀርቡት የወታደራዊው ክንፍ አመራሮች ከዚህ ቀደም በቅኝ ግዛት ዘመን ተደረገ የተባለን ስምምነትን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ አገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት እ.ኤ.አ. 1972 የሃሳብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመናል፤ ድንበሩንም እንደገና ለማካለል ተስማምተናል ትላለች።
በስምምነቱ መሰረት ሁለታችንም የምንቀበለው የመፍትሄ ሃሳብ ላይ እስክንደርስ ድረስ የድንበር ነባራዊ ሁኔታው ባለበት ተከብሮ እንዲቆይ ስለተስማማን አሁን በሱዳን በኩል እየተካሄደ ያለው አይን ያወጣ የወረራ ድርጊት ነው የሚል አቋም ያላት ኢትዮጵያ አገሪቱ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ እየወተወተች ነው።
ኢትዮጵያ በትግራይ ጉዳይ ላይ መጠመዷን የተረዳችው ሱዳን ግን በማን አለብኝነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በኃይል ከተቆጣጠረች እነሆ 108 ቀናት ሆኗል።የኢትጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ትዕግስት እየተሟጠጠ መምጣቱን የሚጠቁም ሃሳብ የያዘ ፅሁፍ አስነብቧል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በንግግር ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አፅዕኖት ሰጥቶ ካረጋገጠ በኋላ ጦርነት ቢጀመር በሁለቱም አገራት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥፋት ይደርሳል ብሎም ቀጠናው ድብልቅልቁ ይወጣል ይህ ደግሞ ማንንም አይጠቅምም ብሏል።ሱዳን የሶስተኛ ወገን መጠቀሚያ እንዳትሆን ወታደራዊው ክንፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ያለው መግለጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁን ላሳየው ትዕግስት ምስጋና አቅርቧል። መግለጫው አገሪቱ የሶስተኛ ወገን መጠቀሚያ እንዳትሆን ሲል በዋናነት ግብፅን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ለመገመት ይቻላል። ምክንያቱም የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ጀነራል አብዱል አልፋታህ አል ቡርሃን ለይፋዊ ጉብኝት በሚል ግብፅ ሲመላለሱ ከመክረማቸው በተጨማሪ ግብፅ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የሕዳሴውን ግድብ ብሎም የኢትዮጵያን ጥቅሞች ለማኮላሸት ላለመስራቷ ልንሰጠው የምንችለው ማረጋገጫ የለም።
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት መግለጫ የደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ጆንሰን ጁማ ኡኮት ከልዑካቸው ጋር አዲስ አበባ መግባታቸውና ጠንከር ባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ የወጣ መግለጫ መሆኑ ለሱዳን የሚሰጠው ትርጉም እንደሚኖር ይገመታል።
ሱዳን ከወረረችው የኢትዮጵያ ግዛት ካልወጣች ንግግር ብሎ ነገር አይኖርም የምትለው ኢትዮጵያ የምናሳየው ትዕግስት ግን ከፍራቻ እናዳይቆጠር የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ስታንፀባርቅ ቆይታለች።
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ መካረር ወደ ጦርነት ማምራቱ አይቀርም የሚሉ አንዳንድ ተንታኞች የመኖራቸውን ያህል በድርድር ሊፈታ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ የሚያነሱም አልጠፉም። የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግብ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ግን ግዜ ያሳየናል።

አስተያየት