የካቲት 12 ፣ 2013

ስደተኞቹ የት ገቡ?

City: Addis Ababaዜናዎች

ሕ.ወ.ሓ.ት መራሹ ኃይል በብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ብሎ የሰየመው ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ

ስደተኞቹ የት ገቡ?

ሕ.ወ.ሓ.ት መራሹ ኃይል በብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ብሎ የሰየመው ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ መካሄድ ሲጀምር ብዙ ነገሮች መለዋወጥ ጀመሩ።


ከተለዋወጡት ነገሮች መካከል አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ይገኝበታል። ከ100 ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞች እንደሚገኙባት የሚነግርላት ትግራይ ጦርነቱን ተከትሎ በአካባቢው የተፈጠረው ችግር እነዚህን ስደተኞች የገፈቱ ቀማሽ ያደረገ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይ ሽመልባ እና ህፃፅ በተባሉ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ ስደተኞች የደረሰባቸው እንግልት የችግሩን ግዝፈት የሚያሳይ እንደሆነ የአይን እማኞች ይናገራሉ።
በጦርነቱ ወቅት ሽሬ የነበሩትና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ኢጀርሳ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ ሽመልባ እና ህፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከመዘረፋቸው በተጨማሪ ሽመልባ የቃጠሎ አደጋ ደርሶበታል።


የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ መጠለያ ጣብያቸውን ለቀው የሸሹ ስደተኞች ሲመለሱ የስደተኛ ጣቢያቸው ተዘርፎ እንደጠበቃቸው የሚናገሩት አቶ ፀጋዬ የተከሰተው ችግር አስከፊ እንደነበር ይገልፃሉ።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ እነዚህ ሁለት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልፆ የነበረ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲም ሁለቱ ጣቢያዎች ላይ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ ማስታወቁ የሚዘነጋ አይደለም።


እነዚህን የመሳሰሉ ሪፖርቶችን ተከትሎ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ጎበዛይ ከ20 ሺህ በላይ ስደተኞች ይኖሩባቸው እንደነበር የተነገሩትን ጣቢያዎች መዘጋታቸው እንደማይቀር ካስታወቁ በኋላ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ተደርጓል።


በውስጡ የነበሩ ስደተኞችም ወደሌሎች የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚዘዋወሩ መነገሩ የሚታወስ ነው። ለመሆኑ እነዚህ ስደተኞች እንደተባለው ወደተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውረዋል ወይንስ እንደሚነገረው በኤርትራ ጦር ታፍነው ተወስደዋል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ጎበዛይ አዲስ ዘይቤ አነጋግራለች።


እንደ አቶ ተስፋይ ገለፃ ከሆነ 5600 ስደተኞች ወደ አዲ ሃሩሽ እና ማይአይኒ ወደሚባሉ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል ያሉ ሲሆን 5000 የሚሆኑት ስደተኞች ደግሞ አዲስ አበባ እንደሚሆኑ እንገምታለን ብለዋል። ወደ ኤርትራ ታፍነው የተወሰዱ ስደተኞች ስለመኖራቸው ማረጋገጫ እንደሌላቸውም አቶ ተስፋይ ገልፀውልናል።ስደተኞቹ ወደ ሽመልባ እና ህፃፅ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ነግረውናል ያሉን ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የ26 አገራት ዜጎች ይኖራሉ ለእነሱም ከመጠለያ ውጪ የመኖር፣ የስራ ፈቃድ የማግኘት እና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የማግኘት እድል እንዳላቸው ጠቁመው ኤርትራውያን ስደተኞችም ካሉበት በማሰባሰብ የእነዚህ ዕድሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እና አቅም ካላቸው እደማንኛውም የውጪ ዜጋ በከተማ ውስጥ እንዲኖሩ ፍቃድ እንደሚሰጣቸው የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

አስተያየት