በኢትዮጵያ ውስጥ ከበሽታና ከጦርነት ቀጥሎ መጠነ ሰፊ ጎዳት እያደረስ ያለው የትራፊክ አደጋ ስለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለረዥም ሆነ ለአጭር ጉዞ ወዳጅ ዘመዱን የሸኘ ሰው ከሰዓታት በኋላ ስልክ በመደወል “በሰላም ደረስክ ?” “በሰላም ገባሽ ?” በማለት በሰቀቀን መጠየቅ ሀገራዊ ልምድ እየሆነ መጥቷል።
በየዕለቱ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰው አሳዛኝ የሞት ዜና ህፃናትን ያለ አሳዳጊ ወላጆችን ያለ ጧሪ አስቀርቷል። የትራፊክ አደጋ ከገጠር እስከ ከተማ ብዙ ቤተሰቦችን እየበተነ፣ አያሌ የግልና የሀገር ሃብት እያወደመ የየዕለት ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ አምና በ2013 ዓ.ም በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ 2ሺህ 746 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሞተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ባሳለፍነው ዓመት የትራፊክ አደጋ የ853 ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አዳነ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የደረሰው የትራፊክ አደጋ እና በአደጋው ምክንያት የተመዘገበው ሞት ከ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር መቀነሱን ይገልጻሉ።
ከሞቱት 853 ሰዎች በተጨማሪም 674 ሰዎች ለከባድ እንዲሁም 830 ሰዎች ለቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን የክልሉ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን መረጃ ያሳያል።
አቶ ብርሃኑ ታደሰ በስራው ምክንያት አዘውትሮ የህዝብ ትራንስፖርት ይጠቀማል። ከስድስት ወር በፊት ከስራ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲጓዝ በደረሰበት የትራፊክ አደጋ በሁለት እግሮቹ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህ ምክንያት ለወራት እግሮቹ በጀሶ ታስረው ሆስፒታል አልጋ ላይ መቆየቱን ይናገራል። የአደጋው መንስዔ በዕለቱ ታክሲው ሙሉ ሰው ጭኖ ሾፌሩ ቢጠበቅ በመዘግየቱ ምክንያት ረዳቱ ልምድ ሳይኖረው ሲያሽከረክር አደጋው መድረሱን ያስታውሳል።
እንደ ብርሃኑ ገለፃ አደጋ ከደረሰበት በኃላ ትራንስፖርት ሲጠቀም ተሸከርካሪው ፍጥነት ከጨመረ ምቾት እንደማይሰማው ይናግራል። “አሁን ላይ ትራንስፖርት ስጠቀም ከአደጋው በፊት የማላስተውላቸውን የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ማስተዋል ጀምራለሁ። ከአሁን አሁን አደጋ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለብኝ” ይላል ከአደጋው በኃላ ያደረብትን የስነ ልቦና ችግር ሲያስረዳ።
የስነ ልቦና ባለሞያዎች እንደሚሉት አደጋ ከተፈጠረ በኋላ ከአደጋ የተረፈ ሰው የስነ ልቦና ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። ይህም በህክምና ሳይንስ አጠራር Post traumatic stress disorder /የድህረ አደጋ የጭንቀት መታወክ/ ሊባል ይችላል። ይህ ችግር ከአደጋ የተረፉ ሰዎች ላይ አደጋውን በማስታወስ መሸበርን የሚያሰከትል የአዕምሮ መታወክ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባስጠናው ጥናት በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ከሚያልፉ ሰዎች መካከል ተሳፋሪዎች አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ፤ ይህም 48.1 በመቶ ነው። የተቀረውን 43.2 በመቶ የሚሸፍኑት በትራፊክ አደጋ ለሞት የሚዳረጉ እግረኞች እንዲሁም 8.7 በመቶ አሽከርካሪዎች ናቸው።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ በ2014 በጀት ዓመት (ከሃምሌ 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም ድረስ) ባለው ጊዜ ውስጥ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ከሰው ሕይወት እና አካል ጉዳት በተጨማሪ 57 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ወድሟል። በዚህም የንብረት ውድመቱ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በ16 በመቶ ብልጫ ያሳያል።
በአጠቃላይ በአማራ ክልል በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች 625 ተሸከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድርሷል። በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት 887 ተሸካርካሪዎች የትራፊክ አደጋ አስተናግደው እንደነበር የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ያትታል።
በዓመቱ ውስጥ የተመዘገበው ጠቅላላ የትራፊክ አደጋ ብዛት 1,539 ሲሆን በ2013 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ተከስቶ ከነበረዉ 2,295 የትራፊክ አደጋ ጉዳት ጋር ሲነፃፀር በ56 በመቶ የአደጋ ጉዳት መጠን የቀነሰ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
ይህን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያው አቶ ደሳለኝ አዳነ ሲናገሩ የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን በትራፊክ ድህንነት ዙሪያ በሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ እንቅስቃሴ፣ የቆጥጥር ስራ እና በሌሎች ምክንያቶች የአደጋው መጠን ሊቀንስ እንደቻለ ይገልፃሉ።
አቶ ደሳለኝ ለአዲስ ዘይቤ እንዳስረዱት ባለፈው በጀት ዓመት በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችና የወደመው ንብረት ለመቀነሱ ከግንዛቤ ስራና ቁጥጥር በተጨማሪ በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት የትራፊክ እንቅስቃሴው ደካማ መሆኑ አስተዋፅዖ አድርጓል።
በክልሉ ከትራፊክ ደህንነት ቁጥጥሩን በማጠናከር ባለፈው በጀት ዓመት ከመንገድ ደህንነት ቁጥጥር (ከራዳርና መደበኛ ቁጥጥር)፣ ከመናኸሪያ ቅጣት እና ከድንገተኛ የተሽከርካሪ ምርመራ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ሪፖርቱ ያሳያል።
የባህር ዳር የመንግስትና የልማት ድርጅት ሾፌሮች አንድነት ማህበር በርካታ አባላት ያሉት ሲሆን ማህበሩ በዋናነት አሽከርካሪዎች በማህበር ተደራጅተው መብትና ግዴታቸውን እንዲወጡ የተቋቋመ ነው። አባላቱ ለስራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ማህበሩ በመንገድ ላይ ምልክቶች እና የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየሰራ አንደሚገኝ የማህበሩ ፀሐፊ አቶ ቁምላቸው እርቀየሱስ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባስጠናው ጥናት በአገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 68.3 በመቶ ያህሉ ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ የሚከሰቱ መሆቸውን ይገልጻል። በሌላ በኩል ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል ትልቁን ድርሻ (85.9 በመቶ) የሚይዘው በአሽከርካሪ ስህተት የሚፈጠር ሆኖ ተመዝግቧል። በተጨማሪም 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶ በእግረኛ ችግር እንዲሁም 0.7 በመቶ በመንገድ ችግር የሚከሰቱ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል።
ይሁንና በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን መጠነ ሰፊ የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የተመለከተ የተሟላና ፈጣን መረጃ ማግኘት ዛሬም ከባድ እንደሆነ ቀጥሏል። በዚህ ዘርፍ የትራፊክ አደጋ መረጃ ስርዓትን ማዘመን ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን መረጃ ወጥ በሆነ መልኩ ለማደራጀት የሚያግዝ የመንገድ ደህንነት አደጋ የመረጃ ስርዓትን (road accident data management system) ለማበልፀግ 'ኢፒቲሳ' ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል። የመረጃ ስርዓቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተነግሯል።
የፌዴራል መንገድ ደኅንነትና የመንገድ ፈንድ አገልግሎት እንዳሳወቀው በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2013 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ 4,161 የሞት አደጋ ደርሷል። በዚህም በ2014 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ከደረሰው 3,971 ሰዎች ሞት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ዓመት በ190 ቀንሷል።
በአገልግሎቱ መረጃ መሰረት በዓመቱ ውስጥ በትራፊክ አደጋ ከደረሰው የሞት አደጋ በተጨማሪ 5,911 ከባድ እና 4,739 ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2014 ዓ.ም 14,621 የትራፊክ አደጋ እንደተመዘገበ ማወቅ ተችሏል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከ22 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በ183 ወረዳዎች ውስጥ ይኖራል። በክልሉ 231 መናኸሪያዎች፣ 2,383 የስምሪት መስመሮች፣ 131,750 ታርጋ የተሰጣቸው ተሸከርካሪዎች፣ 137 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ 122 የከተማ ትራንስፖርት ማህበራት፣ 59 የሕዝብ ትራንስፖርት ማህበራት፣ 5 የትራፊክ ኮምፕሌክሶች እንደሚገኙ ከክልሉ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።