የካቲት 25 ፣ 2013

“ባልደራስ ኦፌኮን ተከትሎ ከምርጫው አልወጣም” - በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር)

ዜናዎች

ከዚህ ቀደም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ የባልደራስ አመራሮች

“ባልደራስ ኦፌኮን ተከትሎ ከምርጫው አልወጣም” - በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር)

ከዚህ ቀደም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ የባልደራስ አመራሮች በተራዘመ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ እንዳሉ በመጥቀስ "የምንገባበት ምርጫ እጅግ አሳስቦናል፤ ምርጫው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዘመን የተለመደውን የምርጫ ዓይነት ሊሆን ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ፓርቲው በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የመወዳደሩ ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ እንደነበር የሚታወስ ነው።


በዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ባልደራስ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)ን ተከትሎ ከምርጫው ይወጣ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ለፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።


ኃላፊው ሲመልሱ “በዘንድሮው ምርጫ ላይ እንወዳደራለን፤ ከምርጫው ፈፅሞ አልወጣንም” ካሉ በኋላ “የዕጩዎች ምዝገባ ዛሬ ስለሚጠናቀቅ ዕጩዎቻችንን አቅርበን እያጠናቀቅን ነው” ብለዋል።


“እኔ ራሴ ዕጩ ሆኜ ሰኞ ዕለት (የካቲት 22፤ 2013 ዓ.ም) ተመዝግቤያለሁ” ያሉን በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) “የዕጩዎች ምዝገባ ዛሬ ከሰዓት ማለቅ ስላለበት የኔ ጓደኞችም እየተመዘገቡ ነው” ሲሉ ነግረውናል።


የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው “ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23፤ ለአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ደግሞ 138 ዕጩዎችን እንደሚያቀርቡ” ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።


የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ እስክንድር ነጋ ላይ  አቃቤ ሕግ የፀረ-ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ክስ እንደመሰረተባቸው የሚታወቅ ነው። 


አቶ እስክንድር ከነበሩበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ “ለውጡ” ከመምጣቱ በፊት ወደነበሩበት አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በተለምዶ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውም አይረሳም።

አስተያየት