ከ43 ዓመታት በፊት 1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ በጎረቤቷ ሶማሊያ ወረራ ተፈፀመባት። “ታላቋን ሶማሊያ" ለመመስረት የወጠኑት የወቅቱ የሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ ህልማቸውን ለማስፈፀም ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛት አካል የቻሉትን ቆርሶ መውሰድ መልካም አማራጭ እንደሆነ ታያቸው።
ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊ የሰው ኃይል፣ የስንቅ፣ የትጥቅ እና የሥነ ልቦና ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ሶማሊያ ወረራዋን በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ብላ ጀመረች።
በሕዝብ የተመረጡትን አብዲራሺድ አሊ ሽመርኬን ያለደም መፋሰስ ከስልጣን ገልብጠው በቦታቸው የተተኩት ዚያድ ባሬ በወቅቱ ከንጉሳዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊው ደርግ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ በደቡብ በኩል ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ዘልቀው ገቡ። በዚህ ጥቃት ሳቢያ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፣ ሃብት ንብረታቸው ተዘረፈ፤ ተፈናቀሉ።
የሶማሊያ ጦር ወደ ሐረር ግስጋሴውን ሲቀጥል የክተት አዋጅ ያወጀችው ኢትዮጵያ ሐረር ላይ 40 ሺህ ገደማ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል አዘጋጅታ ጠበቀች። ኢትዮጵያን ወሮ መሬት ለመውሰድ የመጣው የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ድል እየተነሳ በምትኩ የኢትዮጵያ ጦር አሸናፊነቱ እርግጥ እየሆነ መጣ።
መደበኛውና ሕዝባዊው ሠራዊት በጋራ በወሰዱት የአጸፋ ጥቃት የሶማሊያ ጦር በጅግጅጋ ካራማራ ተራራ ላይ የተደመሰሰው ከዛሬ 43 ዓመት በፊት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. እንደሆነ ታሪክ ይናገራል።
በዚህ ጦርነት ከ16ሺህ በላይ የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የሶማልያ ወራሪ ኃይልን ተዋግተዋል።
አሁን በእርስ በርስ ጦርነት የምትሰቃየው የመን፣ ምስራቅ ጀርመን እና ሰሜን ኮሪያ እንዲሁም ሌሎች አገራት ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል።
የቀድሞው ኢህአዴግ በጠመንጃ አፈ-ሙዝ ሥልጣን የያዘበትን ወቅት በመንግስት ደረጃ የምታስበው ኢትዮጵያ ጠላት የተሸነፈበትን የካራማራን ድል ግን ከደርግ ውድቀት በኋላ በመንግስት ደረጃ የማይከበር አድርጋዋለች። የቀድሞ ሰራዊት አባላትና ግለሰቦች ግን በራሳቸው ተነሳሽነት ያከብሩታል።
የዘንድሮው 43ኛ ዓመት የካራማራ የድል በዓልም በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት ፓርክ ተከብሯል። በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ በጦርነቱ የተሳተፉ የሠራዊቱ አባላት፣ አርበኞች፣ የኩባ ሪፐብሊክ አምባሳደር እና ድሉን ለማሰብ የተሰባሰቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ታድመዋል።
የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያሳዩበት በመሆኑ ተመጣጣኝ ክብርና እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባም በድል በዓሉ ላይ ተነግሯል።
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ካደረገችው ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ ጀመረች። ዚያድ ባሬም 1983 ዓ.ም ላይ ከሥልጣን ተወግደው ወደ ናይጄሪያ ሸሹ። ሕልፈተ ሕይወታቸውም ለአራት ዓመታት በስደት በቆዩባት ናይጄሪያ ሆነ።