የካቲት 26 ፣ 2013

ኮሮና ኢትዮጵያ ውስጥ “እንደሌለ” በተግባር የሚያስተምሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ኮሮና ከየት ወዴት?

ኮሮና ኢትዮጵያ ውስጥ “እንደሌለ” በተግባር የሚያስተምሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት

ከአንድ አመት ገደማ በፊት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በመስሪያ ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት የተሰየሙት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን በይፋ አስታወቁ። ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አንድ ጃፓናዊ የ48 አመት ጎልማሳ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ከገለፁ በኋላ ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው ሲሉ ተናገሩ።

“በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ኢትዮጵያ መግባቱ ተረጋገጠ” የሚለውን የሚኒስትሯን መግለጫ ተከትሎ እንቅስቃሴ የሚበዛባት አዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች ከወትሮውን እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጎሉ። ታክሲዎች መጫን ከሚችሉት የተሳፋሪ አቅም ውስጥ ግማሹን ቀንሰው እንዲጭኑ ተባለ። የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በተለይ አልኮል እና ሳኒታይዘር ታስሰው የማይገኙ ውድ ቁሶች ሆኑ። ለወትሮው በተነፃፃሪነት ብዙም ፈላጊ ያልነበረውና በየመድኃኒት ቤቱ መደርደሪያ ላይ በቀላሉ ይገኝ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) ኮሮና ገባ ሲባል ከ5 እና 10 ብር ተነስቶ እስከ 500 ብር ተሸጠ። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዕጅ እናስታጥብ በሚሉ በጎ ፍቃደኞች ተሞሉ። አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር በሚኖረው ግንኙነት 2 ሜትር ወይንም 2 የአዋቂ ዕርምጃ ያህል መራራቅ እንሚገባ በስፋት ተሰበከ። ቫይረሱን ለመከላከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) ማድረግ ስላለው ጠቀሜታም የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ይወተውቱ ጀመር።


በወቅቱ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ዜና ዕረፍት መነገር ሲጀምር የሰዎች ፍርሃትም እየጨመረ መጣ፤ ጎዳናዎች ጭር አሉ።


ይህ ሁሉ ነገር ከሆነ አንድ አመት ሊሞላው የሳምንታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። እነሆ አሁን ደግሞ “የኮሮና ቫይረስ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ጠፋ” የተባለ ይመስል ያኔ ይደረግ የነበረው አይነት የጥንቃቄ እርምጃ አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው ሰዎችና የጤና ሚኒስቴር ይገልፃሉ።


በአዲስ አበባ ኑሮዋን ያደረገችው ሜሮን ንብረት በኮቪድ ቫይረስ ሳቢያ 2 ቤተሰቦቿን በሞት ተነጥቃለች።


“የቫይረሱ አሳሳቢነት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንዳልሆነ” የምትናገረው ሜሮን “በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ገባ በተባለበት ሰሞን ሲደረግ የነበረው የጥንቃቄ እርምጃ አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ የመቀዛቀዙ ምክንያት ምን እንደሆነ” ትጠይቃለች።

“የአፍ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ከማድረግ፣ ሳኒታይዘር ከመጠቀም እና አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ ባለፈ አንገብጋቢ ካልሆነ በስተቀር ሕዝባዊ መሰባሰቡ ቢቀር” የምትለው ሜሮን “የአደባባይ ኃይማኖታዊ በዓሎች ከጥንቃቄ ጋር ቢከበሩ ነገር ግን አገራዊ በዓላት ሁሉም ባለበት ታስቦ ቢውል፤ በተለይ ደግሞ ለተለያዩ አላማዎች የሚደረጉ ሕዝባዊ ሰልፎች ቢቀሩ የተሻለ” እንደሆነ ትናገራለች።


ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ግዜ ድረስ በኢትዮጽያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 162,954 ደርሷል፤ 2,394 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።


የጤና ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ላይ በ2 ተከታታይ ቀናት ብቻ 615 ሰዎች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል መግባታቸውን እና የ29 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽን ውስንነት በመኖሩ አገልግሎቱ በወረፉ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ኃላፊው “ርቀትን በመጠበቅ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም እጅን በመታጠብ ለኅብረተሰቡ አርአያ ሆኖ መገኘት ይገባል” ቢሉም በተለያዩ አካባቢዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደረጉ የተባሉ የድጋፍ ሰልፎች እና ሕዝባዊ በዓላት ላይ የታየው ድርጊት የቫይረሱን ስርጭት የሚያስፋፋ እንጂ የሚገድብ እንዳልሆነ መታዘባቸውን አስተያየታቸውን የሰጡን ሰዎች ተናግረዋል።


በቅርቡ የሲዳማ ክልል ይፋዊ የምስረታ በዓል ላይ ታድመው የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌንዳሞ ጋር እንኳን 2 ሜትር ሊራራቁ ቀርቶ አፍ ለአፍ ገጥመው የሚጠጣ ነገር ሲጎነጩ የሚያሳየው ፎቶ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ፍቅርን፤ በኅብረት መኖርን የሚያስተምር ቢሆንም በሌላ በኩል ግን በዘመነ ኮሮና ይህን ያህል መዘናጋት ሕዝቡ “ኮሮና የለም” ወደሚል ድምዳሜ እንዲያመራ የሚያደርግ ነው የሚል አስተያየት ይደመጣል።“ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የድጋፍ ሰልፍ ስለሚኖረን የካቲት 03 ቀን 2013 ዓ.ም ከ2:30 ጀምሮ በከንቲባው ጽ/ቤት ተገኝታችሁ ድጋፋችሁን እንድታሳውቁ እየገለፅን ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚደረግ በተባለው ሰዓት በቦታው እንድትገኙ እናሳውቃለን” በሚል ቀጭን መልዕክት ለድጋፍ ወጣ የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል፤ በድጋፍ ሰልፉ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) ካላደረገ መሳተፍ እንደማይችል እና ርቀቱን መጠበቅ እንደሚኖርበት ለዚህም ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚካሄድ የሚገልፅ መልዕክት ግን የመግለጫው አካል አለመሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።


የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ግን የቫይረሱ ጥቃት አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ ከመናገር አልተቆጠቡም። “ሁሉም የመተንፈሻ መሳሪያዎች በህመምተኞች ተይዘው ሌላው የጠናበት ህመምተኛ መሳሪያውን በሞት እና በሕይወት መካከል ሆኖ እየጠበቀ ነው” የሚሉት የጤና ሚኒስትሯ “በአዲስ አበባ 54 በመቶ በአገር ደረጃ ደግሞ 35 በመቶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) ተጠቃሚዎች ቁጥር እንደቀነሰ” ተናግረዋል።


“በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው አዲስዓለም ጌጡ በኅብረተሰቡ ዘንድ የጥንቃቄ መቀዛቀዝ” መኖሩን ገልፆ “ይህም የመንግስት አካላት እርምጃ መውሰድ ባለመቻላቸው እንደሆነ” ይናገራል።


አዲስዓለም እንደሚለው “ምንም እንኳን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ከባድ ቢሆንም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) እና ሳኒታይዘር መጠቀም ግን ከባድ አይመስለኝም” ይላል።“በተለይም ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው የእምነት ተቋማት፣ ክብረ-በዓሎች እና ሰልፎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ከባድ ስለሚሆን በተወሰነ ሰው እና ለሁሉም ወጥ በሆነ መልኩ መደረግ” እንደሚገባውም ያነሳል። “ባሥልጣናት ጥንቃቄዎችን ለአጭር ጊዜ ከማሳየት ባለፈ ቋሚ የሆነ ነገር እንዳልተመለከተም” አክሏል።


“በኃይማኖታዊ በዓላት፣ ስፖርታዊ ክንውኖች፣ በተለያዩ ዝግጅቶች፣ ካፌ እና ሬስቶራንቶች ውስጥ በአጠቃላይ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ” የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ቢገልፁም እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው እንደሆነ በተጨባጭ የሚታየው ሁነት አስረጂ ነው።ለመሆኑ ከሰሞኑ ሲካሄዱ የሰነበቱ የድጋፍ ሰልፎችና በዓላት ላይ የነበረውን ሁኔታ የጤና ሚኒስቴር እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄ ለጤና ሚኒስቴር ለማቅረብ ያደረግነው ሙከራ የሚመለከታቸው አካላት “ጉባዔ ተቀምጠዋል” በሚል የተደጋገመ ሰበብ ሳይሳካ ቀርቷል።“ተራቀዋል” የሚባሉትን አገራት ጭምር ያርበደበደው የኮሮና ቫይረስ ገና በዕርዳታ ክትባት የምትጠብቀው አገር ላይ ቀለል ተደርጎ መታየቱ የሚያስከፍለን ዋጋ ምን ያህል እንደሚሆን ግን በግዜ ሂደት ይታያል።

አስተያየት