መጋቢት 4 ፣ 2013

“የዓለም የሴቶች ቀንን የማክበር ቀልድ"

ወቅታዊ ጉዳዮችበብዛት እየተወራ ያለጉዳይ

(100 ዓመት ያለፋቸው ያልተመለሱ ጥያቄዎች)

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed for the past five years.

“የዓለም የሴቶች ቀንን የማክበር ቀልድ"

(100 ዓመት ያለፋቸው ያልተመለሱ ጥያቄዎች)

የሴቶች ቀን ሲከበር 100 ዓመት አለፈው፡፡ ዓለም የክብረ በዓሉን አስፈላጊነት አስመልክቶ መናገርና ማክበር ከጀመረች 110ኛ ልደቷን አክብራለች፡፡ በኢትዮጵያም የአንድ ጎልማሳን እድሜ ያህል አስቆጠረ፡፡ የዘንድሮው የሴቶች ቀን ሲከበር ለ45ኛ ጊዜ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ያላገኘው ኖቬምበር (ህዳር) 19 የሚከበረው የወንዶች ቀን እውቅና ያገኘውን በመላው ዓለም የሚከበረውን የሴቶች ቀን በዓል በልጦታል።

የዓለም አቀፉ የሴቶች ክብረ በዓል መነሻ የሥራ ሰዓት ይሻሻል፣ የተሻለ ክፍያ ይኑር፣ ሴቶች በምርጫ ይሳተፉ የሚለውን የመብት ጥያቄ ያነገቡ15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች አደባባይ መውጣታቸው ነበር፡፡ ይሕም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ የመጀመርያውን ብሄራዊ ቀን ከማወጁ አንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ1908 መሆኑ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ 110 ዓመት ቢሆነውም መልስ አላገኘም፡፡ የሥራ ሰዓት ማሻሻያ፣ የተሻለ ክፍያ እና የምርጫ ተሳትፎ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶችም ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከነባሩ የወዛደሮች ጥያቄ እስከ ዘመነኛው #me-too (#እኔም)እንቅስቃሴ ድረስ ሴቷ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሏት፡፡ ከአያት የተወረሰው የመብት ጥያቄ የልጅ ልጅ ላይም አልተመለሰም፡፡ "ዛሬም የሴቶች ቀን የመድረክ ማድመቂያ፣ የትርኢት ማሳመሪያ ነው፡፡ ፕሮፖዛሎቹ ዕለቱን አስውበው የሚያልፉ፣ የጥቂቶችን ኪስ የሚያደልቡ እንጂ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጡ አይደሉም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ለ45 ዓመታት አከበርነው፡፡ አሁንስ አይበቃም? እለቱን አክብረን ሴቷን ከናቅን ለምን አይቀርብንም?" የሚል አንድምታ ያለው ሀሳብ ያናገርናቸው ሠዎች አጋርተውናል።

በዚህ ጽሁፍ "መብቴ ካልተከበረ ቀኑን አላከብርም" የሚሉ ሴቶችን ሀሳብ በመያዝ እና እንዲህ ለማለት ያበቃቸውን ችግር ለአንባቢ ለማድረስ እንሞክራለን፡፡

ክብረ በዓሉን በጥቂቱ

የዚህ ዓመቱ አከባበር አምና ዕንዳየነው ነበር፡፡ ‘ማርች 8ትን ማክበር እንዴት ተጀመረ?’ በሚል መዛግብት ተነበቡ፤ በሐበሻ ቀሚስ የደመቁ ሴት ባለሥልጣናት በሚያምር ፈገግታቸው ‘የእንኳን አደረሳችሁ!’ መልእክት አስተላለፉ፤ ‘ሴቷ የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል ናት!’፣ ‘ሴት ልጅ እህት ናት!’፣ ‘እናት ናት!’፣ ‘ሚስት ናት!’፣ ‘ልጅ ናት!’፣ ‘አክስት ናት!’፣ ‘አያት ናት!’ የሚለው "ያረጀ ያፈጀ" ፈሊጥ  መገናኛ ብዙኃን ናኘ፡፡ የካቲት 28 (ማርች ሰባትን) እና የካቲት 30 (ማርች ዘጠኝን) የማይመስል ወሬ ማርች ስምንት ላይ ተደመጠ፡፡ ቄጠማ ተጎዘጎዘ፣ ዳቦ ተቆረሰ፣ እልልታ ቀለጠ፡፡ ‘ሴቷ ትችላለች!’ የሚል መፈክር ተደመጠ፡፡ ሴትን አሞጋሽ ዘፈኖች አየሩን ሞሉት፡፡ ጥቂት ስኬታማ ሴቶች ስማቸው ተነሳ፡፡ አበቃ! በቀጣይ ዓመትም ከዚህ የዘለለ አከባበር እንደማይኖር ለመናገር ነቢይ መሆን ላያስፈልግ ይችላል፡፡

ታሪክ ሲገላበጥ የሀገሪቱን ጀግና ሴቶች፦ የሲዳማዋ ንግሥት ፉራ፣ የጉራጌዋ የቃቄ ወርድወት፤ የአርበኞቹ ወ/ሮ ከበደች ሥዩም፣ የወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ፣ ንግሥት ሳባ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ መስቀል ክብራ፣… ሲዘከሩ እንኳን አልተስተዋለም፡፡ ምሳሌው ሁሉ ባህር ተሻግሮ የመጣ ነው ይመስላል። ሐገረሰባዊ ዕውቀት፣ ታሪክ እና እውነት፣ አጠያየቁም አመላለሱም ሀገሪቱን አይመስልም፡፡

ሴቶች በፊልም እና ሙዚቃ ውስጥ

አንድ ማኅበረሰብ ራሱን ከሚገልጽባቸው መንገዶች ውስጥ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ ሐሳብን እና አስተሳሰብን ማሳያ ሥራዎች ውስጥ ሴቶች በምን መልኩ እንደተነሱ ስንመለከት አለስደንጋጭ ይሆናል፡፡ ፊልሞች ውስጥ የተሳለችው ሴት ማንም ገንዘብ ያለው ሰው ሁሉም የሚወስዳት፣ በተፈጥሯዊ ቁመናዋ ብቻ የምትመካ እና ህይወቷ በወንድ ፈቃድ የተመሠረተች ናት፡፡ ለወንዱም ከወሲባዊ አገልግሎቶች የዘለለ አበርክቶዋም አነስተኛ እንደሆነ በተደጋግሚ ይታያል፡፡ ይህንን መሰል ፊልሞች መሠራታቸው የገሀዱዓለም ነፀብራቅ ቢሆንም እነዚህ መበራከታቸው በሌላኛው በኩል ያሉትን የሴቶች ማንነት ዕንዳይታይ አድርጎታል። በጅምላ ለመፈረጅም ጭምር!

ይህንን ጽሑፍ ለማሰናዳት ካነጋገርኳቸው መካከል የሆነችው ወጣት ማስተዋል ካሰሳሁን "ቀኑ ከመከበሩ በፊት ባለ ቀኗ ለእራሷ እና ሌሎች ለባለቀኗ ያላቸውን አስተሳሰብ በተለይም በባህል ደረጃ መሞረድ ተቀዳሚ የቤት ሥራ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ቀኑን ማክበር የቀልድ ከመሆን አይዘልም፡፡" የሚል ሐሳብ ሰጥታኛለች፡፡ ማሰተዋል በመደምደሚያዋ ‹‹ሴት ልጅ እናት ባትሆንም በሴትነቷ ብቻ የምትከበርበትን ጊዜ እናፍቃለሁ!›› ብላናለች፡፡

የሥራ ሰዓት

ማርች ስምንትን ከወለዱት ጥያቄዎች አንዱ የሥራ ሰዓት ይሻሻል የሚል ጥያቄ ነው፡፡ የፋብሪከ ሠራተኛ ሴቶች ከ8 ሰዓታት (ሕጉ ከሚፈቅደው) በላይ ሥራ ላይ ማሳለፋቸውን የተቃወሙ ሴቶች ናቸው አደባባይ የወጡት፡፡ ከ100 ዓመት በፊት የተጠየቀው ጥያቄ ግን አሁንም ጥያቄ እንደሆነ አለ፡፡

 በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች በአማካይ ከወንዶች የበለጠ ይሠራሉ ነገርግን በክፍያ በ16% ያንሳሉ። የሚሠሯቸው ሥራዎች ምንም እንኳን አድካሚ እና አስፈላጊ ቢሆንም ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ አይከፈላቸውም። የተሻለ ገንዘብ የሚያስገኙ ቦታዎች በወንዶች ተይዘዋል። ወይም የወንዶች ብቻ ናቸው ተብለው ይታሰባሉ፡፡ የሥራ ሰዓቱም እንደዛው ሚዛኑን ስቶ በርካታ ቅጂዎች ባሏቸው የሕትመት ውጤቶች ሳይቀር የሥራ ሰዓታቸው ከ10ሰዓት በላይ የሆኑ ማስታወቂያዎች ወጥተዋል፡፡ ሕግ ጣሹ ሕጉን ሲያፈርስ በመሸሽግ እንኳን አይደለም፡፡ በአሰሪዎቻቸው አስገዳጅነት እና የኑሮን ጫና ለመቋቋም ሲሉ 8 ሰዓታትን አሳልፈው እንደሚሰሩ የሚናገሩትን የነዚህን ሴቶች ጥያቄ መመለስ ከክብረ በዓሉ እንደሚቀድም ያነጋገርኳቸው በርካታ ሴቶች ይስማሙበታል።

ተመጣጣኝ ክፍያ

ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ መርህ የተጀመረው በኢንደስትሪ አብዮች (Industrial movement) አከባቢ ሲሆን በ19ኛው ክፍለዘመን 1830 ታላቋ ብሪታንያ ላይ የነበረው የሴቶች እንቅስቃሴ ምሳሌ ነው። ማርች  (መጋቢት) 31 ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ የሚለው ሃሳብ ይከበራል። በሙያ፣ በትምህርት እና በክህሎት ተመሳሳይ የሆኑ ሴት እና ወንድ እኩል ክፍያ አሁንም አያገኙም፡፡

 "ይህንን ችግር መቅረፍ የሚገባቸው የአመራር ሰዎች፣ ሕግ አውጭዎች እና ሌሎች ባለሥልጣናት የሴቶች ቀንን ማክበር የሚመስላቸው ሕጉን ማሻሻል ሳይሆን ሐበሻ ቀሚስ ለብሶ ኬክ መቁረስ ነው" ያለኝ ድርጊቱ ያማረራት ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገች የ40 ዓመት ሴት ናት፡፡

ሴቶች እና ምርጫ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኦሰመኮ) በቅርቡ ጥናትን መሰረት አድረጎ ባወጣው መግለጫ፡- በኢትዮጵያ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ በተለይም በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እና በሌሎች የምርጫ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ ሴቶች በማኅበራዊ ሚድያም ሆነ በፊት ለፊት ለተለያዩ ጾታን መሰረት ላደረጉ የቃላት እና የአካል ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ስለማረጋገጡ አትቷል፡፡

መግለጫው በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶቻቸውን መነጠቃቸውን፣ እስር፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ ከእምነት ቦታዎችም ጭምር መታገድን ጨምሮ እስከ በቤተሰብ መገለል ድረስ የተለያዩ ችግሮች እንደደረሰባቸዉ ደርሼበታለሁ ብሏል። ይህን መሰል ጾታን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እንዳይፈጸሙ የዘንድሮው አከባበር ምን አስተዋጽኦ አበረከተ? ሁሉም ለራሱ ጠይቆ ለራሱ እንዲመልሰው የምጋብዘው ጥያቄ ነው፡፡

ሴቶች እና መደበኛ ያልሆነ ገቢ

እ.ኤ.አ በ2016 የተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩት ሴት ሠራተኞች 36 በመቶ ያህሉ መደበኛ ባልሆነ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አረጋግጧል፡፡ ቋሚ ገቢ፣ የሥራ አካባቢ እና የሥራ ዋስትና የሌላቸው እነኚህ ሴቶች መደበኛውን የሕይወት እንቅስቃሴ የሚያውክ አጋጣሚ ሲኖር 'ሳይበሉ ሊያድሩ' የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡ በቅርቡ የተከሰተውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በቤት ውስጥ መቆየት ግዴታ ሲሆን፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሲዳከሙ ቀዳሚ ተጎጂ ሴቷ ነበረች፡፡ የዚህ ሰበብ ብዙ ነው፡፡ ትምህርት፣ የስነተዋልዶ መረጃ፣ የጎጂ ልማዶች በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

አካላዊ እና ፆታዊ ጥቃት

በዓለም ላይ 15 ሚሊዮን ሴቶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ያገባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 40 በመቶ ሴቶች ያለ እድሜያቸው አግብተዋል፡፡ በሌላ ዓለም አቀፍ ጥናት ደግሞ በዓመት 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴት ሕፃናት ደግሞ ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይገመታል። በዓለም 200 ሚሊዮን በኢትዮጵያ ደግሞ 65 በመቶ ሴቶች ይገረዛሉ።

 በትዳር ወይም በጾታዊ ወዳጅነት ውስጥ ሆነው በአጋሮቻቸው የሚገደሉት 38 በመቶ ያህል ሲሆኑ በህይወት ካሉት ውስጥ ደግሞ ከ5 ሴቶች መካከል አንዷ ትደፈራለች፡፡ ከ3 ሴቶች በአንዷ ላይ አካላዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት ይፈጸማል፡፡

ጥናቱ አስደንጋጭ ብሎ ባወጣው መረጃ ከ15 - 49 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ዓለም ላይ ካለ ገዳይ በሚባሉት ህመሞች ከካንሰር፣ ከመኪና አደጋ፣ ከወባ በሽታ እና ጦርነት ላይ ከሚደርሠው ጉዳት የበለጠ በአስገድዶ መደፈር ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆናቸውን ያስቀምጣል። ኢትዮጽያ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መሠረት ፆታዊ የእኩልነት መብትን ባለማክበር 116ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

~ መደምደሚያ

እነዚህ ጥናቶች እና መሬት ላይ ያሉት እውነታዎች የሚያሳዩን ‹‹ማርች 8›› የፈንጠዝያ በዓል አለመሆኑን ነው፡፡ ዕለቱን ዓመት ውስጥ አንድ ቀን አክብረን 364 ቀናት የምንረሳው አይደለም፡፡ ማርች 8 ያለፈውን ሥራችንን የምንገመግምበት፣ የወደፊቱን ትልም የምናወጣበት ትርፍ እና ኪሳራችንን የምናወራርድበት ዕለት መሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን በዓሉ በዓል ብቻ ሆኖ ይቀራል፤ ሴቷም ከችግሮቿ አትላቀቅም፡፡ 

አስተያየት