የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከግዜ ወደ ግዜ እየተስፋፉና ተደራሽነታቸውን እያሰፉ መምጣታቸው ዜጎች የመፃፍና የመናገር መብታቸውን ከሌላው ግዜ በተለየ እንዲለማመዱት ዕድል የሰጠ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን የጥላቻ ንግግር፣ የተሳሳተ መረጃ እና ገፋ ሲልም የስም ማጠልሸት ዘመቻ የሚካሄድባቸው የውጊያ አውድማዎች ላለመሆናቸው ሊቀርብ የሚችል መተማመኛ የለም ይላሉ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያዎች።
የተለያዩ አገራት በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የሚተላለፉ የሐሰት መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል ሕግ ከማውጣት ጀምሮ መሰል ስራዎችን የማጣራት እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ስራ እንደሚያከናውኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ይረዳል የተባለ አዋጅ በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ተግባር ገብቷል። የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች ተላልፈው የሚገኙ ሁሉ የማኅበራዊ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ የእስራት እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ያስቀምጣል።
ለመሆኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ተግባር ከገባ አንድ አመት ያስቆጠረው ይህ አዋጅ ተግባራዊ እየተደረገ ነው? ይህ አዋጅ የሰዎችን የመናገር መብት ይገድባል? እንደተባለው የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል አስችሏል? ስንል የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።
ማንነቴን አትጥቀሱ ያሉ አንድ የሕግ ባለሙያ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “ከጅምሩ ይህ አዋጅ ሊወጣ የቻለው የሰዎችን እንደልብ የመናገር መብት ለመገደብ ታስቦ እንጂ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል አይደለም።” እንደ ባለሙያው አስተያየት ከሆነ አንድ አካል የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ተካሄዷል ብሎ ክስ የሚያቀርበው በምን መስፈርት ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ።
“ለምሳሌ በአንድ አካባቢና ማኅበረሰብ ውስጥ የሚነገሩ ንግግሮች ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱ የጥላቻ ንግግር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ስለዚህ ይህንን አዋጅ ጠቅሶ ክስ የሚያቀርበው አካል በምን መስፈርት ነው የጥላቻ ንግግር ተነግሯል ብሎ ክስ የሚመሰርተው” ሲሉ ይሞግታሉ።
“የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትም ቢሆን መንግስት እንዲነገሩበት የማይፈልጋቸውን መረጃዎች አፍኖ ከያዘ በኋላ በአንድም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ይህንን መረጃ አግኝተው የሚያሰራጩ ሰዎችን እንዴት አፍኜ የያዝኩት መረጃ ወጣብኝ የሚል ምክንያትን መሰረት በማድረግ የሐሰተኛ መረጃ ለመከላከል ይረዳል የተባለውን አዋጅ ጠቅሶ የሐሰት ክስ ሊመሰርት ይቻለዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን ከላይ በሕግ ባለሙያው በቀረበው ሃሳብ አይስማሙም። “ይህ አዋጅ የዜጎችን በነፃነት የመናገር መብት ለመገደብ ታስቦ የወጣ አዋጅ ሳይሆን በሰዎች ላይ የሚደርስን የጥላቻ ንግግርና ብዙዎችን እያሳሳተ የሚገኘውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመገደብ አላማ ያደረገ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
“አዋጁ ከበስተጀርባው የያዘው ሌላ መብትን የመገደብ ዓላማ የለውም የሚሉት አቶ አወል ሰዎችን መቅጣት እና ማሰር ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ትልቁ ነገር የንቃተ ሕግ ስራ መስራት እና ማኅበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ኖሮት እራሱን እና ሌሎችን መጠበቅ እንዲችል ማድረግ ስለሆነ ይህንኑ ማድረግ እስከምንችል ድረስ አሁን ያለው የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ያስችላል የተባለውን አዋጅ ወደ ተግባር እየተረጎምነው አይደለም” ብለዋል።
“የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት እና በአገሪቱ ዉስጥ ባሉ በሁሉም የመገናኛ መንገዶች በዘመቻ መልክ ስለ አዋጁ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሰራ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ “ከአሁን በኋላ ግን ማኅበረሰቡ ዉስጥ በቂ ግንዛቤ አለ ብለን ስለምናምን ወደ ህግ ማስፈፀም የምንገባ ይሆናል፤ ነገር ግን እስካሁን ይህንን አዋጅ ጠቅሰን ያስቀጣነው ሰዉ የለም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ወደ ስራ ስትገቡ እንዴት አድርጋችሁ ነው በተሳሳተ ገፅ “የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት መረጃ” ያስተላልፋሉ የሚባሉ አካላትን ከሳችሁ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የምታስቀጡት በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ አወል በደፈናው “ይህ የቴክኒክ ስራ ነዉ፤ ከዚህም በላይ በዉጭ አገር ሆነዉ መሰል ድርጊት የሚፈፀሙትን መቆጣጠር የሚያስጭል አሰራር አለዉ፤ ከዚህ ቀደምም በዚህ ዙሪያ በሰራነዉ ስራ ዉጤታማ ሆነንበታል” ሲሉ መልሰዋል።
ዳይሬክተሩ “ሰርተነው ውጤታማ ሆነንበታል” ያሉትን ስራ “ቴክኒካዊ ጉዳይ ነው” በሚል ሰበብ በዝርዝር ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
“የጥላቻ ንግግር መዘዙ ብዙ ነዉ፤ እንዲህ በቃል እንደሚነገረዉ ቀላል አይደለም” የሚሉት በፌደራል የሕግ ስልጠናና ምርምር ተቋም የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ገብረመቀስል ገብረዋህድ “የጥላቻ ንግግር መሰረቱ የሚጣለዉ በጥቁር እና ነጭ መካከል ከነበረዉ ግዜ ጀምሮ እንደሆነ” ያነሳሉ።
የሕግ ባለሙያው የጥላቻ ንግግር ዘመቻ ውጤቱ ሰፊ እንደሆነና የጀርመን ናዚ በአይሁዶች ላይ ያስከተለዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፤ በሩዋንዳ ከ800 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች እልቂት እንዲሁም በአገራችን በቅርብ ጊዜ በተለይ እየተስተዋለ ያለዉ ችግርን በተምሳሌትነት ያነሳሉ።
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ አዋጁን የተላለፈ አካል የማኅበራዊ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጣ እንደሚችል ተቀምጧል።
የአለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀፅ 19 “ሁሉም ሰዉ የማሰብ እና ሃሳቡን የማንፀባረቅ መብት አለዉ” የሚል ድንጋጌ ያስቀመጠ ሲሆን ነገር ግን ይህ በሌሎች ላይ ጉዳት እንዳደርስ እና ሌሎችን ለመጠበቅ ሲባል በአንቀፅ 12 ላይ “ማንም ሰዉ በክብሩ እና እና በመልካም ስሙ ላይ ጥቃት ሊደርስብት አይገባም” ሲል ይደነግጋል።