የካቲት 26 ፣ 2013

‹‹ያስመጣናቸውን ማሽነሪዎች እና ተሽርካሪዎች እንዳናስገባ ተከልክለናል››ባለሐብቶች

ዜናዎች

በሶማሌ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሐብቶች ከውጭ ያስመጧቸውን ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ወደ ሐገር ውስጥ

‹‹ያስመጣናቸውን ማሽነሪዎች እና ተሽርካሪዎች እንዳናስገባ ተከልክለናል››ባለሐብቶች

በሶማሌ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሐብቶች ከውጭ ያስመጧቸውን ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ወደ ሐገር ውስጥ ማስገባት አለመቻላቸውን ተናገረዋል፡፡ በክልሉ ለኢንቨስትመንት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በልማት ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ወደ ሐገር ውስጥ የተመለሱት ባለሐብቶቹ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ 'ዲያስፖራዎች' እና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ናቸው፡፡

ባለሐብቶቹ ከቀረጥ ነጻ እንዳናስገባ ተከልክለናል ያሏቸውን ማሽነሪዎች እና ተሸርካሪዎች የጀመሯቸውን የልማት ሥራዎች ለማጠነከርና ለማስፋፋት ሊጠቀሙባቸው እንዳሰቡ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከጅግጅጋ ዘግቧል፡፡

ኢንቨስተሮች ለሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች የሚሆኑ መገልገያዎችን ከቀረጥ ነፃ ወደ ሐገር ውስጥ እንዲያስገቡ በተሰጠው ዕድል መሰረት ሕጋዊ መሰፈርቶችን በሟሟላት ማሽነሪዎቹን እና ተሽከርካሪዎቹን ቢያስመጡም፣ የፌደራል የጉምሩክ ኮሚሽን ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ወደ ክልሉ እንዳያስገቡ ከልክሏቸዋል፡፡


እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ወደብ የደረሱት ንብረቶች ለወራት ወደብ ላይ በመቆየታቸው ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገዋል፡፡ ዩሱፍ አብዱላሂ የተባሉ ቅሬታ አቅራቢ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ


"ተሽከርካሪዎቹ ከሁለት ወር በላይ ወቻሌ እና በርበራ ወደብ በመቆማቸው ለቆዩበት ኪራይ ለመክፈል ተገደናል፡፡ ይህ ተጨማሪና አላስፈላጊ ወጪ ነው›› ብለዋል፡፡በክልሉ መዋአለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት ባለሐብቶች ጉዳያቸው እልባት እንዲያገኝ ወደ ጉምሩክ ኮሚሽን ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ቢመላለሱም መፍትሔ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ድሬዳዋን ጨምሮ ሌሎች የጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የቀረጥ ነፃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡›› የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አገልግሎቱን ያቋረጠበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው አስረድተዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የዲያስፖራና የኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲአዚዝ መሀመድ ባለሀብቶቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው የባለሀብቶቹን ቅሬታ አስመልክቶ ቢሮው ለኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደብዳቤ ቢጽፍም እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል። የተነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ በፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምላሽ እንዲሰጥበት በአዲስ ዘይቤ የጅግጅጋ ሪፖርተር በኩል ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

አስተያየት