የካቲት 26 ፣ 2013

አገልግሎት የማይሰጡት ሕንጻዎች እጣ ፈንታ ምንድነው?

ዜናዎች

ጎንደር ከተማ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው እየተነሱ የሚበርዱ ግጭቶች ውስጥ እንደነበረች ይታወቃል

አገልግሎት የማይሰጡት ሕንጻዎች እጣ ፈንታ ምንድነው?

ጎንደር ከተማ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው እየተነሱ የሚበርዱ ግጭቶች ውስጥ እንደነበረች ይታወቃል፡፡ በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚፈነዳው አመጽ መሰረተ-ልማቶችን አጥፍቷል፡፡ ከመንግሥት እስከ ግለሰብ፣ ንብረቶችን ለውድመት ዳርጓል፡፡ 

በወቅቱ ለጥቃት የተዳረጉት ሕንፃዎች ከግርግሩ ማብቃት በኋላ አሁንም ድረስ ከነጠባሳቸው ይታያሉ::ሕንፃዎቹ የተጎዱት፤ ድንጋይ ይዘው አደባባይ በወጡት የአመጹ ተሳታፊዎች ዘንድ፤ ባለቤቶቻቸው "የሥርአቱ ተላላኪዎች" እና "አገልጋዮች" እንዲሁም "በድብቅ ጉዳይ አስፈፃሚዎች" በሚል ምክንያት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ 

ይሁን እንጂ ከነበረው መንግሥታዊ አስተዳደር ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት ያልነበራቸው ግለሰቦችም ጥሪታቸው በአደባባይ አመጹ ተጎድቷል፡፡ሥራ ፈትተው የቆሙትን ሕንጻዎች በተመለከተ መንግሥት ምን ማድረግ ነበረበት ስንል የሕግ ባለሙያ ጠይቀናል፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ አብዲ በሰጡት ምላሽ  ‹‹ሰላም እና ጸጥታን ማስፈን የመንግሥት ሥራ ነው:: ሰዎች ሕንጻ የሚገነቡት ዛሬ ከተገነባው ነገር ነገ እጠቀማለሁ ብለው ነው፡፡ ግብር የሚከፍሉትም መንግሥት ባለው መዋቅር ንብረታቸውን እንደሚጠብቅ ተማምነው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ ክስተት በሚያጋጥምበት ጊዜ መንግሥት ማድረግ የሚችለው ጥፋተኞችን ለፍርድ ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የግለሰብ ንብረት ላይ ጣልቃ ገብቶ ተጠቀሙበት ወይም አትጠቀሙበት ሊል አይችልም፡፡ እግድ ካለ ወይም ሕገወጥ ሥራ ከተሰራበት ብቻ ነው ጣልቃ የሚገባው፡፡ ቦታው ለኢንቨስትመንት የተሰጠ ከሆነ ግን በተመደበለት ጊዜ ወደ ሥራ ካልገባ ለሌላ አልሚ አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል›› ብለዋል፡፡
 

በዚህ ዘገባ ላይ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የንግድ ምክር ቤት አባል ለአዲስ ዘይቤ አንደተናገሩት ‹‹አንዳንድ የሕንጻ ባለቤቶች ከመስተዳድሩ ካሳ ተቀብለዋል፡፡ ቤቶቹን አስተካክለው ሥራ ለመጀመር ግን ይፈራሉ፡፡ የቀድሞው ስርአት ደጋፊዎች እንደሆኑ የሚያምኑ ሰዎች ድጋሚ የሚያጠቋቸው ዐይነት ስሜት እንዳለባቸው ሰምቻለሁ›› ብለውናል፡፡ 
 

ባለሐብቶቹ አሁን የሚገኝበትን ቦታ በተመለከተም ‹‹አዲስ አበባ ወይም በሌሎች የሐገሪቱ ክፍሎች እንጂ ጎንደር ውስጥ የሉም›› የሚል ምላሽ አግኝተናል፡፡የጎንደር ከተማ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ቻላቸው ዳኜ በበኩላቸው ‹‹በወቅቱ በነበረው ሕዝባዊ ትግል በአጠቃላይ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሕንጻዎች አሉ:: ከለውጡ ወዲህም አብዛኛዎቹ ከእድሳት በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ግለሰቦቹ ቀርበው ወደ ሥራ ለመግባት የመዘግየት ሁኔታ አለ፡፡ በሂደት የምንፈታው ይሆናል›› ብለዋል፡፡

በቀጣይ ለሕንጻዎቹ ባለቤቶች ጥሪ እንደሚደረግና በሒደት ሕንጻዎቹ ሥራ የሚጀምሩበት መንገድ እንደሚመቻች ሰምተናል፡፡

አስተያየት