በዛሬው ዕለት ማለትም መጋቢት 6፤ 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እጅግ ረጃጅም የታክሲ ጥበቃ ሰልፎች ታይተዋል።
በርግጥ ለወትሮውም ቢሆን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ረጃጅም ሰልፎችን ማስተናገድና ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መቆየት የተለመደ ቢሆንም የዛሬው ሰልፍ ግን ከከዚህ ቀደሙ በጣም የተለየ መሆኑንና ኅብረተሰቡን ለማስተናገድ የተሰማሩት 12 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው ታክሲዎች ቁጥር ማነስን መሰረት በማድረግ የታክሲ ባለንብረቶችን፣ ተራ አስከባሪዎችንና የመዲናይቱን የትራንስፖርት ቢሮ ይህ ለምን ሆነ ስንል አነጋግረናል።
ያነጋገርናቸው ተራ አስከባሪዎች እንደነገሩን ከሆነ “የታክሲ ባለንብረቶች የትራንስፖርት አገልግሎት ላለመስጠት አድማ መተዋል።” “በጣም ረጅም ሰልፍ የተከሰተበትና ሰዎች ረዘም ላለ ደቂቃ የትራንስፖርት አገልግሎት ሳያገኙ እንዲጉላሉ የሆነበት ምክንያትም ይህ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
አገልግሎት በመስጠት ላይ እያለ አግኝተን አስተያየቱን የጠየቅነው ግለሰብ ማንነቱን እንዳንጠቅስ ከነገረን በኋላ በሰጠን አስተያየት “በርግጥም የታክሲ ሹሮችና ባለንብረቶች በዛሬው ዕለት ስራ የማቆም አድማ መተዋል” ሲል ገልፆልናል።
እርሱ ይህንን አድማ ለምን እንዳልተቀላቀለ የጠየቅነው ይህ የታክሲ ባለንብረት “ሶስት ልጆች እንዳሉትና የዚህ አድማ ተሳታፊ ቢሆን ልጆቹን የሚያበላቸው ነገር እንደማይኖር እንዲሁም ገቢው ከዕጅ ወደ አፍ እንደሆነ ነግሮናል።”
12 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው የታክሲ ባለንብረቶች መቱ የተባለውን አድማ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ “ባለንብረቶቹ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ባለማቆማቸው ምክንያት አድማ ተመቷል ለማለት እንደሚያዳግት” ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሆነ “ብዙ የታክሲ ባለንብረቶች ይህንን አድማ አልተቀላቀሉም።”
ታዲያ ከወትሮው በተለየ መንገድ እጅግ በጣም ረጃጅም የታክሲ ጥበቃ ሰልፎች የታዩበት ምክንያት ምንድን ነው ያልናቸው ዳይሬክተሩ “ሁሉም ሳይሆኑ የተወሰኑት ስራ በማቆማቸው ምክንያት የተፈጠረ ነው ሱሉ ተናግረዋል።”
“ከተለመደው ቁጥር ዝቅ ያለ ታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ” ያልካዱት አቶ አረጋዊ ባሳለፍነው “ሳምንትም ምልክት ታይቶ ነበር” ሲሉ ከገለፁ በኋላ “የታክሲ ባለንብረቶቹ ሶስት ጥያቄዎች እንዳሏቸው አንስተዋል።”
አንደኛው ጥያቄ “በተደጋጋሚ ጥፋት ፈፅመው የሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የቅጣት መጠን በዝቷል የሚል ሲሆን” ሁለተኛው ደግሞ “የመለዋወጫ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የትራንስፖርት ዋጋ ላይ ማሻሻያ ይደረግ” የሚል እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
ሶስተኛው ጥያቄ “ጠዋት ላይ ወደተመደብንበት መስመር ስንሄድ እግረመንገዳችንን ሰዎች አሳፍረን እንጓዝ” የሚል እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ “የትኛውም አይነት ጥያቄ ግን መቅረብ ያለበት ስራ በማቆም ሳይሆን በተደራጀ መንገድ በማህበራት በኩል ለሚመለከተው አካል በማቅረብ እንደሆነ” ተናግረዋል።
“የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የወቅቱን ሁኔታ ጨምሮ የመለዋወጫ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ ማስተካከያ ተደርጓል” የሚሉት አቶ አረጋዊ “አሁን ያለውን ግዜያዊ የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት ግን የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው” ብለዋል። በዚህም “የሸገር፣ አንበሳ እና ቅጥቅጥ አውቶብሶችን በየመስመሮቹ እንዲሰማሩ እያደረግን ነው” ሲሉ ገልፀዋል።
አድማው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የእናተ ቢሮ ምን እርምጃ ሊወስድ ይችላል ያልናቸው ዳይሬክተሩ “እርሱን በሂደት እናየዋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።
አዲስ ዘይቤ ባደረገው ቅኝት መታዘብ እንደቻለው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሰዎች ታክሲ ጥበቃ ረጅም ሰልፍ ይዘው ለረጅም ደቂቃዎች ቆመው ተመልክቷል።